News

የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም የ2018 በጀት አመት የስራ መጀመሪያ ስብሰባውን አካሄደ

የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች የተበጀተላቸውን የህዝብ ሀብት በአግባቡ መጠቀማቸውን ለማረጋገጥ የኦዲት ባለድርሻ ተቋማት በባለቤትነትና በሃላፊነት ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ የሚያስችላቸውን የፎረሙን የ2017 እቅድ አፈጻጸም በመገምገም በ2018 ረቂቅ እቅድ ላይ ተወያይተው  ጥቅምት 11 ቀን 2018 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄዱት መድረክ አጽድቀዋል፡፡

የጋራ እቅዱን ያቀረቡት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) በ2017 በጀት አመት ከቀደሙት አመታት የተሻለ ቅንጅታዊ የክትትል፣ የቁጥጥርና የድጋፍ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው በ2018 በጀት አመት እቅድም ሊሰሩ የታሰቡ ቁልፍ ተግባራትን ለኦዲት ባለድርሻ አካላት የትብብር ፎረም አቅርበዋል::

የተከበሩ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር)  በመድረኩ እንደተናገሩት የፎረሙ ዓላማ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተሠሩ የኦዲት ሪፖርቶች መሰረት ተቋማት የተበጀተላቸውን የህዝብ ሀብት መንግስት ባስቀመጠው መመሪያና አቅጣጫ መሠረት ህጎችን ተከትለው ስራ ላይ ማዋለቸውን ለማረጋገጥ የክትትልና የቁጥጥር ስራው ላይ በጋራ በመስራት ተጠያቂነትን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል::

ሰብሳቢዋ አክለውም ባለፈው በጀት ዓመት በፌዴራል መ/ቤቶች ውስጥ በተገኙ የኦዲት ግኝቶች ላይ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እና በቋሚ ኮሚቴ አባላት በተሰጡ ምክረ ሃሳቦች መሰረት ተገቢው የእርምት እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታውሰው በዚህም በርካታ የህዝብ ሀብት ማስመለስ መቻሉንና ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ ጥረት እንደተደረገ አብራርተዋል::  ባለፈው በጀት ዓመት የተስተዋሉ ችግሮች ስጋቶችን በተመለከተም የመፍትሄ ሃሳቦችን አቅርበዋል::

በመድረኩ የተገኙት የኦዲት ባለድርሻ አካላት የሥራ ኃላፊዎች ባነሱት ሀሳብ ባለፈው በጀት አመት ፎረሙ በቅንጅት ውጤታማ የሆኑ ሥራዎችን መስራቱን አስታውሰው በ2018 በጀት አመትም የተሻለ ለመሥራት የክትትልና የቁጥጥር ሥራቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እና በአቅም ግንባታና በአሠራር ሊፈቱ የሚገቡ ጉዳዮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ፎረሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ በክትትልና ቁጥጥር ሥራው ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸው በቀደሙት አመታት በተሰሩት የኦዲት የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች ለመንግስት የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮች አስተዋጽኦ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡

ዋና ኦዲተሯ አክለውም በቀጣይ የኦዲት ሥራ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ሥራን ለይቶ ከመስራት፣ ከአቅም ግንባታ፣ ተጠያቂነት ከማረጋገጥ እና ሊሰበሰቡ የሚገቡ ተሰብሳቢ ሂሳቦች ላይ የተጠናከረ ሥራ ከመስራት አንጻር የተጠናከረ ጥረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

የኦዲት ባለድርሻ አካላትም ለእቅዱ ተጨማሪ ግብዓት የሚሆኑ ዝርዝር ሀሳቦችን በማንሳት የተወያዩ ሲሆን በመድረኩ የቀረበውን የ2018 የጋራ እቅድ በማፅደቅ ፎረሙ ተጠናቋል::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *