የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደርን በተመለከተ ተሻሽለው የወጡ አዋጅና መመሪያዎችን ለማስተዋወቅ ሲሰጥ የነበረዉ ሁለተኛ ዙር ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡
ስልጠናው ከሐምሌ 21 እስከ ነሐሴ 02 /2017 ዓ.ም ከፌዴራል ግዥና ንብረት ባለስልጣን በመጡ አሰልጣኝ ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን ከመ/ቤቱ የኦዲት የስራ ኃላፊዎችና ኦዲተሮች እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ የድጋፍ ዘርፍ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በጥቅሉ 193 የሚሆኑ ሰልጣኖች በስልጠናው ተሳትፈዋል፡፡
በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ሥልጠናው ተሻሽሎ በወጡ የግዢ አዋጅና መመሪያ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ የተሰጠ መሆኑን ገልፀው ሥልጠናውን በጥሩ ሁኔታ ለሰጡ የባለስልጣን መ/ቤቱ አሰልጣኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በቀጣይም ከግዢ አዋጁ ጋር በተያያዘም ሆነ በተሻሻሉት የፋይናንሺያልና የክዋኔ ኦዲት ማንዋሎች ላይ ቀጣይነት ያላቸው ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ዋና ኦዲተሯ ገልፀው ሠልጣኞች አዳዲስ የሚወጡ መመሪያዎችንና አሰራሮችን በግል በማንበብ ይበልጥ በዘርፉ የሚገባቸውን እውቀት ማዳበር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች በስልጠናው ማጠናቀቂያ በሰጡት ሀሳብ ስልጠናው ለስራቸው ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ያገኙበትና በግዥና ንብረት አያያዝ ላይ የነበሩ ብዥታዎችን ያጠፋላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር ስልጠናዎች በአጠቃላይ 410 ሰልጣኞች የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይም በተመሳሳይ መልኩ የክዋኔ ኦዲተሮች በተሻሻሉት የግዢ ህጎች የሚሳተፉበት ሦስተኛ ዙር ስልጠና ከነሀሴ 5 እስከ ነሀሴ 9/2017 ዓ.ም የሚቀጥል መሆኑን ከመ/ቤቱ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡