News

የአገልግሎት መ/ቤቱ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓቱን መሻሻል እንዳለበት ተጠቆመ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓቱን መሻሻል እንዳለበት አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠው የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የ2012 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ሰኔ 22/2014 ዓ.ም በተካሄደው ይፋዊ የህዝብ ውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

በአገልግሎት መ/ቤቱ በ2012 በጀት ዓመት ለሆቴል መስተንግዶ በግልጽ ጨረታ መገዛት ሲገባቸው በዋጋ ማወዳደሪያ ግዢ ተፈጽሞ መገኘቱ፣ የዋጋ ማወዳደሪያ ሳይሰበሰብ የሆቴልና የትራንስፖርት አገልግሎት ግዢ መካሄዱ እና በግልጽ ጨረታ ማስታወቂያ ሳይወጣ በውስን ጨረታ ግዢ ተፈጽሞ መገኘቱ ተመላክቷል፡፡

የመስክ ሥራ ደርሶ መልስ ለሰሩ ሠራተኞች በብልጫ ውሎ አበል መከፈሉ፣ የውጭ ሀገር አበል ለተጠቀሙበት ማስረጃው ሳይቀርብ ክፍያ መፈጸሙ፣ በግዢ እቅድ ያልተካተቱ የለቀማ ግዢዎች መፈጸማቸው እና ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብን በተመለከተም በወቅቱ ያልተሰበሰቡና ያልተከፈሉ ሂሳቦች መገኘታቸው ተገልጿል፡፡

ከበጀት አጠቃቀም ጋር በተያያዘም በበጀት ዓመቱ በመመሪያ ከተፈቀደው በላይ ሥራ ላይ ያልዋለ በጀት መገኘቱ፣ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓት /IFMIS/ ወይም አይቢክስ /IBEX/ የማይጠቀም ቅ/ጽ/ቤት መገኘቱ እና በንብረት አያያዝና በተሸከርካሪ አስተዳደር በኩልም በዋናው መ/ቤትም ሆነ በተለያዩ ቅ/ጽ/ቤቶች በርካታ ያልተወገዱ ንብረቶችና ተሸከርካሪዎች መገኘታቸውን ቋሚ ኮሚቴው ገልጾ የተቋሙ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይግዙ እና ሌሎች የተቋሙ አመራሮች በቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ የድርጊት መርሃ ግብር ከማዘጋጀት ባለፈ ክትትል በማድረግ የእርምት እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የተቋሙ አመራሮች በማብራሪያቸው አንዳንድ ጊዜ ከእቅዳቸው ውጪ በመንግስት ፍላጎት የሚጠየቁ ሥራዎችን በፍጥነት ለማከናወን የተለያዩ ግዢዎችን ከመመሪያ ውጪ ለመፈጸም መገደዳቸውን፣ በአንዳንድ ቅ/ጽ/ቤቶች ከሙያተኛ አቅም ማነስ ጋር የተያያዙ ክፍተቶች እንደነበሩ አስታውሰው በአሁኑ ወቅት በተለያየ ደረጃ ከህግ ውጪ ይፈጸሙ የነበሩ ግዢዎችና ክፍያዎች እንዲታረሙ መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

ከበጀት አጠቃቀም አንጻርም በወቅቱ በእቅድ የተያዘው ሥራ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ በጀቱን ለመጠቀም አዳጋች ሁኔታ ማጋጠሙን እና ከንብረት አያያዝና ተሸከርካሪ አስተዳደር ጋር በተያያዘም በርካታ ሥራዎች ቢሰሩም አሁንም የቀሩትን ለማስወገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ እንደሚገኙ አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ አገልግሎቱ የሂሳብ አመዘጋገባቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ባዘጋጀው የአይቢኤክስ ወይም ኢፍሚስ ሥርዓት ሊሆን እንደሚገባ፣ በተሰብሳቢ ሂሳብ መሻሻል ቢኖርም አሁንም የሚቀረው ከፍተኛ ያልተሰበሰበ ሂሳብ ሊሰበሰብ እንደሚገባው እና በርካታ ያልተወገዱ ንብረቶች በመ/ቤቱ የሚገኙ በመሆኑ በዚህም በኩል ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የውስጥ ቁጥጥሩ እና የገንዘብ አያያዝ ላይም አገልግሎት መ/ቤቱ አተኩሮ ሊሠራ እንደሚገባ ያወሱት ዋና ኦዲተሯ ከዚህ ቀደም መመሪያን በተላለፉ የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይም ተጠያቂነት የማረጋገጥ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት አገልግሎት መ/ቤቱ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓቱ ወቅቱ በሚጠይቀው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መሠረት ሊሆን እንደሚገባና ከመመሪያ ውጪ የሚፈጸሙ ግዢዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ጠቁመዋል፡፡

አክለውም ሥራዎችን በእቅድ በመምራት ማስፈጸም እንደሚያስፈልግ፣ በህግ የተያዙ ጉዳዮችን ተከታትሎ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ እና በንብረትና ተሸከርካሪ አያያዝ ረገድም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የቋሚው ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው ተቋሙ የኦዲት ግኝቱን መነሻ በማድረግ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየ ያለውን አሰራሩን የማሻሻል ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው የኦዲት ግኝቶቹ ሰፊ በመሆናቸው ተቋሙ ግኝቶቹን ለማስተካከል ትኩረት መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የአገልግሎት መ/ቤቱ እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም የኦዲት ማሻሻያ መርሃ ግብር እንዲያቀርብ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር በዘረጋው የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓት መሠረት ተገቢውን አሠራር በሁሉም ቅ/ጽ/ቤ/ቶች እንዲተገብር፣ የኦዲት ግኝቱን የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድ አካል አድርጎ እንዲንቀሳቀስ፣ በመ/ቤቱ ችግር የፈጠሩ የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ካሉም አስተዳደራዊና የወንጀል ተጠያቂነት አሠራርን እንዲያረጋግጥ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን አሳስበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴርም በበኩሉ መወሰድ ያለባቸው የተጠያቂነት እርምጃዎች ካሉ በ2 ወር ጊዜ ውስጥ እርምጃ ወስዶ ሪፖርት እንዲያደርግ እና የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎትም ከተቋሙ ጋር በመነጋገር በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ያልተወገዱ ንብረቶች እንዲወገዱ በማድረግ ሪፖርት እንዲያቀርብ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *