News

የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማጎልበትና ስለመቻቻል ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ፈርጀ ብዙ ጥቅም እንዳለው ተገለጸ

የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማጎልበት እንዲሁም ስለመቻቻል ያላቸውን ግንዛቤና ክህሎት ማሳደግ  ግጭቶችን ለመከላከል፣ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ማህበራዊ ለውጥንና ፍትህን ለማስፈን ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ፡፡ በሴቶችና ወጣቶች ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሰራተኞች በሀገራችን ለ114ኛ በአለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ117ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን “የሰላም፣ የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶቻችን በማጎልበት የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ” በሚል ሀገራዊ መሪ ቃል ነሀሴ 12 ቀን 2009 ዓ.ም በመ/ቤቱ አዳራሽ አክብረዋል፡፡

የሴቶችና ወጣቶች ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ገዛኸኝ ሙሊሳ በወቅቱ ባደረጉት ገለጻ ወጣቱ በራሱ ጉዳዮች ላይ በተሳተፈ፣ ተጠቃሚ በሆነና የመቻቻል አቅሙ በተገነባ መጠን ሰላም፣ ዴሞክራሲና እድገት እንደሚረጋገጡ ገልጻው ወጣቱን ባሳተፈ መልኩ በነዚህ ጉዳዮች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ አቶ ገዛኸኝ በዓሉ የሚከበርበት ሀገራዊ መሪ ቃልም በዚሁ ምክንያት መመረጡን ተናግረዋል፡፡

አቶ ገዛኸኝ የዘላቂ ልማት አንደኛው ግብ ሰላማዊና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተ ማህበረሰብ መፍጠር ላይ እንደሚያተኩርና ስኬቱም በሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ገልጸው ለዚህ ስኬት ወጣቱን በሰላም ግንባታ ውስጥ ማሳተፍና የመሪነት ሚና እንዲጫወት ማብቃት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም የዘንድሮው የዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ “Youth Building Peace” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡

አቶ ገዛኸኝ ከወጣቶች ጉዳይ ጋር አያይዘው ስለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምንነትና አስፈላጊነት ሰፊ  ገለጻ አድርገዋል፡፡ በገለጻቸው ላይ ባለሙያው ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስለሚገኘው ፋይዳ ሲያስረዱ “ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ህዝቧ ውስጥ ሰላሳ በመቶ ያህል ድርሻ የሚይዘውን ወጣት ትውልድ በዚህ የአገልግሎት መስክ ላይ በማሰማራት ከምታገኘው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር ወጣቶች ከማህበረሰቡ ጠቃሚ ባህላዊ እሴቶችን እንዲቀስሙ እድል ለመፍጠር ያስችላቸዋል” ብለዋል፡፡

አቶ ገዛኸኝ አያይዘውም “እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገሮች ድህነትን ለመቅረፍ፣ ወደ ተሻለ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመሻገር፣ ማህበራዊ ለውጥን ለማምጣትና ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድን ለማፍራት ይችሉ ዘንድ ወጣቶች የራሳቸውን ሀሳብ፣ ጉልበት፣ እውቀትና ተነሳሽነት መጠቀም እንዲችሉ የበጎ ፈቃደኝነትን ጽንሰ ሀሳብን በራሳቸው መንገድ መቀበልና ማዳበር ይገባቸዋል” ብለዋል፡፡

የሴቶችና ወጣቶች ጉዳዮች ዳይሬክተር ወ/ሮ ሙሉ ጥሩነህ በበኩላቸው የመ/ቤቱ ወጣት ሰራተኞችም ሆኑ መላው ሰራተኛ እንደየአቅማቸው በየአካባቢያቸው ባሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ውስጥ በመሳተፍ ለህብረተሰቡና ለሀገሪቱ ሊያበረክቷቸው የሚችሏቸው በርካታ ጥቅሞች እንዳሉ ጠቅሰው ይህንን ጠቃሚ ተግባር ማከናወን እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

የመ/ቤቱ ሰራተኞች በመድረኩ በተነሱት ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን አስተያየቶችንም  ሰጥተዋል፡፡ ሰራተኞቹ በሰጡት አስተያየት በዋናነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርህ ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸው ነገር ግን ይህንን መገንዘብ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ መርሁን በተቋም ደረጃ ወደተግባር የሚቀይሩበት መንገድ ሊመቻች እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በሰራተኛው ዘንድ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመሳተፍ ተነሳሽነቱ ካለ በዳይሬክቶሬታቸው በኩል ይህንን ለማስተባበር ፈቃደኝነቱ እንዳለ ወ/ሮ ሙሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *