News

የዩኒቨርሲቲ የምርምር ውጤቶች የሀገሪቱን ችግሮች በተጨባጭ የሚፈቱ መሆን እንደሚገባቸው ተጠቆመ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የምርምር በጀት አስተዳደር ስርዓትና ሌሎች የምርምር ሂደቱን የሚመለከቱ ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ በ2012/2013 በጀት ዓመት ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት መሠረት ያደረገ ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት ሚያዚያ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የዩኒቨርሲቲውን የምርምር ስርዓት በሚመለከት በተካሄደው ኦዲት የታዩ ግኝቶችን ለማስተካከል የተወሰዱ እርምጃዎችን አስመልክቶ ከቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው  የምርምር ፈንድ አስተዳደር ስርዓት ግልጽነት የጎደለው፣ ለምርምር የተመደበው በጀት ተግባራዊነትም ምቹ ያለመሆኑ እና የተናበበና የተጣጣመ የተመራማሪዎች ትስስር እንዲሁም ከሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ጋር መፈጠር ያለበት የቅንጅት አሠራር ዝቅተኛ መሆኑም በኦዲቱ መታየቱ በመድረኩ ላይ ተጠቁሟል፡፡

ለምርምር የሚፈቀድ በጅት በቂ ያለመሆንና እርሱም ቢሆን ዘግይቶ የሚለቀቅ በመሆኑ በተመራማሪዎች ስራ ላይ ችግር መፍጠሩ እንዲሁም ቅድሚያ በሚሰጣቸው የምርምር መስኮች ቅደም ተከተል ላይ ወቅታዊ ክለሳ አለመደረጉ፣ የምርምር ግብአቶች ግዥ ሥርዓቱም የምርምር ባህሪን ያላገናዘበ መሆኑ፣ የምርምር ውጤቶች በሀገራዊ ልማት ላይ ያመጡት አዋንታዊ ተጽዕኖን ለማወቅ መደረግ የሚገባው የክትትል ግምገማ አለመከናወኑና በምርምር ስራዎች ላይ ያለው የሴቶች ተሳትፎም ዝቅተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተለይም የምርምር ውጤቶች የኢንዱስትሪና የማህበረሰብ አገልግሎትን በመደገፍ ረገድ ያለቸው ሀገራዊ ፋይዳ በሚጠበቀው ልክ ያለመሆኑ እና በመንግስት በጀት የሚካሄዱ ምርምሮች በጥናት የተደገፈ በጀት ያልተመደበላቸው መሆኑ እንዲሁም በተመራማሪዎች የሚቀርቡ የምርምር ፕሮፖዛሎችን የማጽደቅ ሂደቱ ረጅም ጊዜ የሚወስድ እንዲሁም ግልጽነት የጎደለው እና የጥናትና ምርምር መረጃ አያያዝ ስርዓቱም  ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ አለመደረጉ ተነስቷል፡፡

ማቲዎስ አንሰርሙ (ዶ/ር) የዩኒቨርስቲው የአስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት እና ምትኬ ሞላ (ዶ/ር) የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ኦዲቱ ጠቃሚና ትምህርት የተወሰደበት መሆኑን አመላክተው በተነሱት ጥያቄዎች ላይ በጋራ  ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በዩኒቨርስቲው ስር ካሉ ኮሌጆች ከሚመጡት የምርምር በጀት ፍላጎት ጥያቄዎች አንጻር የመንግስት በጀት በቂ ያለመሆኑና እሱንም ቢሆን በውድድር ለተመረጡ ምርምሮች ቅድሚያ እንደሚሰጥና በአብዛኛው በአለም አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች በሚገኙ የምርምር ፈንዶች የምርምር ወጪዎች እንደሚሸፈኑ ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የመንግስት ተቋም እንደመሆኑ የምርምር በጀት ስርዓቱ ከመንግስት የፋይናንስና የግዥ አሠራር ጋር የተያያዘ በመሆኑ የምርምር ፈንድ አስተዳደር ስርዓቱንና የምርምር ግብዓት ግዥዎችን ምቹነት በሚፈለገው ደረጃ ለመጠበቅ እንደማይቻል የጠቆሙት የዩኒቨርሲተው አመራሮች የምርምር ስራዎች መረጣ በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት በመስኩ ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ባላቸውና ተአማኒነት ባላቸው ምሁራን  የሚካሄድ በመሆኑ በግልጽነት ላይ ጥያቄ የሚነሳ አይደለም ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን  የምርምር ውጤቶች በሚፈለገው ደረጃ ለሀገር ልማትና ለህብረተሰቡ ተጨባጭ ፋይዳ ሊያመጡ የሚችሉበትን ሁኔታ በበለጠ መፍጠር የሚገባ መሆኑን በመጥቀስም እስካሁን በተሰሩ የምርምር ስራዎች አለም አቀፍ ተቀባይነት ባስገኙ የምርምር ውጤቶች አማካይነት ተጨባጭ ሀገራዊ ፋይዳ ያመጡ ስራዎች መሰራታቸውን እና ለዚህም ሀገሪቱ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ከሚመለከታቸው የተፋሰስ ሀገራት ጋር ባደረገቻቸው ውይይቶች በጂኦ ፊዚክስ የምርምር ውጤት ጉልህና ተጨባጭ ተጽዕኖ ያሳደሩ ሳይንሳዊ የመከራከሪያ ሀሳቦችን ማመንጨት መቻሉን በዋቢነት አንስተዋል፡፡

በ 16 በመቶ ላይ የሚገኘው የሴት ተመራማሪዎች ቁጥር በሚፈለገው ደረጃ ላይ ያለመድረሱን ያልሸሸጉት የዩኒቨርስቲው አመራሮች ተገቢ በሆነ የምርምር መስፈርት እና ውድድር ውስጥ ያለፉ ብቁ ሴት ተመራማሪዎችን ለማፍራት በእርስ በእርስ መረዳዳትና በስልጠና ላይ የተመሰረተ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የምርምር ውጤቶች ባስገኙት ፋይዳ ላይ መከናወን የሚገባው የክትትል ግምገማ በሚፈለገው ደረጃ ያልተካሄደና ከኦዲቱ በኋላ የግምገማ ስርዓቱን ለመተግበር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተው የአለም አቀፍ እና ሀገራዊ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ አሠራር ስምምነቶችን ጨምሮ ከሁሉም የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ቅንጅታዊ አሠራር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት ዩኒቨርሲቲው በኦዲት ግኝቶቹ መሰረት የምርምር ስርዓቱን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባው ገልጸው ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አንጻር አንጋፋና በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ እንደመሆኑ ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በአሠራሩ ሞዴል መሆን እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው ከአነስተኛ የምርምር መስኮች ይልቅ ደረጃውን ለሚመጥኑና ትላልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ለሚያስገኙ የምርምር ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት የሚገባው መሆኑን የጠቆሙት የመድረኩ ተሳታፊዎች ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር የበለጠ ማጠናከር የሚገባ መሆኑንና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመምከርና አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎችንና አሠራሮችን እንዲሻሻሉ በማድረግም ዕውቀት አመንጪና ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ውጤቶችን ማስገኘት እንዲሁም ለምርምር ፈንድ አስተዳደር ስርዓቱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ኦዲቱ በዩኒቨርሲቲው የምርምር ፈንድ አስተዳደር ስርዓት፣ የምርምር ሂደት እና የምርምር መረጃ ልውውጥ ስርዓት ውጤታማነት ላይ አቅጣጫ በማስቀመጥ የተካሄደ መሆኑን በምክረ ሀሳባቸው መግቢያ ላይ ያነሱት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው የምርምር ስራ ከሌሎች በተለየ ከስራው ባህሪ ጋር የሚጣጣም ምቹ ሁኔታ ሊኖው እንደሚገባ በመግለጽ በምርምር ግበአቶች ግዥ ስርዓት ላይ ያሉ ማነቆዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የማያሰሩ መመሪያዎችንና አሠራሮችን ማሻሻል ይገባል ብለዋል፡፡ ፡፡

ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች አካላት ጋር በጋራና በቅንጅት ሆኖ በመስራት ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል የጠቆሙት ም/ዋና ኦዲተሯ ምርምሮች የሀገሪቱንና የህብረተሰቡን ችግር ፈቺና አሳታፊ  እንዲሆኑ ለማድረግ የምርምር ዘርፎች በዚህ ዙሪያ ከሚሰታፉ የዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ ጋር እና ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ የተደረሰባቸው መሆን እንደሚገባቸው እና የምርምር ውጤቶች ያስገኙትን ፋይዳ በመገምገምና መለካት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የምርምር ርዕሰ ጉዳዮችን ድግግሞሽ በተመለከተም ትኩረት መስጠት እንደሚገባና በተደጋጋሚ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ የተደጋገሙ ምርምሮች የሚያመጡትን የሀብትና የጊዜ ብክነት መቀነስና ለአዳዲስ የምርምር ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት እንዲሁም የምርምር መረጃ አያያዝ ስርዓቱንም ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ  በሀገሪቱ የፖለተካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ የሀገሪቱ አንጋፋ ዩኒቨርስቲ መሆኑን በማውሳት የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ ዩኒቨርስቲው የኦዲት ግኝቶቹን መሰረት በማድረግ የሀገሪቱን ችግሮች በተጨባጭ የሚፈቱ  የምርምር ስራዎች ላይ ማተኮር አለበት ብለዋል፡፡

በምርምር ሂደቱ ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመስራት መፍታት እንደሚያስፈልግ እና ከሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎቻቸው በመቀነስ ለምርምር ሥራዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባም የተከበሩ አቶ ክርስቲያን አሳስበዋል፡፡

በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የኦዲት ግኝት ማስተካከያ ሪፖርትና የድርጊት መርሀ ግብሩን በማዘጋጀት አስከ ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲያቀርብ፣ ወደፊት የሚያደርጋቸው ምርምሮችም የሀገሪቱን የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ ማዕከል ያደረጉ፣ የግል ባለሀብቱን ጭምር በማቀናጀት ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ በማድረግ እንዲሁም የሴት ተመራማሪዎችን ተሳትፎ በማሳደግና በቅንጅታዊ አሠራርና በመረጃ አያያዝና ልውውጥ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን በመቅረፍ ረገድ የተሻለ ስራ በመስራት አጠቃላይ የምርምር ሂደቱን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *