News

የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ለኦዲት ግኝቶች ትኩረት በመስጠት ህግና መመሪያ ጠብቆ ሊሠራ እንደሚገባ ተገለፀ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የ2008 በጀት ዓመት ሂሳብ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ያደረገው የሂሳብ ኦዲትን መሰረት በማድረግ ይፋዊ ስብሰባ መጋቢት 17፣ 2010 ዓ.ም ባካሔደበት ወቅት ዩኒቨርስቲው ለኦዲት ግኝት ትኩረት በመስጠት ህግና መመሪያን ተከትሎ ሊሠራ እንደሚገባ አሳሰበ፡፡
በይፋዊ ስብሰባው ቋሚ ኮሚቴው የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ከህግና መመሪያ ውጭ ፈፅሟቸዋል በተባሉ አሠራሮች ላይ ጥያቄዎችን አቅርቦ የተቋሙ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሠጡ አድርጓል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ባቀረባቸው ጥያቄዎች ዩኒቨርስቲው በበጀት ዓመቱ ብር 4,682,383.93 በትክክለኛ የወጪ ሒሳብ አርዕስት ሳይመዘግብ መገኘቱ፤ ከዶልቼ ኢንጂነሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር የኤሌክትሪክ፣ የውሃና የጥገና ብር 158,742.57 እንዲሁም ለዩኒቨርስቲው የምክክር መድረክ መከፈል የሚገባው ብር 20,000 በድምሩ 178,742.57 የበጀት ዓመቱን ሳይጠብቅ የወጣ ወጪ መሆኑ፤ በብር 170,722.78 የተለያዩ ግዢዎች የተፈፀመባቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች የንግድ ሥራ ፈቃድ እያላቸው ህጋዊ ያልሆነ ደረሰኝ አቅርበው ክፍያ ተፈፅሞ መገኘቱ፤ በተለያዩ የድጋፍ ክፍያዎች መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት በድምሩ ብር 1,060,000.00 የክፍያ ደረሰኝ ሳይቀርብ መከፈሉንና የተከፈለው ሒሳብ በበጀት ዕቅድ ዘመን በበጀት አርዕስት ያልተካተተ መሆኑ እና የህዋ ሳይንስ በተማሪዎች ዘንድ ለማስረፅና ዝንባሌያቸውን ለማሳደግ በክልል ደረጃ እና በዩኒቨርስቲ ውስጥ ፈተና ለፈተኑ መምህራን በመንግስት የተፈቀደ የክፍያ ተመን ሳይኖርና በውል ሳይያዝ የዩኒቨርስቲው ሥራ አመራር በወሰነው መሠረት ለ5 ፈታኞች በድምሩ ብር 24 ሺህ ተከፍሎ እንደተገኘ የኦዲት ግኝቱ ተገልጿል፡፡
ያለጨረታ የተፈፀሙ ግዥዎችን በተመለከተ ዩኒቨርስቲው በብር 69,476,518.45 የተለያዩ ግዢዎችን ከህግ፣ ደንብና መመሪያ ውጪ ያለምንም ውድድር በቀጥታ ግዢ ፈፅሞ መገኘቱ፤ ለህክምና ት/ቤት የዩኒቨርስቲው ተቀጣሪ ያልሆኑ ሐኪሞችን ከመመሪያ ውጪ በቁርጥ ክፍያ ውል በመያዝ ከጫና በላይ የትርፍ ሰዓት ክፍያ በሚል በድምሩ ብር 975,694.85 ከፍሎ መገኘቱ፤ ለግንባታ ፕሮጀክት ፅ/ቤት በተፈቀደው የኮንትራት ሥራ መደብ መሠረት ሥራ አስኪያጅ፣ ምክትል ሥራ አስኪያጅና ባለሙያዎች ባላቸው የሥራ ልምድ አወዳድሮ ዩኒቨርስቲው መቅጠር ሲገባው ያለውድድር ቦታውን ለመምህራን በመስጠት ጥቅማ ጥቅሞች እንዲከፈላቸው ማድረጉ፤ ለባለሙያዎች ማበረታቻ በሚል በወር ብር 4,000.00 እንዲከፈላቸው በሥራ አመራሩ የተወሰነው የክፍያ ስሌት ከሲቪል ስርቪስ መመሪያ ውጪ የሆነና በምን ስሌት እንደተሠራ የሚያስረዳ ማስረጃ የሌለ መሆኑ፤ ግንባታዎችን ክትትል ለሚያደርጉ ባለሙያዎች ብር 40,265፣ ለተለያዩ የዩኒቨርስቲው የአስተዳደር ሠራተኞች 477,197.71፣ ለሰርቪስና አንቡላንስ ሹፌሮች ብር 11,152.00፣ ለሐኪሞችና ስፔሻሊስቶች ከውስጥ ገቢ ብር 462,072.00 በድምሩ ብር 990,686.71 የማበረታቻ ክፍያና የትርፍ ሰዓት ክፍያ ከህግ፣ ከደንብና ከመመሪያ ውጭ ተከፍሎ መገኘቱ በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በኮንስትራክሽንና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ዙሪያ ዘላላም ሥራ ተቋራጭ ድርጅት በብር 25,309,962.09 ለሚገነባው ግንባታ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ውጪ ከውሉ 30% (ብር 7,592,988.62) ብቻ የተጨማሪ ግንባታ ሥራ መሰራት ሲገባው ከመመሪያ ውጭ የብር 26,374,222.23 (104.2%) ተጨማሪ ግንባታ ሥራ መፈፀሙ፤ የጂ አይ ዜድ አይ ኤስ (GIZ-IS) ድርጅት ትምህርት ሚኒስቴር ባሳተመው ደረሰኝ ከተለያዩ ኮንትራክተሮች የሰበሰበውን ብር 682,243.73 ተጨማሪ እሴት ታክስ ወደ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን ገቢ ስለማድረጉ ማስረጃ ሊያቀርብ አለመቻሉ፤ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ዩኒቨርስቲው በተለያዩ የሒሳብ መደቦች በድምሩ ብር 3,137,589.86 ከ2001 እስከ 2008 በጀት ዓመት መወራረድ ሲገባው ያላወራረደ መሆኑ እና በወቅቱ ለሚመለከታቸው አካላት መከፈል ሲገባቸው ያልተከፈሉና በበጀት ዓመቱ መጨረሻ መወራረድ ሲገባቸው ያልተወራረዱ ከ2001 እስከ 2008 በጀት ዓመት የቆዩ በድምሩ ብር 682,877.12 ተከፋይ ሒሳቦች መኖሩ ተገልጿል፡፡
በጀትን በተመለከተም ለዩኒቨርስቲው የተመደበ የተስተካከለ በጀትና በሥራ ላይ የዋለው የወጪ ሒሳብ ሲመዛዘን ከመደበኛና ከካፒታል በጀት በድምሩ ብር 2,430,240.07 በተለያዩ የበጀት ርዕሶች ከ10% በላይ ሥራ ላይ ያልዋለ በጀት መኖሩ፤ በ2008 በጀት ዓመት በ4 ግለሰቦች ስም እንቅስቃሴ የሌለውና ባልተለመደ ሒሳብ ምዝገባ ሚዛን የተያዘ በድምሩ ብር 22,662.91 መኖሩ እና ከ2002 እስከ 2008 በጀት ዓመት በሌጀር ላይ በተለያዩ ግለሰቦች ስም ብር 36,532.22 ተከፋይ ሒሳብ ተመዝግቦ መገኘቱ በኦዲቱ ታይቷል፡፡
የንብረት አያያዝን በተመለከተም በዩኒቨርስቲው አሮጌ ጎማዎች፣ የተሽከርካሪ ባትሪዎች፣ የአርማታ ብረቶች፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው የተለያዩ መድሃኒቶች ተለይተው ሳይወገዱ ለብዙ ጊዜ እንደተቀመጡ፤ 14 ቴሌቭዥኖች፣ 400 አሮጌ ፍራሾች ለብልሽት እየተዳረጉ እንደሚገኙ፤ የንብረት መዛግብቶች ሥራ የማከናወን እና የንብረት የመያዝ ሥራ በአንድ ሠራተኛ እንደሚሠራ፤ ግንባታቸው ተጠናቆ በንብረትነት ርክክብ ያልተደረገባቸውን ህንጻዎች የተሟላ ታሪክ የሚያስረዳ ምዝገባ አለመደረጉ ተገልጿል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በኦዲት ሪፖርቱ ከተገለጹ ግኝቶች ጋር በተያያዘ ደንብና መመሪያ ውጪ ለምን ተግባራቱ እንደተፈፀሙና ተፈፅመዋል የተባሉ ስህተቶችን ለማስተካከል የተሰሩ የእርምት ስራዎች ምን እንደሆኑ የዩኒቨርስቲው አመራሮች እንዲያስረዱ ጠይቋል፡፡
አቶ ደሳለኝ በቀለ በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የፋይናንስና በጀት አስተዳደር ዳይሬክተር በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ዩኒቨርስቲው የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ የድርጊት መርሃ ግብር አዘጋጅቶ በተነሱት ችግሮች ላይ የእርምት እርምጃዎችን ሲወስድ እንደቆየና የማስተካከያ ሥራዎችን መሥራት እንደተቻለ ገልፀዋል፡፡
የወጪ ሒሳብ መደብን ጠብቆ አለመመዝገብን በተመለከተ የተጠቀሰው ግኝት በዩኒቨርስቲው የስፖርት ትምህርት ክፍል ማስተማሪያ እቃዎች የተመለከተ መሆኑንና ስህተቱ የተፈጠረው በግዥ ሒደት እቃዎቹ መመዝገብ የነበረባቸው በቋሚ እቃ ሆኖ ሳለ በመማር ማስተማር በመመዝገባቸው እንደሆነ፤ ከዶልቼ ኢንጂነሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በተመለከተም ድርጅቱ እቃዎቹን በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ በማቅረቡና የእቃዎቹን ጥራት አይቶ ለመረከብ ጊዜ በመውሰዱ በቀጣዩ በጀት ዓመት ላይ ክፍያው ሊፈፀም መቻሉን፤ ህጋዊ ያልሆነ ደረሰኝ ሳያቀርቡ ክፍያ ተፈፅሟል የተባለውም ግዥዎቹ የተፈፀሙት በአማራ ክልል ከሚገኙ ህጋዊ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ ነጋዴዎች በሚያቀርቡት ደረሠኝ የተፈፀመ መሆኑን፤ ለድርጅቶች የተደረገ ድጋፍን በተመለከተ ድጋፍ ከተደረገላቸው ውስጥ ደረሰኝ ያቀረቡ እንዳሉና ሁለት ድርጅቶች ግን ደረሰኝ ማቅረብ ባይችሉም የባንክ ገቢ ደረሰኝ ማቅረባቸውን፤ የህዋ ሳይንስን በተመለከተ ለአማራ የዩኒቨርስቲዎች ፎረም ቀርቦ የተወሰነና የዩኒቨርስቲው ማኔጅመንት የጉዳዩን ጠቀሜታ አይቶ በወሰነው መሠረት ፈተና ለፈተኑ መምህራን የቁርጥ ክፍያ መፈፀሙንና ከኦዲት አስተያየት በኋላ መሰል ክፍያዎች እንዲቆሙ መደረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
ያለጨረታ የተከፈሉ የተለያዩ ግዢዎችን በተመለከተ አቶ ደሳለኝ ምላሽ ሲሰጡ ዩኒቨርስቲው በርካታ ግዥዎችን የሚፈፅመው ዩኒቨርስቲው ካቋቋመው የመንቆረር አግሮ ኢንዱስትሪ መሆኑን፤ የሆቴል መስተንግዶ ግዥም ያለውድድር የሆነው በከተማው ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ባለመኖራቸው በማኔጅመንት ውሳኔ የተመረጡ ሆቴሎች ላይ የአገልግሎት ግዥ እንደተፈፀመ፤ የምግብ ዘይትም ከሞጆ ዘይት ፋብሪካ የቀጥታ ግዥ በማኔጅመንት ውሳኔ መፈፀሙንና ከኦዲት አስተያየቱ በኋላ ባለው ዓመት ግዥዎች ሲፈፀሙ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲን በማስፈቀድ ማስተካከላቸውን አስረድተዋል፡፡
መመሪያን ያልተከተለ ክፍያን በተመለከተ የሐኪሞች የትርፍ ሰዓት ክፍያ መንግስት በፈቀደው የሰዓት ክፍያ (Credit Hour) መሠረት መፈፀሙን አስረድተዋል፡፡
ከግንባታ ፕሮጀክቶች ጽ/ቤት ጋር በተያያዘ በዩኒቨርስቲው ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ የተለያዩ የግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ገልጸው ለሥራው ባለው መስፈርት ባለሙያዎችን ከገበያ ላይ አወዳድሮ ለመቅጠር የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ለመምህራን ክፍያ በመፈፀም ሊያሰሩ እንደቻሉ፤ የአስተዳደር ሠራተኞችን ያለአግባብ ተከፍሏል የተባለውን ክፍያም በሲቪል ሰርቪስ የለውጥ ፕሮግራሞች ላይ ለተሣተፉ ሠራተኞች የአከፋፈል መመሪያ ዩኒቨርስቲው በማዘጋጀት እንደተከፈለና በኋላም ከሲቪል ሰርቪስ የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር በተሰጠው አስተያየት መሠረት ክፍያዎቹን ማቋረጣቸውን፤ ቅዳሜና እሁድ የሰርቪስ አገልግሎት ሲሠጡ ለነበሩ ሹፌሮች የነበረው አከፋፈል ስህተት መሆኑ ከተገለፀ በኋላ መቆሙን፤ ለሐኪሞችና ስፔሻሊስቶች የተከፈለ ክፍያም በአሠራር ላይ በነበረ የግንዛቤ ችግር የተፈፀመ እንደሆነ፤ ለዘላለም አስማረ የህንጻ ስራ ተቋራጭ ከተሰጠ ከኮንስትራክሽን መሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ ዩኒቨርስቲው የፍሳሽ ቆሻሻ ፕሮጀክት እያስገነባ ቢገኝም ፕሮጀክቱ መዘግየቱንና ረጅም ጊዜ የወሰደ እንደሆነ ገልፀው ፕሮጀክቱን የመከታተል ሚና ያላቸው የትምህርት ሚኒስቴር እና ጂ አይ ዜድ መሆናቸውን አቶ ደሳለኝ አስረድተዋል፡፡
ፈሰስ ለመደረጉ ማስረጃ ያልቀረበበትን የተጨማሪ እሴት ታክስን በተመለከተ አቶ ደሳለኝ ሲያስረዱ በ2007 ዓ.ም ለተጨማሪ እሴት ታክስን ለገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን ገቢ ማድረጉን ነገር ግን በኦዲት ትክክል እንዳልሆነ በተገለጸላቸው መሠረት በ2008 ሲቋረጥ እንደገና ለምን ገቢ አልተደረገም የሚል የሚጣረስ አስተያየት እንደተሰጣቸው እና ችግሩ ከዩኒቨርስቲው አቅም በላይ መሆኑን አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡
ከውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳቦች ጋር በተያያዘ ዩኒቨርስቲው ከኦዲት ግኝት በኋላ ኮሚቴ በማዋቀር እያንዳንዱን ግኝት በማጣራትና ባለቤቱን በመለየት ከግለሰብና ከተለያዩ አካላት ሂሳቦቹ እንዲመለሱ ጥረት መደረጉንና በህግ አግባብ መታየት ያለባቸውንም በመለየት በፍርድ ቤት እንዲታዩ እየተደረገ መሆኑን እና ከአገር ውጪ የወጡ አካላትና ዋስትና ያልተገኘባቸው ግለሰቦች ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ለበላይ አካል ማሳወቃቸውን፤ ከተከፋይ ሒሳብ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርስቲው ሥር ነቀል እርምጃ መውሰዱን ገልፀው ከ396ሺህ ብር በላይ ለሚመለከታቸው አካላት ክፍያዎች እንዲፈፀሙ መደረጉንና ቀሪ ከ286 ሺህ ብር በላይ ሒሳብ ውሳኔ ያልተሰጠባቸውና በቀጣይ መፍትሔ እንዲሠጥባቸው ለማድረግ ጥረቱ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
በሥራ ላይ ያልዋለ የመደበኛ እና ካፒታል በጀት ጋር በተያየዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነጋዴዎች ከዩኒቨርስቲው ጋር ውል ይዘው በወቅቱ እቃ ሳያቀርቡ በመቅረታቸው ያልተከፈለ እና ለመምህራን ቅጥር ማስታወቂያ ወጥቶ ባለመቀጠራቸው በጀቱ ሥራ ላይ ሳይውል መቅረቱን እና ባልተለመደ ሒሳብ ሚዛን የተያዘ የመደበኛ በጀት ተሰብሳቢ ሒሳብና ተከፋይ ሒሳብ የተገኘውን ግኝት ከኦዲት አስተያየት በኋላ ሙሉ በሙሉ ማስተካከላቸውን አቶ ደሳለኝ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ታደሰ ጤናው በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት በቋሚ ኮሚቴው በተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ተጨማሪ ምላሽ ከንብረት አያያዝ ጋር በተያያዘ የተሽከርካሪ ባትሪዎችና የአርማታ ብረቶች በሽያጭ እንዲወገዱ ተደርጎ ገንዘቡ ገቢ መደረጉን፤ በመጋዘን ተቀምጠው ከነበሩት 14 ቴሌቭዥኖች ውስጥ ሰባቱ ተጠግነው አገልግሎት እንዲሠጡ መደረጉንና ቀሪዎቹ በጥገና ላይ እንደሚገኙ፤ የንብረት ምዝገባና ንብረት አያያዝ በአንድ ሠራተኛ እንዲከናወን የተደረገው ክፍሉ በሁለት ሰው የሚሠራ ሥራ የሌለው በመሆኑ እንደሆነ፤ በህንጻ አስተዳደር በኩል የአስተዳደር ህንፃዎች ምዝገባ መደረጉንና ከህንፃዎቹ ውስጥ ርክክብ የተደረገባቸውና ያልተደረገባቸው እንዳሉና ለመምህራን መኖሪያ የሚሆን 10 ኮንዶሚኒየም ህንጻዎች ገዝቶ ርክክብ መፈፀሙን ነገር ግን ታሪካቸውን ለመመዝገብ በፕሮጀክት ጽ/ቤት በኩል በሂደት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በዩኒቨርስቲው አመራሮች የተሰጡትን ምላሾች ካዳመጡ በኋላ ሊሻሻሉና ሊታረሙ ይገባሉ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በተሰጠው አስተያየት መሠረት መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት ከተከፈለው ገንዘብ ጋር በተገናኘ ዩኒቨርስቲው ለተለያዩ ድርጅቶች የሚያደርጋቸው ድጋፎች ተገቢ አለመሆናቸውን፤ ግዥዎች በግዥ መመሪያ የሚፈፀሙ እንጂ በማኔጅመንት ስብሰባ የሚወሰኑ አለመሆናቸው ታውቆ መሰል አሠራሮች በአፋጣኝ ሊታረሙ እንደሚገባ፤ ማንኛውም ገቢ በህጋዊ የገቢ ደረሰኝ ሊያዝ እንደሚገባ፤ መምህራን በግንባታ ሥራዎች ላይ እንዲሣተፉ ማድረግ የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚጎዳና ተገቢ አሠራር ባለመሆኑ መስተካካል እንዳለበት፤ ጥቅማጥቅም ክፍያዎች በህግና መመሪያ መሠረት ሊፈፀሙ እንደሚገቡ፤ ዩኒቨርስቲው ህጋዊ አሠራርን በማስፈን አርአያነት ያለው ማካሄድ እንደሚጠበቅበት እና የበጀት አጠቃቀሙን የተሻለ ለማድረግ ዕቅዱን በወቅቱ ማሻሻል እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር በሰጡት አስተያየት ከጂ አይ ዜድ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ እሴት ታክስ የሰበሰበው ጂ አይ ዜድ እንደመሆኑ ታክሱን ገቢ ማድረግ ያለበትም ዩኒቨርስቲው ሳይሆን ጂ ኤ ዜድ ሊሆን እንደሚገባ፤ በ2008 ዓ.ም የተሰጡ አስተያየቶች ሳይሻሻሉ በ2009 በጀት ዓመትም ችግሮቹ መደገማቸውን አስቀምጠው የተቋሙ አመራሮች በኦዲት ግኝቱ መሠረት እየሠራን ነው ይበሉ እንጂ በተግባር የተለወጠ ነገር እንደሌለና ዩኒቨርስቲው ለኦዲት አስተያየት የሚሰጠው ስፍራ በጣም አናሳ እንደሆነ ገልጸው ከዚህ አይነት አመለካከት መውጣት እንዳለበት አስገነዝበዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሰጡት አስተያየት የስፖርት እቃዎችን ምዝገባ ከማስተካል ባለፈ በተጨማሪ ሌሎች ንብረቶችም በዚሁ አግባብ ተስተካክሎ እንዲመዘገቡ ማድረግ እንደሚገባ፤ ከግዥ ጋር በተያያዘም በዋናነት ግዥ የሚፈፀመው የፌዴራል መንግስት የግዥ ሥርዓትን ተከትሎ መሆኑ ታውቆ ግዥዎች ከየትም ቦታ ሲፈፀሙ ህጋዊ ደረሰኝ ከሚያቀርቡ አካላት ብቻ ሊሆን እንደሚገባ፤ ዩኒቨርስቲው ለተለያዩ ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አቁሚያለው ይበል እንጂ ድጋፎቹ በ2009 በጀት ዓመትም መቀጠላቸውንና የሚደረገው ድጋፍ ተገቢ መሆኑ ከታመነም በበጀት አስቀድሞ መያዝ እንደሚያስፈልግ፤ ከህዋ ሳይንስ ጋር በተያያዘ ዓላማው ጥሩ መሆኑን ገልፀው ነገር ግን የአሠራር ሥርዓት ሊበጅለት እንደሚገባ፤ ያለጨረታ ግዢ መፈፀምን በተመለከተ መመሪያ የተዘጋጀው ግልፅ አሠራር እንዲኖር ለማድረግ፣ ህገወጥ አሠራርን ለመቅረፍና የውድድር ሥርዓትን ለመፍጠር እንደሆነ በመግለፅ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲም ቢሆን ከዚህ ድርጅት ግዙ ብሎ ማዘዝ እንደማይችል ገልፀዋል፡፡
መመሪያን ያልተከተሉ የመምህራን ክፍያ ጋር በተያያዘ የኮንታክት አወር (Contact Hour) እና ክሬዲት አወር (Credit Hour) ክፍያዎቹ የሚለያዩ ከሆነ ግልፅ ሆነው እንዲቀመጡ ለሚመለከተው አካል አሳውቆ ግልፅ መመሪያ እንዲወጣለት ማድረግ እንደሚያስፈልግ፤ የግንባታ ፕሮጀክትን በተመለከተ አስተማሪዎቹን ከትምህርት ሥራቸው አምጥቶ ግንባታ ላይ እንዲሣተፉ የሚደረጉ ከሆነ የማስተማር ሥራው እየተሰራ እንዳልሆነ ስለሚገልፅ ሊታረም የሚገባው አሠራር እንደሆነ፤ የጥቅማጥቅም ክፍያን በተመለከተ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቋረጥ መወሰኑን ተከትሎ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር መመሪያ ማስተላለፉንና የዩኒቨርስቲ አመራር መመሪያውን ሊተላለፍ እንደማይችል፤ ለአስተዳደር ሠራተኞችና ሹፌሮች የተከፈሉ ክፍያዎችን በተመለከተም በተለይ ከውስጥ ገቢ የሚከፈሉ ክፍያዎች ሲፈፀሙ ፀንተው ያሉ ህግና ሥርዓቶችን ጠብቆ መሆን እንዳለበት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መመሪያ ማስተላለፉን፤ አንድ ሠራተኛ በሁለት የሥራ ኃላፊነቶች ላይ እንዲሠራ የተደረገበት አግባብ የንብረት አስተዳደር ላይ ግልጽነት የሚፈጥር ባለመሆኑ በሁለቱም መደብ ተገቢው የሰው ሃይል ሊቀጠር እንደሚገባ፤ ከጂ አይ ዜድ ጋር በተያያዘ መንግስት በጀት የፈቀደው ለዩኒቨርስቲው እንደመሆኑ መጠን ዩኒቨርስቲው ድርጅቱ ተጨማሪ እሴት ታክስ ለገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን ማስገባቱን የመከታተል ህጋዊ ግዴታ እንዳለበት ገልፀው ዩኒቨርስቲው የፋይናንስ ሥርዓቱን ህጋዊ አሠራርን ተከትሎ ተግባራዊ እንዲሆን ትከረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አቶ ገመቹ አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በመጨረሻ በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርስቲው የኦዲት ግኝትን መሠረት አድርጎ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ የማሻሻያ እርምጃ መውሰዱ ጅምሩ ጥሩ መሆኑን ገልፀው በኦዲት ግኝት መሠረት እርምት የተወሰደባቸውን ጉዳዮች ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንደሚገባ፤ መመሪያንና ደንብን ያልተከተሉ አሠራሮች ተገቢ ባለመሆናቸው ህጋዊ አሠራር ሊከተሉ እንደሚገባ፤ ከአቅም በላይ የሆኑ የአሠራር ችግሮች ካጋጠሙም መመሪያውን ከሚያወጣው አካል ጋር በመነጋገር መፍትሔ ሊፈለግ እንደሚገባ፤ የውስጥ ኦዲትንም በአደረጃጀት ደረጃ በአግባቡ በማደራጀትና የውስጥ አቅም አንዲሆን መስራት እንደሚያሻ፤ ከግዥ ጋር በተያያዘም ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ዩኒቨርስቲው በእቅድ መመራትና ከቁጥቁጥ ግዢ መውጣት እንደሚገባው እንዲሁም የትምህርት ተቋማት አርዓያ በመሆን ከኦዲት ግኝት ሊወጡ የሚገባ በመሆኑ ዩኒቨርስቲው አሠራሩን በፍጥነት ሊያሻሽል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *