News

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የመንግስትን የፋይናንስ ህግ ተከትሎ መስራት እንዳለበት ተገለጸ

 

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የመንግስትን የፋይናንስ ህግ ተከትሎ በመስራት በ2010 በጀት አመት የሂሳብ ኦዲቱ የታዩበትን ድክመቶች ማስወገድ እንዳለበት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ህዳር 17፣ 2012 ዓ.ም ከኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ወቅት አሳሰበ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኮሚሽኑ ላይ ያደረገው የፋይናንሻል ኦዲት ኮሚሽኑ በሂሳብ አያያዝና በንብረት አስተዳደር በኩል በርካታ ድክመቶች እንዳሉበት አሳይቷል፡፡

ከድክመቶቹ መካከል ኮሚሽኑ በባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በኩል ለጅቡቲ የወደብ አገልግሎት እንዲከፈል ለሰጠው 36.39 ሚልየን ብር የገቢ መቀበያ ደረሰኝ አለመቀበሉ፣ በ1.3 ቢልየን ብር የቀረጥ ሂሳብ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በኮሚሽኑ ስም ወደሀገር ውስጥ ላስገቡት እህልና አልሚ ምግብ የገቢ ደረሰኝና ዲክላራሲዮን አለማቅረቡ ብሎም በ1.92 ቢልየን ብር ለገዛው ስንዴና አልሚ ምግብ እንዲሁም በብር በ7,475 ለገዛው የመኪና ወንበር ልብስና ተጓዳኝ እቃዎች የንብረት ገቢ ደረሰኝ አለማቅረቡ ይገኛሉ፡፡

ከዚህም ሌላ ኮሚሽኑ በ544.6 ሚልየን ብር የመኪና ጎማ፣ የፕላስቲክ ሺት፣ የምግብ ዘይትና ወተት እንዲሁም  በ12 ሚልየን ብር የመጓጓዣ አገልግሎት በድምሩ 556.6 ሚልየን ብር የሚያወጣ የእቃና የአገልግሎት ግዥ ካለጨረታ በቀጥታ ፈጽሟል፡፡ የእርዳታ እህል ላጓጓዙ አገልግሎት ሰጪዎች ከከፈለው ገንዘብ ውስጥም በተጨማሪ እሴት ታክስና በገቢ ግብር መልክ መሰብሰብ የነበረበትን በድምሩ 1.8 ሚልየን ብር ሳሰበስብ ቀርቷል፡፡

በሌላ በኩል ደብሊው ኤ ለተባለ ዘይት አቅራቢ ድርጅት 86.3 ሚልየን ብር የቅድመ ክፍያ ሲከፍል ዋስትና እንዳላስቀረበና ለዚሁ ድርጅት በድጋሚ 185.1 ሚልየን ብር ለሚያወጣ ዘይት ግዥ ቅድሚያ ክፍያ 129.5 ሚልየን ብር የባንክ ዋስትና መቀበል ሲገባው 18.5 ሚልየን ብር ብቻ ዋስትና መቀበሉ በኦዲቱ ታውቋል፡፡

እንደዚሁም ለድርቅ መቋቋሚያና ለሌሎች ስራዎች በሚል ለክልሎች የተለያዩ ቢሮዎች በባንክ ካስተላለፈው ወደ 806.5 ሚልየን የሚጠጋ ብር ውስጥ ላወጡት ወጪ ዝርዝር የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ ክልሎቹ ባቀረቡት የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ብቻ ሂሳቡን እንዳወራረደ ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

በተጨማሪም ከውሎ አበልና ለሰራተኛ ለመጓጓዣ ከተሰጠ ቅድሚያ ክፍያ ውስጥ ከ608.7 ሚልየን ብር ለረጅም አመታት ሳይወራርድ በተሰብሳቢነት ተገኝቷል፡፡

ኮሚሽኑ አገልግሎት የሚሰጡና የማይሰጡ ንብረቶቸን በወቅቱ እንደማይመዘግብና እንደማያስወግድም ኦዲቱ አመልክቷል፡፡

ኦዲቱ ሌሎች የሂሳብ አያያዝ ድክመቶችንም አሳይቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሀመድ ዩሱፍ ስለግኝቶቹና ግኝቶቹን ለማረም በኮሚሽኑ ስለተወሰደው እርምጃ ማብሪያ እንዲሰጥ በጠየቁት መሰረት ኮሚሽነሩ ክቡር አቶ ምትኩ ካሳና የመ/ቤቱ የስራ ኃፊዎች በዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በሰጡት መልስም በባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በኩል ለጅቡቲ ወደብ ብር 36.4 ሚልየን ለስንዴ ማራፊያና ማስጫኛ የቅድሚያ ክፍያ እንዲከፈል ሲደረግ ኮሚሽኑ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ በወቅቱ መቀበሉን ገልጸዋል፡፡ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በጅቡቲ ወደብ ላይ በጅቡቲ ፍራንክና በአሜሪካ ዶላር የከፈለው ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ብር ተቀይሮ የ36 ሚልየን ብር ሳይሆን የ55 ሚልየን ብር ህጋዊ ሰነድ ለማወራረጃነት እንዳቀረበና ለዚህ ገንዘብ በድጋሚ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ማቅረብ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም አስፈላጊው ሰነድ በመቅረቡ ችግሩ እንደተፈታ ገልጸዋል፡፡

ከ1.3 ቢልየን ብር በላይ በቀረጥ ሂሳብ በኮሚሽኑ ስም በወጪ ተመዝግቦ የገባው እህልና አልሚ ምግብን በተመለከተም ኮሚሽኑ በውጭ ሀገር እርዳታ ድርጅቶች ወደ ሀገር ለሚገባ እርዳታ የቀረጥ ሽፋን እንደሚሰጥ ገልጸው ነገር ግን እርዳታው ኮሚሽኑ ጋር ሳይደርስ በቀጥታ ወደ እርዳታ ሰጪዎቹ መጋዘን የሚሄድ በመሆኑ ኮሚሽኑ ገቢ ላላደረገው እቃ የገቢ ደረሰኝ መቁረጥ እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ችግሩን ለገንዘብ ሚኒስቴር ማሳወቁን ገልጸው ሚኒስቴሩ  ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ጋር በመሆን ለችግሩ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ አያይዘውም ኮሚሽኑ በ1.9 ቢልየን ብር ያስገባው ስንዴና አልሚ ምግብ በቀጥታ ከወደብ ተነስቶ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ወዳሉት መጋዘኖቹ እንደገባና መድረሳቸውን በማረጋገጥ ክፍያ እንደፈጸመ ገልጸው ነገር ግን አጓጓዦቹ ዋናውን የንብረት ገቢ ደረሰኝ የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ ለመቀበል ስለሚወስዱ የገቢ ደረሰኙን ማቅረብ እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡ ንብረቱ ገቢ ስለመደረጉ ከየመጋዘኖቹ ማስረጃው ስላለ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከዚያው ማጣራት እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ የመኪና ወንበር ልብሱም ገቢ መደረጉን አክለዋል፡፡

ብር 556.6 ሚልየን የሚያወጣ የእቃና የአገልግሎት ግዥ ካለጨረታ በቀጥታ ከመፈጸሙ ጋር አያይዘውም አደጋዎች ሲፈጠሩ በሚኖረው አጣዳፊ ሁኔታ ምክንያት የጨረታ ሂደት በመጠበቅ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ በሚል ካለጨረታና በቀጥታ ከአንድ አቅራቢ ግዢ እንደሚፈጸም ነገር ግን በነዚህ ወቅቶችም ቢሆን የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲን እንደሚያስፈቅድ ገልጸዋል፡፡ ከመ/ቤቱ የስራ ባህሪ አንጻርም የግዢ ህጉ ሊሻሻልና ኮሚሽኑ ልዩ መብት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውጪ የምግብ ዘይት በንግድ ሚኒስቴር በኮታ ከተሰጡት አቅራቢዎች ኤጀንሲው እንደሚገዛ እህል ደግሞ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ከውጭ ሀገር ተገዝቶ እንደሚገዛና ከሀገር ውስጥ ከተገዛም በንግድ ሚኒስቴር በሚመራ ኮሚቴ ጥናት ተደርጎ በሚወሰን ዋጋ መሰረት በፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ስር ከተደራጁ የህብረት ስራ ማህበራት ግዥ እንደሚፈጸም፣ ማህበራቱ ማቅረብ ካልቻሉም የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲን በማስፈቀድ ከማንኛውም አቅራቢ እንደሚገዛ ገልጸዋል፡፡

የእርዳታ እህል ካጓጓዙ አገልግሎት ሰጪዎች ከሚሰበሰበው ተጨማሪ እሴት ታክስና ገቢ ግብር ጋር በተያያዘም ከዚህ ቀደም ገንዘቡን ለመሰብሰብ ሙከራ ተደርጎ አጓጓዦቹ ይህ ታክስና ግብር አይመለከተንም በማለት ስራ አቋርጠው ችግር መፈጠሩን አስታውሰዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በ2006 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ እና በገንዘብ ሚኒስቴር በ2010 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ መነሻነት ኮሚሽኑ ታክስና ግብሩን በአሁኑ ወቅት እየሰበሰበ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

ዲ ደብሊው ለተባለ ዘይት አቅራቢ ድርጅት የቅድመ ክፍያ ሲከፈል መቅረብ ከነበረበት ዋስትና ጋር በተገናኘም በ2002 በወጣ መመሪያ መሰረት አቅራቢው 50 በመቶ ዋስትና እንዲያቀርብ በማድረግ እንደተስተካከለና ወደፊት ተመሳሳይ ስህተት ላለፈጸም እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

ለክልሎች ስለተላለፈው ገንዘብ ሲገልጹም ገንዘብ ሚኒስቴር ከበጀት ቀመር ጋር በተየያዘ ምክንያት ለክልሎች ገንዘቡን መላክ ስለማይችል በኮሚሽኑ በኩል መላኩን አስታውሰው ኮሚሽኑ በተላከው ገንዘብ እስከወረዳ ድረስ የተሰሩ ስራዎችን ወርዶ ማረጋገጥ ስለማይችል ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ክልሎቹ በሚያቀርቡት የገቢ ደረሰኝ እንዲወራድ ተደርጓል ብለዋል፡፡ በዚህም ተሰብሳቢ ከነበረው 3.5 ቢልየን ብር ውስጥ በከፍተኛ ጥረት ወደ  806.5 ሚልየን ብር ማድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ሰነድ ይምጣ ከተባለ እስከወረዳ ድረስ ተወርዶ ለተሰሩ ስራዎች ኮሚሽኑ ማስረጃ ማቅረብ እንደማይችል ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ገንዘብ ሚኒስቴርና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ተነጋግረው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ባለው ስልጣን ሂሳቡን አዲት እንዲያደርግ ካልሆነም የክልል ዋና ኦዲተር ቢሮዎች ኦዲት እንዲያደርጉት ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

ከውሎ አበልና ለመጓጓዣ ለሰራተኛ ከተሰጠ ቅድሚያ ክፍያ ጋር ተያይዞ ካልተወራደው ከ608 ሚልየን ብር ውስጥ ወደ 283.8 ሚልየን ብር የሚጠጋ እንዲወራድ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ሳይወገዱ የተከማቹ ንብረቶችን አስመልክቶም ከ40 አመታት ጀምሮ የተከማቹ ንብረቶች እንዳሉና ከነዚህም ውስጥ በአሁኑ ወቅት የሌሉ የድሮ ተሽከርካሪዎች መለዋወጫዎች እንደሚገኙ ገልጸው በተወሰነ ደረጃ ቁርጥራጭ ብረቶችን፣ ጎማዎችንና የማያገለግሉ ተሽከርካሪዎችን ማስወገድ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን ሰነድ ያልተገኘላቸው ተሽከርካሪዎችን ለማስወገድ እንዳልተቻለና ያልተወገዱ ኮምፒዩተሮችም እንዳሉ ገልጸው የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በሚሰጠው መመሪያ መሰረት ለማስወገድ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የስራ ኃላፊዎቹ በሌሎቹ የሂሳብ አያያዝና የንብረት አስተዳደር ድክመቶች ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅም ሆነ የንብረት አስተዳደር መመሪያዎች ኮሚሽኑን ከስራ ባህሪው አንጻር የማያሰሩበት ሁኔታ ስላለ ቋሚ ኮሚቴው፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተርና ኮሚሽኑ ተነጋግረው መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሰጡት አስተያየት ኮሚሽኑ ከሰዎች ህይወት ጋር ተያያዥነት ያላቸው በርካታ  ስራዎችን እንደሚሰራ በዋና ኦዲተር መ/ቤት በሚገባ እንደሚታወቅ ገልጸው የመንግስት በጀትም ሆነ በእርዳታ የሚገኘው ገንዘብ በመመሪያዎች መሰረት ለታለመለት አላማ መዋሉን መረጋገጥ አለበት በሚል ኦዲቱ እንደተካሄደ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል ብለዋል፡፡

የግዥ አዋጁ ሁለንተናዊ የሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን የሚያመቻች እንደሆነና በአስቸኳይ ጊዜም ቢሆን ግዢ እንዴት መፈጸም እንደሚገባው የሚያስረዳ እንደሆነ በመጥቀስ አስቸኳይ ያልሆኑና ታቅደው መከናወን ይችሉ የነበሩ እንደ ተሽከርካሪ ጎማ ያሉ ግዥዎችን በምሳሌነት በመጥቀስ ህጎቹ አላሰራ በማለታቸው ብቻ በአስቸኳይ ግዥ የተፈጸመ አስመስሎ ማቅረቡ ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ለእርዳታ ስራ የተፈጸሙ ግዥዎችም ቢሆኑ የግዢ ህጉ ችግር ያለበት በመሆኑ የተካሄዱ እንደሆኑ በማስመሰል መቅረብ የለበትም ብለዋል፡፡ አላሰራ ያሉ ህጎች ካሉም ለሚመለከተው አቅርቦ በአግባቡ መፈጸም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በኩል የሚፈጸመው የቅድሚያ ክፍያ አሰራር ላይም ከሂሳብ አሰራር አኳያ ችግር እንዳለበት በመግለጽ አሰራሩ እንዲፈተሽ አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኮሚሽኑ ለክልሎች ካስተላለፈው ገንዘብና ወደራሱ መጋዘኖች ካስገባውን ንብረት ጋር ተያይዞ ገቢ ተደርገው በአግባቡ ስራ ላይ ስለመዋላቸው አስፈላጊ ሰነዶችን እስከወረዳ ድረስ የስራ ግንኙነትን ፈጥሮ በራሱ አሰባስቦ ለኦዲት ማቅረብ ሲጠበቅበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር እየሄደ ኦዲት ያድርጋቸው በሚል ጉዳዩን የገፋበት አግባብ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ ለክልሎች የተላለፈው ገንዘብ በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን የማረጋገጥ ሀላፊነት የኮሚሽኑ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡ ኮሚሽኑ ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስፈቅዶ እርዳታ ሰጪዎች ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተው በየመጋዘኖቻቸው ገቢ ያረጓቸውን እህልም ሆነ ሌሎች ንብረቶች መረጃም ቢሆን ከድርጅቶቹ ጋር ግንኙነት ፈጥሮ ማምጣት ይቻል እንደነበረ አመልክተዋል፡፡

በንብረት አወጋገዱ፣ ምዝገባና አያያዝ ላይም የማስወገድ ጅማሮዎች ቢኖሩም ስራው ገና በሂደት ላይ ያለና በጥልቀት ያልተገባበት እንደሚመስል ገልጸው ኤጀንሲው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እስከመጨረሻ ድረስ ጥረት በማድረግ ንብረቱን ማስወገድ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተጨማሪ ጥያቄዎችን አቅርበው ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን በባለድርሻ አካላትም አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በሰጡት አስተያየት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ኮሚሽኑ የሰው ህይወትና ንብረት እንዳይጠፋ እንደሚሰራ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ገልጸው ኮሚሽኑ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ሲቀበል በህግ ሊመራ እንደሚገባና ህጎቹ አላሰራ ካሉትም የተለየ ህግ እንዲወጣለት ለሚመለከተው አካል ጥያቄ የማቅረብ ሀላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሰረት ኮሚሽኑ ከኦዲቱ መጠናቀቅ በኋላ በተወሰኑ ግኝቶች ላይ ማስረጃ እንዳቀረበ ገልጸው በይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረኩ ላይ በተነሱት አንዳንድ ግኝቶች ላይ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡

በዚህም ኮሚሽኑ በእርዳታ ሰጪዎች ለሚመጣው እህል በቀረጥ መልክ ሂሳቡን በወጪ መዝግቦ ከያዘ ንብረቱን ተረክቦ የገቢ ደረሰኝ መቁረጥና ለእርዳታ ሰጪዎቹ ማሰራጨት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ በኮሚሽኑ መጋዘኖች ለገቡ ንብረቶችም ሰነዱ መቅረብ ያለበት በኮሚሽኑ እንደሆነ ገልጸው ለዚህም ሰነዶቹን አሰባስቦ ለመያዝ አሰራሩን ማስተካከል እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡

ከቀጥታ ግዢ ጋር በተያያዘም የንግድ ሚኒስቴር በግዢ አፈጻጸም ላይ መመሪያ መስጠት እንደማይችልና የመንግስትን የግዥ መመሪያ መሰረት አድርጎ ግዢ መፈጸም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የእርዳታ እህል የሚያጓጉዙ አገልግሎት ሰጪዎች ተጨማሪ እሴት ታክስና የገቢ ግብር አይመለከታቸውም በተባለው ጉዳይ ላይም ሲያስረዱ በ2011 በወጣው መመሪያ መሰረት ለየብስ፣ ለአየርና ለባህር ትራንስፖርት ኪራይ አገልግሎት ከሚከፈሉ ክፍያዎች የተጨማሪ እሴት ታክስን ዊዝሆልዲንግ (vat withholding) ቀንሶ ማስቀረት እንደሚገባ ስለተደነገገ ኮሚሽኑ ገንዘቡን ቆርጦ ለመንግስት ገቢ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ለክልሎች የተላለፈው ገንዘብ ለታሰበለት ስራ መዋሉ መረጋገጥ ያለበት በመሆኑ በገቢ ደረሰኝ ብቻ መወራረዱን የዋና ኦዲተር መ/ቤት እንደማይቀበለውም ክብርት ምክትል ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ገንዘቡ ለታሰበው አላማ ስለመዋሉ ኮሚሽኑ አስፈላጊ ሰነዶችን ማቅረብ አለበት ብለዋል፡፡

ከተሰብሳቢ ሂሳብ ውስጥ የተወራረደው 282.8 ሚልየን ብር እንዳለ ሆኖ ያልተወራረደው ቀሪ ገንዘብ ላይም በቀጣይ ኮሚሽኑ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ክብርት ወ/ሮ መሰረት ተናግረዋል፡፡

ከንብረት ማስወገድ ውጪም የንብረት አያያዙ ሰፊ ክፍተት ያለበት በመሆኑ ኤጀንሲው በዚህ ዙርያም ጠንክሮ መስራት አለበት ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት ለእርዳታ ሰጪዎች የሚገባው እህልና ሌሎች ግብአቶች ወደ ኮሚሽኑ መጋዘን የማይገቡ በመሆኑ ከቀረጥ ነጻ እነዲገቡ ገንዘብ ሚኒስቴርን እንዲጠይቅ ከሁለት አመታት በፊት የዋና ኦዲተር መ/ቤት ለኮሚሽኑ ምክር ሰጥቶ እንደነበር አስታውሰው ይህንን ጉዳይ ኮሚሽኑ ተከታትሎ መፍታት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሂሳብ መዝግቦ ገንዘቡን ወጪ ካደረገ በኋላ ንብረቱ ገቢ መደረጉን የሚያሳይ መረጃ አለማቅረቡ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ገልጸው ኮሚሽኑ ላወጣው ወጪ የንብረት ገቢ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡ በእርዳታ ሰጪዎች በኩል የገባው እርዳታ ስርጭትም በደንብ መረጋገጥ አለበት ብለዋል፡፡

መሰብሰብ ያለበትን ታክስ ሳይሰበስቡ መቅረት ይህን በፈጸመው ኃላፊ ላይ ተጠያቂነት የሚያስከትል ጉዳይ መሆኑንም ክቡር ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ለክልሎች ካስተላለፈው ገንዘብ ጋር ተያይዞም ማንኛውም አካል በጀት እስከተቀበለ ድረስ በጀቱ ስራ ላይ ስለዋለበት አግባብ በቂ ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት ገልጸው ኮሚሽኑ ማስረጃ አላቀርብም ካለ ተጠያቂነቱን እንደሚወስድ አሳስበዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም ለክልሎች ገንዘብ የሚሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወሰነው ቀመር እንደሆነና ገንዘቡን ለክልሎች ማስተላለፍ አስፈላጊና የሚታመንበት ከሆነም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ተጨማሪ በጀት ታውጆ መላክ ሲገባው ገንዘብ ሚኒስቴር ከዚህ ባፈነገጠ መንገድ ገንዘቡን እየላከ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ይህንን አካሄድ ማስተካከል ይገባዋል ብለዋል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው የፋይናንስ ኦዲት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን በሰጡት አስተያየት ኮሚሽኑ ጫናና ውስብስብ ጉዳዮች እንዳለበት ግንዛቤ ቢኖርም ከህግና መመሪያ ውጪ የሆኑ ተግባራትን ማከናወን እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡

የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ ትክክለኛ አሰራር ተፈጥሮ ኮሚሽኑ የሚሰጠው አገልግሎት ለተጠቃሚው መድረስ አለመድረሱን ማረጋገጥ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን ከህግ አኳያ አላሰራ የሚሉ ጉዳዮች ካሉ በደንብ ለይቶ ለገንዘብ ሚኒስቴር ማቅረብና ከዋና ኦዲተር መ/ቤት ጋር በመነጋገር መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሀመድ ዩሱፍ ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣንና ሀላፊነት አንጻር የተቋቋመበትን አላማ ለማስፈጸም በኦዲት ግኝት የተገኙ ጉድለቶችን በአስቸኳይ ማረም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *