የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓት ትግበራን (IFMIS) እውን ለማድረግ ስለመረጃ አስተዳደር ሥርዓቱ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሥልጠና ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በመጡ ባለሙያዎች ለተቋሙ የፋይናንስ ሠራተኞችና ለሚመለከታው ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች መጋቢት 12፣ 2009 ዓ.ም ተሰጠ፡፡
ስልጠናውን የከፈቱት የፌዴራል ዋና ኦዲተሩ ልዩ ረዳት አቶ ሻሾ መኮንን የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓት (IFMIS) እስከአሁን አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን ነባሩን የፋይናንስ የመረጃ አያያዝ በዘመናዊ መንገድ ለመለወጥ ያስችል ዘንድ የሚተገበር መሆኑን ገልጸው ስርዐቱን በሁሉም የመንግስት መ/ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ የገንዘብና
ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መ/ቤት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ስልጠናም የዚሁ አካል መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ሰልጣኝ በትኩረት እንዲከታተልና ለተፈፃሚነቱም የራሱን ጉልህ ሚና እንዲጫወት አሳስበዋል፡፡
ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አይቤክስ/ኢፍሚስ ፕሮጀክት ፅ/ቤት በመገኘት ስለኢፍሚስ (IFMIS) ፅንሰ-ሃሳብና አተገባበር ስልጠና የሰጡት አቶ ቅባቱ ሰይፉ ስለኢፍሚስን ምንነት፣ በኢትዮጵያ ስላለው አተገባበር፣ ስለ ሪፖርት አፃፃፍ፣ ከደህንነት ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች፣ ሥርዓቱ ሲተገበር ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ችግሮች፣ ስለ ሰርአቱ አተገባበር ስትራቴጂ እና ስለቀጣይ የአፈፃፀም ተግባራት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ትግበራውን ለመጀመር ያስችል ዘንድ አስፈላጊ ግብዓቶች ተማልተው ሊገኙ እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትም ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ግንቦት መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ እንደታሰበ አቶ ቅባቱ ገልፀዋል፡፡
የአቶ ቅባቱን ገለፃ ተከትሎ ሠራተኞች ተጨማሪ ማብራሪያ በፈለጉባቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን ኢፍሚስ (IFMIS) በሁሉም የመንግስት መ/ቤቶች ተግባራዊ ሲደረግ የተቋማቱን የፋይናንስ አስተዳደር የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በምን አግባብ ኦዲት እንደሚያደርግ፣ የኢፍሚስ (IFMIS) የመረጃ አያያዝ ከመረጃ ነፃነት አንፃርና ከደህንነት ጋር በተያያዘ ምን ያህል አስተማማኝ ስለመሆኑ እና ከሰራተኞች መልቀቅና አለመሟላት ጋር በተያያዘ በሥራው ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖና ማብራሪያ እንዲሠጣቸው ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡
አሰልጣኙም ምላሻቸው የኢፍሚስ ቴክኖሎጂ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ሥራ ላይ ችግር እንደማይፈጥርና ይህን ሊያስተናግድ የሚችልበት አሠራር እንዳለው፤ የመረጃ ደህንነቱም አስተማማኝና ዘመኑ የሚጠቀመውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚሠራ በመሆኑ ስጋት ሊፈጠር እንደማይገባ እንዲሁም በየተቋማቱ ስልጠናውን የወሰዱ ሰራተኞች መልቀቅ እና በአዲስ ሰራተኞች መተካት ስራውን በአግባቡ በማከናወን ችግር እንደሚፈጠርና በተቻለ ፍጥነት አዲስ የገቡትን ሠራተኞች በማሰልጠን ለሥራ ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡፡
በመጨረሻም ስራውን ለመምራት የተቀጠረው የቴክኖብሬን አማካሪ ድርጅት ኃላፊ ኃላፊ አቶ ኃይለልዑል ግርማ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር በዚህ የኢፍሚስ (IFMIS) ትግበራ የመክፈቻ መድረክ ላይ ብዛት ያለው ሠራተኛ ተገኝቶ ሥልጠናውን መከታተሉ መ/ቤቱ ምን ያህል ለሥርዓቱ ትኩረት እንደሰጠ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ባስተላለፉት መልዕክት ይህ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓት በአግባቡ እውን ለማድረግ ቁልፉ ጉዳይ አሰራሩን ሙሉ በሙሉ መተግበር ሲቻል በመሆኑ መ/ቤቱም ሆነ ሠራተኛው ከፍተኛ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡