News

የአሠልጣኞች ሥልጠና ላጠናቀቁ ሠራተኞች ሰርተፍኬት ተሰጠ

በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ሲሠጥ የነበረውን የአሰልጣኞች ስልጠና በውጤታማነት ላጠናቀቁ 30 ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ታህሣስ 05፣ 2010 ዓ.ም ተሰጠ፡፡

በሰርተፍኬት አሰጣጥ ስነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የታክስ ኦዲት ትራንስፓረንሲ (TAUT) ኮምፖነንት ሊደር ሚስተር ኮንሌዝ ሔሮን በእንግሊዝ መንግስት ቻርተርድ ኢንስቲትዩት ኦፍ ፐብሊክ ፋይናንስ ኤንድ አካውንታንሲ (CIPFA) ድጋፍ ሲሰጥ የነበረውን የአሰልጣኞች ስልጠና በውጤታማነት ላጠናቀቁ 30 የተቋሙ ሠራተኞች የእንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ሚስተር ኮንሌዝ መልዕክታቸውን ባስተላለፉበት ወቅት ሥልጠናውም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በማቋቋም ላይ ለሚገኘው የስልጠና ተቋም የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ፍላጎት ታሳቢ ያደረገና በፋይናሺያል፤ ክዋኔ እና አይቲ (IT) ኦዲት ላይ አቅም የሚሰጥ እንደሆነ፤ በተለያዩ የአመራርነት ክህሎቶች ላይ ሥልጠና እንደሚሰጥ፤ የተቋሙንም የኦዲት ሙያተኞች አቅም በማጎልበት የኦዲት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው፤ የክልል ዋና ኦዲተር ቢሮዎችንም በአቅም ግንባታ ለመደገፍ የሚያስችለው አቅም እንደሚፈጥርና በቀጣይም አሁን በአማካሪ ድርጅት በኩል የሚሰጠውን ስልጠና ሙሉ በሙሉ በማስቀረት በተቋሙ ሠራተኞች መስጠት የሚያስችል እንደሆነ ሚስተር ኮንሌዝ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬቱን  ሥልጠናውን ላጠናቀቁ ሠራተኞች ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ለአንድ ተቋም ተልዕኮ መሳካት አንደኛው ወሳኝ ጉዳይ ብቁ የሰው ኃይል መኖሩ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ለተቋሙ የሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ያስችለው ዘንድ ብሎም የኦዲት ሥራን ይበልጥ ጥራት ባለው ሁኔታ ለመስራት ተቋሙ የራሱን አሰልጣኞች ማፍራቱ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሠረት አሰልጣኞቹ በቀጣይ ሰልጣኞችን በሚፈለገው ሁኔታ በማብቃት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ገልፀው በትጋና በታማኝነት የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ከአደራ ጭምር መልዕታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሥልጠናው በአራት ዙር ከግንቦት 28 እስከ ጳጉሜን 3፣ 2009 ዓ.ም ድረስ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን በዚህ ሥልጠና የተመረጡት ሠልጣኞች በቀጣይ በተቋሙ ለሚሰጡ ስልጠናዎች በአሰልጣኝት የሚሳተፉ ይሆናሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *