News

የነጠላ ኦዲት አዋጅና መመሪያን በሁሉም ክልሎችና የፌዴራል ከተማ አስተዳደሮች ለመተግበር የሚያስችል ስልጠና ተሰጠ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በሁሉም የክልልና የፌዴራል ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የፌዴራሉ መንግስት ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች የሚያደርገው ድጋፍና ድጎማ ኦዲትን /የነጠላ ኦዲትን/ ለመተግበር የሚያስችል የአንድ ቀን ሥልጠና በቢሾፍቱ ከተማ የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት አካሄደ።

ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ቢሮዎች እንዲሁም የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የተውጣጡ ከ 90 በላይ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 94 ንዑስ አንቀጽ 2፣ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1146/2011 መሰረት መ/ቤቱ ከፌዴራል መንግስት ለክልል መንግስታት የሚሰጠውን ድጋፍና ድጎማ አፈጻጸም ኦዲት የማድረግ ስልጣን እንዳለው ተደንግጓል፡፡

የክልል መንግስታት ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችም ይህንኑ ኦዲት የሚያደርጉበት ሁኔታ የነበረ በመሆኑ በአሠራር ላይ የተፈጠረውን የኦዲት ድግግሞሽ ለማስወገድ ሲባል የነጠላ ኦዲት አዋጅ 1251/2013 እና የአዋጁ ማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር 2/2014 እንዲወጡ መደረጉ ይታወሳል፡፡

በዚሁ መሰረት የነጠላ ኦዲት አዋጅ ትግበራ በ2015 በጀት አመት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በኦሮሚያ፣ በሲዳማ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

የአሁኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክም ከ2016 በጀት አመት ጀምሮ ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የነጠላ ኦዲት አሠራርን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲችሉ በ22ኛው የዋና ኦዲተሮችና የባለድርሻ አካላት የምክክር ጉባኤ በተስማሙት መሰረት ኦዲቱን ወጥ በሆነ መንገድ ለመተግበር ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

በግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤና ምክትል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ ከሰልጠናው ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በሰጡት ሀሳብ በስልጠናው ከመሳተፍ ባለፈ የነጠላ ኦዲት ትግበራ ይበልጥ የተሳካ እንዲሆን ገንቢ ሀሳቦችን በማቅረብ እና በንቃት በመሳተፍ ሥልጠናውን የተከታተሉትን ተሳታፊዎች አመስግነው በቀጣይም ትግበራው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የተጀመሩ ቅንጅታዊ አሠራሮችና ድጋፎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም የነጠላ ኦዲት አዋጅ የክልሎችን አቅም ለመገንባትና ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር እንዲሁም የኦዲት ሥራ ድግግሞሽን፣ የሥራ ጫናንና አላስፈላጊ የጊዜ ብክነትን የሚያስቀር መሆኑን ዋና ኦዲተሯ ጠቁመው በትግበራ ሂደት የሚያጋጥሙ ተሞክሮዎችን መሠረት በማድረግና ከሂደቱ ትምህርት በመውሰድ አፈጻጸሙን ለማሻሻል ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው የክልልና የፌዴራል ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች፣ የፋይናንስ ቢሮዎችና የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የነጠላ ኦዲት አዋጅን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ሚና አብራርተው ኦዲቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የሚደረጉ የአቅም ግንበታ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

የነጠላ ኦዲቱ ትግበራ ዓለማ የድጋፍና ድጎማ ሂሳብን ወጥ የሆነ ሥርዓት እንዲከተል ለማድረግ፣ የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓትን ለመዘርጋት፣ የፋይናንስ አስተዳደሩን ለማጠናከር፣ በኦዲት ተደራጊው ላይ የሚደረገውን የኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረት፣ ውጤታማና የታለመለትን ዓላማ የሚያሳካ የኦዲት ሀብት አጠቃቀም እንዲኖር ለማስቻል፣ በኦዲት ምክንያት ሊከሰት ይችል የነበረውን ጫና ለመቀነስ እና ለጋሾች በአዋጁ መሠረት ለሚደረግ የኦዲት ውጤት እምነት እንዲጥሉና እንዲጠቀሙ ለማስቻል መሆኑን በሥልጠናው ወቅት ተገልጿል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *