የሀገሪቱን ገቢ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለውን የአበባ እርሻ በማልማት ሂደት ለግብአቶች አያያዝና አጠቃቀም እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2014/2015 ኦዲት ዓመት በግብርና ሚኒስቴር የአበባ እርሻ ምርታማነትና የአካባቢ አያያዝ ሥርዓት ውጤታማነትን መሰረት አድርጎ ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት የታዩ ግኝቶችን አስመልክቶ ህዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ በርካታ የኦዲት ግኝቶች የተነሱ ሲሆን የአበባ እርሻን በማልማት ሂደት ከህግ ማዕቀፍ፣ ከመረጃ ልውውጥ፣ ከቅንጅታዊ አሠራር፣ ከግብይት፣ ከመሬት ልየታና አጠቃቀም፣ ከሠራተኞች አያያዝና መብት፣ ኬሚካሎችን ጨምሮ ከግብአቶችና ተረፈ ምርቶች አያያዝ፣ አጠቃቀምና አወጋገድ አንጻር ክፍተቶች መኖራቸው እንዲሁም ከልማቱ በተጓዳኝ እርሻዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ከተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ በሰዎች፣ በእንሰሳት፣ በአፈርና በውኃ ላይ ለሚደርሱ የጎንዮሽ ጉዳቶች ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠ በኦዲቱ ወቅት መታየቱ ተገልጿል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር መለስ መኮንንን (ዶ.ር ) ጨምሮ በመድረኩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በተነሱት የኦዲት ግኝቶች ላይ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የአበባ እርሻ ልማት ከቡና በመቀጠል ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ ከመሆኑ አንጻር ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገውና ለዚህም ከኦዲቱ በኋላ የተሰጡ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ አስተያየቶችን መሰረት በማድረግ ችግሮችን ቀርፎ ልማቱን ለማጠናከርና ከእርሻ ግብአቶች እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ ያሉትን የጎንዮሽ ጉዳቶች ለመቀነስ ጥረቶች እየተደረጉ መሆንን ጠቅሰዋል፡፡
ለእርሻ ልማቱ የሚውሉ ኬሚካሎችና ሌሎች ግብአቶችን ከውጭ በማስገባት ሂደት የአለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ስታንዳርዶችን የጠበቁ የቁጥጥርና የክትትል ስራዎች እንደሚሰሩና ከህግ ማዕቀፍና አሠራር ጋር የነበሩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አክለው የገለጹት የስራ ኃላፊዎቹ የኦዲት ግኝቶቹ ባሳዩት መሰረት ከግብአቶች አያያዝ፣ አጠቃቀምና አወጋገድ እንዲሁም ሰዎችንና እንስሳትን ጨምሮ አፈርንና ውኃን እንዲሁም የአካባቢ ምህዳርን ከእርሻ ግብአቶችና ከተረፈ ምርቶች የጎንዮሽ ጉዳቶች ለመከላከል የሚገባውን ያህል ስራ እንዳልተሰራና ችግሮቹን ለማስወገድ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ አባላቱና የመድረኩ ተሳታፊ የሆኑ ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየትም አብዛኞቹ የኦዲት ግኝቶች አስገዳጅ የሆኑ በየደረጃው ያሉ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቶና በሚመለከታቸው አካላት አጸድቆ በመተግበርና ከባለድርሻዎች ጋር ሊኖር የሚገባውን ቅንጅታዊ አሠራር በማጠናከር የሚቀረፉ መሆናቸውን ጠቅሰው የእርሻ ልማቱ አጠቃላይ ግብ የህዝብን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር መታየት አለበት ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከኦዲቱ በኋላ የተሰጡ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ አስተያየቶችን በመቀበልና የተሰሩና ያልተሰሩ ተግባራትን በመለየት ማቅረቡ ግኝቶቹን ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ጥረት አመላካች መሆኑን ጠቅሰው ኬሚካልን ጨምሮ ለእርሻ ልማቱ ከውጭ የሚገቡ ግብአቶችን መጠን ከልማት እርሻዎቹ ተገቢ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ በማድረግና የግብአቶቹን አላስፈላጊ ክምችት በማስወገድ በአካባቢ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን የጎንዮሽ ጉዳች መቀነስ ይገባል ብለዋል፡፡
ከህግ ማዕቀፍ፣ ከመሬት ልየታና አጠቃቀም፣ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ኬሚካሎችና ተረፈ ምርቶች ከማስወገድ፣ ከውኃና ከአፈር እንዲሁም የአካባቢ ምህዳር ብክለትን እና በሰውና በእንሰሳት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ከመቀነስ፣ ከሠራተኞች መብትና ጤንነት፣ ከመረጃ ልውውጥና ቅንጅታዊ አሠራር ጋር የተያያዙና ሌሎች በኦዲቱ የታዩ ክፍተቶችን መቅረፍ እንደሚገባ አክለው የገለጹት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ግብርና ሚኒስቴር ከኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ አበባውን አምርቶ ለሽያጭ እስከ ማቅረብ ድረስ ባለው ሂደት ተሳታፊ ከሆኑ የተለያዩ ተቋማት ጋር ያለውን የአሠራር ቅንጅት በማጠናከር ለውጤታማነቱ መስራት አለበት ብለዋል፡፡
የአበባ እርሻ ልማት ለሀገሪቱ ከሚያስገኘው ከፍተኛ ገቢ አንጻር ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑንና ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያገናኝ ስራ የሚከናወንበት ዘርፍ እንደመሆኑ ትኩረት የሚሻ ቅንጅታዊ አሠራር የሚያስፈልገው መሆኑን በማጠቃለያ አስተያየታቸው የጠቀሱት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው ተገቢ የህግ ማዕቀፍና የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ ችግሮችን መቅረፍ የሚገባ መሆኑን አሳስበዋል፡፡
አክለውም በመረጃ አያያያዝና ቅብብሎሽ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሠራተኞች አያያዝና መብት እና በመሬት አጠቃቀም ላይ ትኩረት ያለው ስራ እንዲሰራና አስከ ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ የተሻሻለ የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ እንዲቀርብና በአበባ እርሻ ልማት ስም ተይዘው ለሚፈለገው ዓላማ በጥቅም ላይ ያልዋሉ መሬቶች በጥቅም ላይ እንዲውሉና ለአፈጻጸሙም ሪፖርት እንዲቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡