News

“የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ስናከብር በሕገ-መንግስቱ የተጣለብንን ኃላፊነት በላቀ ውጤታማነት ለመወጣት ቃል በመግባት ነው፡፡” ክቡር ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሠራተኞች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን፤ ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀንንና የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀንን አከበሩ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሠራተኞች 12ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን “በህገ መንግስታችን የደመቀ ህብረ ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን!” በሚል መሪ ቃል ህዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም በመ/ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች አከበሩ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በስነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የህገ-መንግስቱን ዓላማዎች በአግባቡ በመገንዘብ የህዳሴ ጉዟችን ዳር እንዲደርስ፣ ለሀገራችንና ለህዝቦቿ ዘላቂ እድገት እንዲፋጠን እንዲሁም ሰላም፣ ዴሞክራሲያዊ ስርአትና መልካም አስተዳደር እንዲረጋገጥ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የበኩሉን ሚና መጫወት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተር አያይዘውም  የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያለፈና የተዛባ ታሪካቸውን አርመው፣ በጎውን ታሪካቸውንና የአብሮነታቸውን ልምድ አበልፅገው በፍትህዊነት፣ በመከባበርና በመፈቃቀድ የጋራ የመልማትና የማደግ ፍላጎታቸውን በዴሞክራሲያዊ አግባብ ለማሣካት ቃል የገቡበት የቃል ኪዳን ሰነድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዕለቱ የመ/ቤቱ ሠራተኞች ከኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ቀን ጎን ለጎን የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀንንና ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀንን ያከበሩ ሲሆን ይህንን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት “በመሰረታዊነት የራሳችንን አመለካከት በማስተካከል ጤናማ ጾታዊ፣ ግለሰባዊና ማህበራዊ ባህሪያትንና ግንኙነቶችን በማዳበር፣ ህብረተሰባችንን በጉዳዮቹ ዙርያ በዘላቂነት በማስተማር እንዲሁም ለችግሩ ሰለባዎች ወገናዊ ፍቅርንና እንክብካቤን በማሳየት ችግሮቹን መከላከልም ሆነ ከተከሰቱ በኋላ የሚያደርሱትን አሉታዊ ውጤት መቀነስ ይቻላልም፤ ይገባልም ሲሉ ክቡር ዋና ኦዲተሩ አስገንዝበዋል፡፤

በበዓሉ አከባበር ወቅት በህገ-መንግስቱ፣ በመ/ቤቱ ተልዕኮ፣ በጸረ-ጾታዊ ጥቃትና በኤች.አይ.ቪ ኤድስ  ዙሪያ የጥያቄና መልስ ውድድር ተካሄዷል፡፡ በውድድሩም አራት ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን ለተሳታፊዎቹ  ከምክትል ዋና ኦዲተሮች እጅ የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል::

በየዓመቱ ህዳር 22 ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን በሀገራችን ለ30ኛ ጊዜ “አሁንም ትኩረት ለኤች አይ ቪ መከላከል!” በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን የሥራ አከባቢ ደህንነትና ጤንነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ታመነ ጌታሁን ቫይረሱ በሃገራችን ስላለው ስርጭት፣ በይበልጥ በቫይረሱ ተጠቂ ስለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በሽታው እያደረሰ ስላለው ተፅዕኖ፣ ስለምርመራ እና ህክምና እንዲሁም ሌሎች ወቅታዊ የቫይረሱ የስርጭት ሁኔታ ገለጻ አድረገዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም ከህዳር 16 -ታህሣስ 1 ቀን ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን (የነጭ ሪባን ቀን) በሀገራችን ለ12 ጊዜ “በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስቆም የወንዶችን አጋርነት ማጠናከር!” በሚል ሀገራዊ መሪ ቃል ተከብሯል፡፡ በወቅቱ የሥርዓተ ጾታ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ገዛኸኝ ሙሊሳ ጾን መሰረት አድርገው ስለሚፈፀሙ ጥቃቶች፣  በሴቶች ላይ ስለሚፈፀሙ የጥቃት ዓይነቶችና ስለሚያስከትሉት ውጤት፣ ስለህግ ማዕቀፎችና ሰነዶች እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በኤች.አይ.ቪ ኤድስና በጾታዊ ጥቃት ላይ በቀረቡት ገለፃዎችና ጥያቄዎች ላይ ክቡር ዋና ኦዲተሩ በሰጡት ማጠቃለያ በተለይም በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን ለማስቆም ህጎች እንዲሻሻሉ ከማድረግ ባለፈ የማህበረሰብ አስተሳሰብ ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባና ጥቃቱ ደርሶ ሲገኝም ጥቃት አድራሾቹ በህግ ፊት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡ ከኤች.አይ.ቪ ኤድስና ስርጭት ጋር በተያያዘም የመ/ቤታችን ሰራተኞች በመስክ ሥራ ላይ የሚሰሩ እንደመሆናቸው ለበሽታው እንዳይጋለጡ የግንዛቤ ማስጨበጡ ሥራ ተጠናክሮ በትኩረት መሠራት እንዳለበትና እና ለበሽታው የተጋለጡ ሠራተኞችም ካሉ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *