በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የ2012 በጀት ዓመት በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተዘጋጀ የህጋዊነት ኦዲት ሪፖርት ላይ ይፋዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡
በይፋዊ ስብሰባው የሂሳብ ኦዲት ሪፖርቱን መሠረት በማድረግ ቋሚ ኮሚቴው ከህግና ከመመሪያ ውጪ ለተፈጸሙ ግኝቶች ኢንስቲትየቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
በኦዲት ሪፖርቱ ኢንስቲትዩቱ የወለል ምንጣፍ እና መጋረጃ ከነሙሉ መገጣጠሚያው በብር 293,330.50 ወጪ ጨረታ ሳያካሂድ በቀጥታ ግዢ ፈጽሞ እንደተገኘ እና በወጪ ተመዝግበው ሪፖርት ላይ ከተካተቱ መካከል ብር 963,732.54 የሚያወጡ የወጪ ሰነዶች ለኦዲት ሥራ አለማቅረቡ ተገልጿል፡፡
ተሰብሳቢ ሂሳብን በተመለከተም ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት ድረስ የቆዩ በድምሩ ብር 173,157.84 ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ እንዲሁም ለባለጥቅሙ ያልተከፈለ ብር 63,059.30 ውዝፍ ተከፋይ ሂሳብ መኖሩ እና ለመደበኛ እና ለካፒታል በጀት ከተደለደለው በድምሩ ብር 8,437,565.88 ሥራ ላይ አለመዋሉ ተጠቁሟል፡፡
በንብረት አስተዳደር፣ በተሸከርካሪ ሥምሪት አያያዝና አጠቃቀም ጋር በተያያዘም በርካታ ክፍተቶች መታየታቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ የኢንስቲትዩቱ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳሬክተር ዶ/ር ታመነ ኃይሉ በሰጡት ምላሽ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝት አሠራራቸውን ለማሻሻል ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸው የድርጊት መርሃ ግብር በማዘጋጀት በኦዲት ግኝቶች ላይ በየደረጃው የእርምት እርምጃዎችን መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚህም ትክክለኛ የሒሳብ መደብ ካለመጠቀም፣ ያልተገባ ወጪ ከማውጣት እንዲሁም በተሰብሳቢ እና ተከፋይ ያሉ ችግሮች ከኦዲት ግኝቱ በኋላ የማስተካከያ እርምጃ እንደተወሰደባቸው እና በቀጣይም መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ በጥንቃቄ ለመሥራት እየተሠራ መሆኑን ዶ/ር ታመነ ገልጸዋል፡፡
ከንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘም ግኝቱ ትክክለኛ መሆኑን ገልጸው ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እያደረጉ እንዳሉ እና እቃዎቹን ሼድ አዘጋጅተው በዓይነት የማስቀመጥ ሥራዎችም እየሰሩ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የፌዋኦ መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ ኢንስቲትዩቱ የ2012 የሂሳብ ኦዲት ግኝት አሠራራቸውን ለማሻሻል ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ቢገልጹም አብዛኞቹ ግኝቶች አሁንም በ2013 በጀት ዓመት ቀጥለው ተገኝተዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ተቋሙ የወለል ምንጣፍ እና መጋረጃ ግዢ ጨረታ ሳያካሂድ ከመግዛቱም ባለፈ ግዢውን ፈጽሞ የተገኘው በበጀት ዓመቱ መዝጊያ ሰኔ 30፣ 2012 ዓ.ም መሆኑን እና በንብረት አያያዝ በኩልም በድርጊት መርሃ ግብራቸው ስለሰሩት ሥራ ያስቀመጡት ነገር አለመኖሩን ገልጸው በአጠቃላይ ኢንስቲትዩቱ የውስጥ አሠራሩን ሊፈትሽ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላትና የባለድርሻ አካላት ኢንስቲትዩቱ የኦዲት ግኝት ሪፖርትን መሠረት አድርጎ እየወሰደ ያለው የማስተካካያ እርምጃ መልካም ጅምር መሆኑን አንስተው አሁንም ግኝቶቹ ባህሪያቸውን ቀይረው ተጠናክረው መቀጠላቸው ተቋሙ በሚለው ልክ ለውጥ እያደረገ አለመሆኑን የሚገልጹ በመሆናቸው ተቋሙ የወጡ ህጎችና መመሪያዎችን በአግባቡ ተፈጻሚ ማደረግ አለበት ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው ተቋሙ ከዚህ ቀደም በርካታ ችግሮች የነበሩበት እንደሆነ አስታውሰው ችግሮቹን ለመቅረፍ እያደረገ ያለውን ጥረት እውቅና መስጠት ቢገባም ተቋሙ ለውስጥ ኦዲት ትኩረት በመስጠት መሥራት አለበት ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ከትናንሽ ጉዳዮች በመውጣት ለሀገር ጠቃሚ ለሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ትኩረት መስጠት እንዲሁም አጠቃላይ አሠራሩን መፈተሽ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ኢንስቲትዩቱ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እስከ ሚያዚያ 15 እንዲያቀርብ፣ በቀጣይ የ100 ቀናት እቅዱም የመደበኛው የሥራው አካል አድርጎ እንዲሠራ፣የሚወገዱ ንብረቶችንም በሚመለከት የአወጋገድ እቅድ እስከ ሚያዚያ 20 አዘጋጅቶ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው የገንዘብ ሚኒስቴር መ/ቤትም ለውስጥ ኦዲተሮች የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል እንዲያጠናክር አሳስበዋል፡፡