በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የ2012 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ይፋዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡
ኮሚሽኑ በበጀት አመቱ የኦዲት ግኝቱ “አስተያየት ለመስጠጥ የማያስችል” /Disclaimer of Opinion/ የኦዲት አስተያየት እንደተሰጠው እና በቅርቡም በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የገንዘብ ቅጣት እና ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው ተቋማት አንዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በኦዲት ሪፖርቱ ኮሚሽኑ በ2012 በጀት ዓመት ላልተገኘ አገልግሎትና ግዢ በድምሩ ብር 145,341.22 ክፍያ ፈጽሞ መገኘቱ፤ የመነሻ ሰነድ ያልቀረበበት ብር 16,867,409.40 መገኘቱ እና በወጪ ሂሳብ መደብ የተመዘገበ ብር 87,528,865.98 አስረጂ ሰነድ እንዳልቀረበ ተጠቁሟል፡፡
በተለያዩ የሂሳብ መደቦችና አርዕስቶች በድምሩ ብር 1,943,001,907.03 ያልተሰበሰበ ውዝፍ ሂሳብ እና ብር 55,751,342.21 ውዝፍ ተከፋይ ሂሳብ በኦዲቱ መገኘቱም ተመላክቷል፡፡
ከበጀት አጠቃቀም አኳያም ኮሚሽኑ ለመደበኛና ለካፒታል በጀት ከተመደበለት በድምሩ ብር 1,884,093,652.16 ሥራ ላይ ያልዋለ በጀት መገኘቱን እና በኮሚሽኑ ዋና መ/ቤት እና በናሙና በታዩ ቅርንጫፍ መጋዝኖች በርካታ ያለአግባብ የተከማቹና የተያዙ ንብረቶች መኖራቸው ተገልጿል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ የኮሚሽኑ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡
የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች በኦዲት ግኝቱ ላይ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ በአብዛኞቹ ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው በተለይም በኮሚሽኑ የውስጥ ኦዲት ዳይሬክተር የተሰጡ ምላሾች አግባብነት የሌላቸው እና በማስረጃ ያልተደገፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ሥራውን ሲሰራ የኮሚሽኑን የሥራ ባህሪ ታሳቢ ባደረገ መንገድ ማከናወኑን ምክትል ዋና ኦዲተሯ አስታውሰው ነገር ግን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለተፈጸሙ ግዢዎች ተቋሙ ሰነዶችን በአግባቡ መዝግቦ ሊይዝ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም መረጃ ያልቀረበለት የሂሳብ ምዝገባ 16.8 ሚሊየን ብር እንዲሁም መነሻ ሰነድ ያልቀረበበባቸው 87.5 ሚሊየን ብር ሰነዳቸው ተጣርቶ መቅረብ አለበት ብለዋል፡፡
በንብረት አስተዳደር በኩል በተቋሙ በኩል ተወስደዋል ተብለው የቀረቡ የማስተካከያ እርምጃዎች በቀጣይ በክትትል ኦዲት የሚረጋገጡ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን ተቋሙ የራሱን የሥራ ባህሪ ታሳቢ ያደረገ የንብረት አስተዳደር ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባም ክብርት ወ/ሮ መሠረት አስገንዝበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው በተለይም በኮሚሽኑ የውስጥ ኦዲት ዳይሬክተር የተሰጡ ምላሾች አግባብነት የሌላቸው መሆኑን ገልጸው ተቋሙ ያለበትን የተበላሸ የሂሳብና የንብረት አያያዝ ሊፈትሽ፤ በሰው ሃይል ቅጥር እና ብቃት እንዲሁም በአሰራር ሥርዓት ያሉበትን ብልሹ አሠራሮች ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራባቸው ይገባል ብለዋል፡፡
በፍትህ ሚኒስቴር ተላላፊ እና ወንጀል-ነክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ወ/ሮ ትብለጥ ቡሽራ በበኩላቸው የኦዲት ሪፖርቱ አስደንጋጭ እንደሆነባቸው እና በተቋሙ የውስጥ ኦዲተር በኩል ምላሽ የተሰጠበት አግባብም በተቋሙ የሚና መደበላለቅ እንዳለ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም በኦዲት ግኝቱም ሆነ በተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች ከተሰጡ ምላሾች መረዳት የሚቻለው በተቋሙ ሰፊ የአሠራር ችግሮች እንዳሉ የሚያሳይ በመሆኑ በተቋሙ ላይ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ አስተዳደራዊ፣ የወንጀል እና የፍትሃብሔር ተጣያቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሣ በተሰጣቸው አስተያየት መሠረት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀው የሠራተኞችን የአቅም ክፍተት ለመቅረፍ የሪፎርም ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በትኩረት እንደሚሠሩ አስረድተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው በተቋሙ መስተካከል ያለባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መኖራቸውን ገልጸው ተቋሙ በናሙና የታዩ የኦዲት ግኝቶችን መነሻ በማድረግ በጥልቀት ራሱን ሊመለከት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም ኮሚሽኑ እስከ ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የኦዲት ማስተካከያ ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብ፤ የስነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽንም ከስነ-ምግባር ብልሹነት ጋር ተያያዥ ጉዳዮች ካሉ ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብ እና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትም ለኮሚሽኑ በኦዲት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡
አክለውም የገንዘብ ሚኒስቴርም ለኮሚሽኑ ልዩ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ካለበት ችግር እንዲወጣ እንዲያግዝ እንዲሁም የውስጥ ኦዲተር የሙያ ስነ-ምግባር በአግባቡ በመፈተሸ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የአሠራር ብልሹነት በፈጸሙ ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር ተጨማሪ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ወስዶ እስከ ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ እንዲያሳውቅ አሳስበዋል፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር በበኩሉ ከወንጀል አኳያ የሚያስጠይቁ ጉዳዮችን ካሉ በቂ ምርመራ አድርጎ ክስ እንዲመሰርት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡





