News

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የንብረት አያያዝና አጠቃቀም በአግባቡ እየተመራ እንዳልሆነ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የንብረት አስተዳደር በርካታ ግድፈቶች ያሉበት መሆኑ  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተዘጋጀ ይፋዊ ህዝባዊ መድረክ ላይ ተገለጸ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት  በአዲስ አበባ ከተማ በናሙና በተመረጡ የአገልግሎቱ የንብረት ማከማቻ ግምጃ ቤቶችና ዲስትሪክቶች ላይ  የክዋኔ ኦዲት አካሂዶ በርካታ የንብረት አያያዝና አጠቃቀም ክፍተቶች መታየታቸው ተጠቅሷል ፡፡

በንብረት ክፍል የሚሰሩ የተቋሙ ሠራተኞች የአሠራርና የአፈጻጸም  መመሪያ ያልደረሳቸው መሆኑና በአደረጃጀታቸውና በክህሎት እንዲሁም ተገቢውን ባለሙያ በተገቢው ቦታ መድቦ በማሰራት ሂደት ክፍተት መታየቱ ተመልክቷል፡፡

በንጉሱና በወታደራዊው መንግስት ዘመን አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ንብረቶችን ጨምሮ በርካታ ንብረቶች በአግባቡ ሳይወገዱ ወይም አገልግሎት ላይ ሳይውሉ ለረጅም ዓመታት መለየት በማይቻል መልኩ መሬት ላይ ተደራርበው፣ ተዝረክርከውና መጋዘን አጣበው መገኘታቸው እና  ሥርዓቱን የጠበቀ  ቆጠራ ያልተካሄደባቸው ቆጣሪዎችና ሌሎች ንብረቶች በኦዲቱ እንደተገኙ ተገልጿል፡፡

ግምታቸው ብር 7.5 ሚሊዮን የሚገመት በሺህ የሚቆጠሩ ንብረቶች ከ15 ዓመታት ባላይ በአንድ ማከማቻ መጋዘን ታሽገው መገኘታቸው እንዲሁም ከብር 59 ሚሊዮን በላይ ግምት ያላቸው ንብረቶችም በተለያዩ መጋዘኖች ለረጅም ጊዜ በጥቅም ላይ ሳይውሉና ሳይንቀሳቀሱ ተቀምጠው መገኘታቸውና ከ10 ዓመታት በላይ ወጪ ሳይደረጉና አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ የመኪና ዕቃዎች መገኘታቸውም ተጠቅሷል፡፡

ጠንካራ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት ባለመዘርጋቱ በከፍተኛ ዋጋ የተገዙ ትላልቅ ንብረቶች  መዘረፋቸው፣ ጥቂት የማይባሉትም በየቦታው ተበታትነው ለፀሀይና ለዝናብ ተጋልጠው ለከፍተኛ ብክነት መዳረጋቸው በይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባው ላይ የተነሳ ሲሆን የሚቀጣጠሉ፣ የሚፈነዱ፣ የሚተኑና መርዛማ የሆኑ ንብረቶችም ተለይተው ያለመቀመጣቸው ተመልክቷል::

በንብረት አመዘጋገብ፣ በተሽከርካሪ አጠቃቀም፣ እንክብካቤ፣ ቁጥጥርና ጥበቃ እንዲሁም የአጠቃቀም መመሪያ አተገባበር ላይ ክፍተት በመኖሩ ስርቆትን ጨምሮ  በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱ እና  አግባብነት ያለው ጥገና ተካሂዶ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ተሽከርካሪዎች ባሉበት  ተቋሙ ለከፍተኛ የመኪና ኪራይ  መዳረጉ ተጠቁሟል።  ንብረቶች በወጣላቸው ስፔስፊኬሽንና የጥራት ደረጃ ባለመገዛታቸውም በከፍተኛ ወጪ የተገዙ ትራንስፎርመሮችን ጨምሮ በርካታ ንብረቶች አገልግሎት ሳይሰጡ በየሜዳው ላይ ለጉዳት ተዳርገው መባከናቸው ተነስቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የስራ ኃላፊዎች የኦዲት ግኝቶቹን ለማስተካከል ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን በመጥቀስ ቋሚ ኮሚቴው በጥያቄ መልክ በዝርዝር ባቀረባቸው የኦዲት ግኝቶች ላይ ምላሽና ማብራሪያ  ሰጥተዋል፡፡

ክአገልገሎቱ ያልተማከለ አደረጃጀትን የመፍጠር፣ አሰራሮችን የማዘመንና፣ ዋና ዋና ያልሆኑ ስራዎችን በሶስተኛ ወገን የማሰራት የለውጥ ፒላሮችን መሰረት አድርጎ መሻሻል ለማሳየት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የጠቀሱት አመራሮቹ በኦዲቱ ወቅት የተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦችን ለመተግበር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ቀደም ሲል ከነበሩ መመሪያዎች በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት አዲስ የንብረት አስተዳደር መመሪያ መዘጋጀቱንና ለስራ ክፍሎች መድረሱን እንዲሁም የንብረት አስተዳደር ስርዓቱን ለማዘመን የሚያስችል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓት በመዘርጋት የአተገባበር ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በተቋሙ የሰው ኃይል በኩል የነበረውን ክፍተት ለማሻሻል የሰው ኃይል አደረጃጀት ስራዎች ተሰርተዋል፤ ሙያዊ ዕወቀት ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ስልጠናዎችም እየተሰጡ ናቸው ብለዋል፡፡

ተቋሙ ዓመታዊ የንብረት ቆጠራ እያደረገ መሆኑንና  ንብረቶችን ከብልሽትና ከምዝበራ ለመከላከልም አዳዲስ ዕቃ ግምጃ ቤቶችና ባዶ ቦታዎች  መዘጋጀታቸውንና  ንብረቶችን በዘመናዊ ሁኔታ ለማስተዳደርም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው ተሽከርካሪዎችን በግዥና በጥገና የማሟላት ስራ መከናወኑንና አገልግሎት የማይሰጡትን በማስወገድ ለተቋሙ ገቢ ማስገኘት መቻሉንም አብራርተዋል፡፡

 

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው ተቋሙ የኦዲት ግኝቶቹን መሰረት በማድረግ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ የማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ እያደረገ ያለው ጥረት በበጎ ጎኑ የሚታይ መሆኑን ገልጸው ኦዲቱ የአገልግሎቱ የንብረት አስተዳደር ምጣኔ ሀብታዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ መሆኑን ለማረጋገጥ በአዲስ አበባ ከተማ በተመረጡ ናሙና የንብረት ግምጃ ቤቶች፣ የተሽከርካሪ ጥገና ማዕከላትና ዲስትሪክቶች የተካሄደ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ከተቋሙ የሰፋና ትልቅ ሀገራዊ አገልግሎት አሰጣጥ አንጻር የሚገለገልባቸው ንብረቶች በከፍተኛ የሀገር ሀብትና የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው የሚመጡ እንደመሆናቸው የንብረት አስተዳደር  ስርዓቱና የሰው ኃይል አደረጃጀቱ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የጠቀሱት ም/ዋና ኦዲተሯ በኦዲቱ ከታዩት ሰፊና የገዘፉ የንብረት አያያዝና አጠቃቀም ችግሮች አንጻር ተቋሙ በአግባቡ እየተመራ ነው ለማለት እንደሚያስቸግር ጠቁመዋል፡፡ አክለውም በናሙና የተካሄደው ኦዲት በሀገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን ተቋም የንብረት አስተዳደር  የጠለቀ ችግር አመላካች በመሆኑ የችግሩን ስፋት የሚመጥን የሪፎርም ስራ መስራት እንደሚያስፈለግና  ለዚህም ቋሚ ኮሚቴውና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው አስተያየታቸውን ሰጠተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላትና በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው የኦዲት ግኝቱ ተቋሙ እንደ ሀገር ያሉበትን የንብረት አስተዳደር ስፋት ያላቸው ችግሮች አመላካች መሆኑን ጠቅሰው ከፍተኛ የመብራት ችግር ባለበት ሁኔታ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬና የሀገር ሀብት የተገዙ ንብረቶች ያለ አገልግሎት ለበርካታ ዓመታት ለብልሽትና ለምዝበራ ተጋልጠው መገኘታቸው አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የተቋሙ አሠራር የከፋ ሀገራዊ የህዝብ እሮሮ ያለበት መሆኑን ጨምረው የጠቀሱት የመድረኩ ተሳታፊዎች ተቋሙ የሙስናና ብልሹ አሠራር ተጋላጭ ተብለው በጥናት ከተለዩ ተቋማት የመጀመሪያው መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ ተቋሙ ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ ያለው ተነሳሽነት በሚገባው ልክ ያለመሆኑንና የአመራር ቸልተኝነት የሚታይበት መሆኑን በመጥቀስም በመድረኩ ላይ የተሰጡትን ጨምሮ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ አስተያየቶችን እንደ ግብአት በመውሰድ ችግሮቹን እንዲፈታ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ባስቀመጡበት የማጠቃለያ ንግግራቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገለግሎት ካለው የረጅም ዕድሜ አገለግሎት አሰጣጥ አንጻር አሠራሩ ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ መሆን ሲገባው በዚህ ዓይነት የገዘፈ የአሠራር ችግር ውስጥ መገኘቱ አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡ በርካታ የሀገሪቱ ዜጎች አስቸጋሪ በሆነ የመብራት እጦት ውስጥ ባሉበት ሁኔታ በከፍተኛ የሀገር ሀብት ተገዝተው በብልሹ አሠራር ምክንያት ያለ አገልግሎት እየባከኑ ያሉ ንብረቶች መኖራቸው አሳዛኝ መሆኑን በመገንዘብ  ተቋሙ  በተቆርቋሪነት ስሜት  እራሱን ፈትሾ አሠራሩን ማስተካከል እንደሚገባው ጠቅሰዋል፡፡ አክለውም የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች በላድርሻ አካላት በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተቋሙን ከታዩበት ችግሮች ሊያወጣ የሚችል የተጠናከረ የክትትልና ቁጥጥር ስራ ከመስራት ባሻገር ለተቋሙ ንብረት መባከን ተጠያቂ የሆኑ አካላትንና አሠራሮችን በጥናት በመለየት ህጋዊ ተጠያቂነትን  ሊያመጣ  የሚችል ስራ እንዲያከናውኑ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *