News

የኦዲት ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ክትትል ውጤት እያመጣ መሆኑ ተገለጸ

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡

ፎረሙ የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸሙን የገመገመ ሲሆን በበጀት ዓመቱ 26 ህዝባዊ ይፋዊ ስብሰባዎችን፤ 6 የከተማ እና 6 የገጠር የመስክ ጉብኝቶችን በማካሄድ ዕቅዱን 100 ፐርሰንት ማሳካቱ ተገልጿል፡፡

የኦዲት ባለድርሻ አካላቱ ያደረጉት የተቀናጀ የክትትልና የቁጥጥር ስራም ውጤት እያመጣ እና የሀብት ብክነት እንዲቀንስ እያደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በ2014 በጀት ዓመት ባካሄዳቸው ህዝባዊ ይፋዊ ስብሰባዎች፣ የመስክ ጉብኝቶችና ሌሎች የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች በተወሰነ ደረጃ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ማስቻሉን እና የህግ ማዕቀፎች እና የአሠራር ሥርዓቶች እንዲዘረጉ እንዲሁም በኦዲት ምንነት እና ፋይዳ ዙሪያ ግንዛቤ ማሳደግ የተቻለበት ዓመት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ፎረሙ የ2015 በጀት ዓመትንም የጋራ ዕቅድ ያዘጋጀ ሲሆን በቀረበው ዕቅድ ላይ የተለያዩ ተጨማሪ ሀሳቦችን ተነስተው የእቅዱ አካል እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡

በዚህ በጀት ዓመትም ቋሚ ኮሚቴው 14 የሂሳብና ህጋዊነት ኦዲቶች፣ 16 የክዋኔ ኦዲቶች ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማድረግ እንዲሁም ከኦዲት ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት 8 የገጠር እና 6 የከተማ የመስክ ሥራ ጉብኝቶች ለማከናወን መታቀዱ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የዓለም አቀፍ ተሞክሮን መነሻ በማድረግ የኦዲት ባድርሻ ፎረም አባል ሊሆኑ የሚገባቸው ተቋማት ዝርዝር እና በፎረሙ ስለሚኖራቸው ሚና ገለጻ አድርገዋል፡፡

የፎረሙ አባላትም በቋሚ ኮሚቴው የቀረበውን የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድና በዋና ኦዲተሯ በቀረበው የፎረሙ አባላት አስፈላጊነት ላይ ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በቀጣይ ይበልጥ ፎረሙ ተጠናክሮ የሀገር ሀብት ብክነት እንዲቀንስና ተጠያቂነት በየደረጃው እንዲረጋገጥ ጉልህ ሚና ሊጫወት ይገባል ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በመጨረሻ ባስተላለፉት መልዕክት በመንግሥት የሚመደበው በጀት ያለአግባብ እንዳይባክን እና ለታቀደላቸው ዓለማ በአግባቡ እንዲውሉ ለማስቻል ተቋማትን የሚመሩ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስቴር ዴኤታዎች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ቋሚ ኮሚቴው በሚያዘጋጀው የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም መገኘት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *