የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በፋይኔሺያልና ህጋዊነት ኦዲት ዘርፍ እየሰሩ ካሉ የመ/ቤቱ ኦዲተሮች ጋር መጋቢት 5፣ 2011 ዓ.ም ባደረገው የውይይት መድረክ የኦዲት ጥራት በሁሉም የኦዲት ደረጃዎች አስጠብቆ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
ለውይይት መነሻ የሚሆን በ2010/2011 በጀት ዓመት የጥራት ማረጋገጥን በተመለከተ የተከናወኑ ስራዎች በመ/ቤቱ የኦዲት ጥራት ዳይሬክተር አቶ አህመድኑር ሱዋሊህ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ፡፡
አቶ አህመድኑር ዓለም አቀፍ የኦዲት አሠራር ደረጃዎችን /Standards/ መሠረት በማድረግ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የሚሠሩ ኦዲቶች ከኦዲት ጥራት አንፃር ያለበትን ደረጃ ባቀረቡት ፅሑፍ አብራርተዋል፡፡
የቀረበውን የመነሻ ፅሑፍ ተከትሎ ተሳታፊዎች መድረኩ ለቀጣይ ሥራቸው ጠቀሚ ግብዓት ያገኙበት መሆኑን ገልፀው በሥራ አጋጣሚ በሚያጋጥሟቸው ችግሮች ዙሪያ ጥያቄዎችን አቅርበው በፅሑፉ አቅራቢ እና በተቋሙ የበላይ አመራሮች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ መድረኩ አንዱ ከሌላው ልምድ ለመውሰድ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀው በጥልቀት ምላሽ እና ማብራሪያ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ የየሥራ ክፍሉ ዳይሬክተሮችና ማናጀሮች በሥራቸው ያሉ ሙያተኞችን የኦዲት ጥራት ማረጋገጥ ስራዎች ዙሪያ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ግንዛቤያቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ መ/ቤቱ ዓለም አቀፍ የኦዲት ደረጃዎችን አስጠብቆ እንዲዘልቅ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቶባቸው እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልፀው ተቋሙ ከሚሰጠው የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በተጨማሪ ኦዲተሩ የተዘጋጁ ማኑዋሎችን በየጊዜው በማንበብ እራሱን ሊያበቃ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ አያያዘውም በመ/ቤቱ ምንም ዓይነት የኦዲት ጥራት ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ሊኖርበት እንደማይገባ ገልፀው ለዚህም መሳካት የቁጥጥር ሥራን በማጠናከር እና እያንዳንዱ ባለሙያውም የተሰጠውን ኃላፊነት የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ሊፈፅም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡