News

የነጠላ ኦዲት አዋጅና መመሪያን ለመተግበር የሚያስችል 2ኛ ዙር የግንዘቤ ማስጨበጫ ውይይት ተካሄደ

የኦዲት ስራ ድግግሞሽን፣ የስራ ጫናንና አላስፈላጊ የጊዜ ብክነትን ለማስወገድ እንዲቻል በተዘጋጀው የነጠላ ኦዲት አዋጅ እና የአዋጅ ማስፈጸሚያ መመሪያ ትግበራ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ 2ኛ ዙር ውይይት ተካሄደ፡፡

ህዳር 2 ቀን 2015 ዓ.ም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የስልጠና ማዕከል በተካሄደው የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ከመ/ቤቱ የኦዲት ጥራት ዳይሬክቶሬትና የድጋፍና ድጎማ ኦዲት ዳይሬክቶሬት እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የተውጣጡ 9 የኦዲት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1146/2011 መሰረት መ/ቤቱ ከፌዴራል መንግስት ለክልል መንግስታት የሚሰጠውን ድጋፍና ድጎማ አፈጻጸም ኦዲት የማድረግ ስልጣን ያለው በመሆኑና የክልል መንግስታት ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችም ይህንኑ ኦዲት የሚያደርጉበት ሁኔታ የነበረ በመሆኑ በአሠራር ላይ የተፈጠረውን የኦዲት ድግግሞሽ ለማስወገድ ሲባል የነጠላ ኦዲት አዋጅ 1251/2013 እና የአዋጁ ማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር 2/2014 እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

ይህንኑ ተከትሎ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የነጠላ ኦዲት አዋጁንና ማስፈጸሚያ መመሪያውን ለመተግበር የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶችን ከተወሰኑ የክልልና የከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ጋር ተወያይቷል፡፡

በዚህም መሠረት ባለፈው ከሌሎች የተወሰኑ የክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ጋር የመጀመሪያው ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ይህ 2ኛ ዙር መድረክ ያለፈው የመጀመሪያ ዙር ውይይት ቀጣይ መርሀ ግብር መሆኑ ታውቋል፡፡

በግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቱ ላይ በመገኘት በነጠላ ኦዲት አዋጁና መመሪያው አተገባበር ላይ ገለጻ ያደረጉት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ሽመልስ ሲሆኑ የነጠላ ኦዲት ምንነትንና የተለያዩ ሀገራትን የነጠላ ኦዲት አተገባበር ተሞክሮ በማንሳት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በሁለት ዙር በተካሄዱት የነጠላ ኦዲት አዋጅና ማስፈጸሚያ መመሪያ አተገባበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይቶች በመሳተፍ ወደ ትግበራ የገቡ የክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችን አፈጻጸም በመገምገም በቀጣይ የሌሎች ክልል መንግስታት ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችን ወደ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችል ተመሳሳይ መድረክ በመ/ቤቱ በኩል ሊዘጋጅ እንደሚችል ታውቋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *