የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የንብረት አያያዝና አጠቃቀም አስመልክቶ ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት መሠረት የተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦች መተግበራቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል የመስክ ምልከታ ተካሄደ፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዕከላዊ ዕቃ ግምጃ ቤት እንዲሁም የተሸከርካሪ ጥገና እና ትራንስፖርት ቢሮ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ባለሙያዎች ተጎብኝተዋል።
የመስክ ምልከታው ዋና ዓላማ በኦዲቱ ወቅት የታዩ ግኝቶችን መሰረት በማድረግ የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ያሳያቸውን ለውጦች ለመመልከት ያለመ እንደሆነ ከጉብኙቱ ለመረዳት ተችሏል።
የእቃ ግምጃ ቤቶች በአግባቡ ያለማስተዳደር እና በቂ አለመሆን፣ በርካታ ንብረቶች በአግበቡ ያለማስወገድ፣ የንብረት አመዘጋገብ፣ የተሽከርካሪ አጠቃቀም መመሪያ አተገባበር ላይ ክፍተቶች መኖርና ስርቆትን ጨምሮ በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም ከ20 ዓመት በላይ በአንድ መጋዘን ንብረቶች ተከማችተው በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተካሄደ የክዋኔ ኦዲት መታየቱን ቋሚ ኮሚቴው አስታውሷል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ የተከበሩ አቶ ሽፈራው ተሊላ በማብራሪያቸው ኦዲት መደረግ ማለት እራስህን በመስታወት እንደማየት ነው ያሉ ሲሆን፤ ከኦዲት ግኝቱ በመነሳትም አሁን ላይ ዘርፈ-ብዙ ማስተካከያዎች በንብረት አያያዝና አጠቃቀም ላይ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
አክለውም ተቋማቸው በጣም ሰፊ እና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ቅንጫፍ መ/ቤቶች ያሉት በመሆኑ ስራቸውን ከባድ ቢያደርግባቸውም የኦዲት ግኙቱ እንደግብአት በመጠቀም የነበሩትን ችግሮች ለመቅረፍ መጠነ ሰፊ የማስተካከያ ሥራዎችን መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክዋኔ ኦዲት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ደረጀ ደበላ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የታየበትን የኦዲት ግኝት በፍጥነት በማረም አበራታች ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የአገልግሎት መ/ቤቱ የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ አሰራሩን ለማዘመን እና ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመተግበር እንዲሁም የደህንነት ካሜራዎች ሥራ ላይ በማዋል ስር ነቀል ለውጥ እያካሄደ እንደሚገኝ የገለጹጽ የተከበሩ አቶ ደረጀ ተቋሙ የማሻሻያ ሥራውን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሌሎች የቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው የአገልግሎት መ/ቤቱ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኦዲቱ ወቅት ያገኛቸውን ክፍተቶችና ጉድለቶች በተሰጡ አቅጣጫዎች መሰረት ለማስተካከል የሄደበትን ርቀት በጥንካሬ አንስተው ነገር ግን ሀገሪቱ እና ህብረተሰቡ ከተቋሙ ብዙ እንደሚጠብቅ ተገንዝቦ ተቋሙ ከዚህ በላይ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም የተከበሩ አቶ ደረጀ ደበላ በተለይ ለ20 ዓመታት ተዘግቶ የቆየውን የእቃ ግምጃ ቤት ተከፍቶ በዚህ ደረጃ ላይ መሻሻሉን አድንቀው በመጋዘኑ ግምታቸው ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የተከማቹ እቃዎች ቶሎ በጨረታ እንዲወገዱ እንዲሁም በመስክ ምልከታው የታዩ ለውጦች በሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችም እንዲደገሙ አሳስበዋል፡፡





