ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የማኔጅመንት አባላት በለውጥ ስራ አመራር በተለይም በዲስ መልክ ተሻሽሎ የተዘጋጀውን የመ/ቤቱ የሥራ አፈጻጸም አመራር እና ምዘና ሥርዓት ማንዋል ለማስተዋወቅና የትግበራ አቅጣጫዎችን ለማሳየት የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብር ተካሄደ፡፡
በለውጥና መልካም አስተዳደር ስራዎች ዳይሬክቶሬት አማካይነት ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም በመ/ቤቱ የስልጠና ማዕከል ለማኔጅመንት አባላት የተሰጠው የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ በለውጥ ስራ አመራር ሂደት የሥራ አፈጻጸም ስርዓትን አስመልክቶ በተሻለና ቀልጣፋ በሆነ አሠራር በስራ ላይ ለማዋል በሚያስችል ሁኔታ የተዘጋጀውን የትግበራ ማኑዋል በአግባቡ ለመተግበር እንዲቻል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡
ቀደም ሲል ሲተገበር የነበረው የምዘና ስርዓት ከመ/ቤቱ የተለየ የአሠራር ባህሪይ ጋር የማይሄድና የእቅድ አፈጻጸምን በአግባቡ የማይመዝን በመሆኑ የምዘና ዘዴውን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑና የትግበራ ማኑዋሉ ከመተግበሩ በፊትም የአፈጻጸም ምዘና ለሚያካሂዱ የመ/ቤቱ አመራሮች የአተገባበር ግንዛቤ መስጠትና የትግበራ አሠራሩንም ሊያዳብሩ የሚችሉ ሀሳቦችን ማሰባሰብ አስፈላጊ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡
በለውጥና መልካም አስተዳደር ስራዎች ዳይሬክቶሬት በኩል የቀረበውን ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ተከትሎ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን ክብርት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤና ክቡር ም/ዋና ኦዲተር አቶ አበራ ታደሠ በመርሀ ግብሩ ማጠናቀቂያ ላይ ተገኝተው ከተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎችን መነሻ አድርገው የግንዛቤ ማስጨበጫውን አስፈላጊነትና ለውጤታማ ትግበራውም የማኔጅመንት አባላት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የትግበራ ስርዓቱ በሂደት የሚዳብር መሆኑን ጨምረው የገለጹት ከፍተኛ አመራሮቹ ሁሉም የመ/ቤቱ የስራ ክፍሎች እና ሠራተኞች በተለይም የማኔጅመንት አባላት ለማኑዋሉ ትግበራና ለተሻለ የምዘና ሥርዓቱ ውጤታማነት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡