News

የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሂሳብ አያያዝና ንብረት አስተዳደር ሥርአቱን እንዲያሻሽል ተጠየቀ

ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሂሳብ አያያዝና ንብረት አስተዳደር ሥርአቱን በማሻሻል የሀገሪቱ ሀብት በአግባቡና በህጋዊ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ እንዳለበት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በኦጀንሲው የ2007 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም አድርጓል፡፡

በስብሰባው ወቅት ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኤጀንሲው ላይ ያከናወነውን የሂሳብ ኦዲት ግኝት መሰረት በማድረግ በሂሳብ አያያዝና በንብረት አስተዳደር ረገድ በተቋሙ ላይ በታዩ  ጉድለቶች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥና የተወሰዱ እርምጃዎችም እንዲገለጹ ጠይቋል፡፡

ኤጀንሲው በገቢ አሰባሰብ ረገድ ከሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ለአየር ንብረት ትንበያ አገልግሎት በየአመቱ 507ሺህ ብር በገቢ የሰበሰበ ቢሆንም በሚመለከተው አካል የጸደቀ የአገልግሎት ታሪፍ ሳይኖር የተሰበሰበ በመሆኑ ገቢው በታሪፉ መሰረት መሰብሰቡን ማረጋገጥ እንዳልተቻለ እንደዚሁም ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሂሳብ መደቦች ለውሎ አበል፣ ለመጓጓዣና ለሌሎች ጉዳዮች የተሰጠ ከ2.4 ሚልዮን ብር በላይ አለመወራረዱ እነዚህ ጉዳዮችም በ2006 በጀት አመት ኦዲት ግኝት ላይ አስተያየት ቢሰጥባቸውም አለመስተካከላቸው ተመልክቷል፡፡

በተከፋይ ሂሳብ ረገድም ከ3.7 ሚልዮን ብር በላይ የሆኑ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በተከፋይ የተያዙ ልዩ ልዩ ሂሳቦች መኖራቸውና ይህም በ2006 በጀት አመት ኦዲት ግኝት ላይ አስተያየት ቢሰጥበትም አሁንም እንዳልተስተካከለ ተገልጿል፡፡

ከወጪ ሂሳብ ጋር በተያያዘም በድምሩ ከ17 ሺ ብር በላይ የሆኑ ወጪዎች በትክክለኛው የሂሳብ መደብ ላይ አለመመዝገባቸው፣ ከሐምሌ 01፣ 2006 እስከ ሰኔ 30፣ 2007 ዓ.ም በተዘጋጁ ሁሉም ቫውቸሮች ክፍያ ከመፈጸሙ በፊት በጀት ስለመፈቀዱ በወጪ ማስመስከሪያ ደረሰኝ ላይ በፊርማ ያልተረጋገጠ መሆኑ እንዲሁም ከ75 ሺህ ብር በላይ ለሆነ ግዥ ጨረታ መውጣት ሲገባው ከ580 ሺህ ብር በላይ የሆነ የሆቴል መስተንግዶ አገልግሎት በዋጋ ማወዳደሪያ የተፈጸመ መሆኑ በኦዲቱ ተመልክቷል፡፡

በሂሳብ ሰነድ አያያዝና አጠቃቀም በኩልም በኤጀንሲው የአዳማና ጅግጅጋ ቅርንጫፎች ችግሮች መኖራቸውና የውስጥ ኦዲተር የሌላቸው መሆኑ በኦዲቱ ተገልጿል፡፡

ከንብረት አስተዳደር ጋር ተያይዞ በዋናው መ/ቤት ከሐምሌ 01፣ 2006 እስከ ሰኔ 2007 ዓ.ም ድረስ የአላቂና ቋሚ እቃዎች ስቶክ ካርድ ምዝገባ አለመደረጉ፣ በአዳማ ቅርንጫፍ የእቃ ግምጃ ቤት የንብረት ወጪ ደረሰኝ በጅግጅጋ ቅርንጫፍ ደግሞ የንብረት ገቢና ወጪ ደረሰኝ የማይዘጋጁ መሆኑ እንዲሁም በሁለቱም ቅርንጫፎች አንዳንድ እቃዎች በስቶክ ካርድ ላይ ያልተመዘገቡ መሆኑና አገልግሎት የማይሰጡ እቃዎች በግምጃ ቤቶቹ መገኘታቸውን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

ከበጀት አጠቃቀም ጋር በተገናኘም በ2007 በጀት አመት ለየፕሮግራሞቹ የተፈቀደው በጀት አጠቃቀም በየሂሳብ ኮዶቹ ሲታይ ከ12 ፐርሰንት በላይ ብር 13,930,699.05 ስራ ላይ አለመዋሉ እንዲሁም ብር 1,952,325.26 ለየሂሳብ መደቦቹ ከተደለደለው በጀት በላይ ስራ ላይ መዋሉ ተመልክቷል፡፡

በነዚህ የኦዲት ግኝቶች ምክንያትና በተወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎች ላይ የኤጀንሲው ዋና  ዳይሬክተር አቶ ዱላ ሻንቆና ሌሎች የኤጀንሲው የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

_DSC0016ከሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ስለሚሰበሰበው ገቢ አስመልክቶ በ1973 ዓ.ም ሚቲዎሮሎጂ የአቪዬሽን መ/ቤት አንድ ዲፓርትመንት እንደነበረና በዚሁ አመት ራሱን ችሎ ሲገነጠል አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ በሚል በዚያ ጊዜ በነበረው አሰራር 507 ሺህ ብር ከአቪይሽን መ/ቤቱ ይሰጠው እንደነበረ፣ ከሃያ አመታት በፊት የአገልግሎት ክፍያው እንደሚያንስ ኤጀንሲው አስጠንቶ ለመንግስት ቢቀርብም ውሳኔ እንዳልተሰጠው አሁን ግን ከዓለም አቀፍ አሰራር ጋር የተጣጣመ ክፍያ እንዲያገኝ ኮሚቴ አቋቁሞ ሰነድ በማዘጋጀት ላይ እንደሆነና ሲጠናቀቅ መንግስትን እንደሚያስወስን ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡

ያልተወራረዱ ሂሳቦችን በተመለከተም በዋናው መ/ቤትም ሆነ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በቂ ባለሙያ ባለመኖሩ የመጣ መሆኑን ገልጸው ኮሚቴ ተቋቁሞ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ወደኋላ በመሄድ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን በማጣራት ከ8.8 ሚልዮን ብር በላይ በተሰብሳቢ ይታይ የነበረው ተወራርዶ ማስረጃው ለሚመለከታቸው አካላት እንደተላከ ገልጸዋል፡፡

በተከፋይ የተያዙ ሂሳቦች ጋር በተያያዘም ሂሳቦቹ በእዳ የተያዙ ወይም ግዴታ የተገባባቸው ገንዘብ ሳይሆኑ የሂሳብ ማስተካከያ ያልተሰራባቸው ነገር ግን በየአመቱ ለገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ፈሰስ የተደረጉ በወረቀት ላይ ያሉ ሂሳቦች መሆናቸውን ገልጸው ሰነዶችን በማሰባሰብ በውስጥ ኦዲት ተጣርቶ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ቀርቦ ሲረጋገጥ ተገቢው እርምጃ መወሰዱንና የተከፋይ ሂሳብ መጠኑን በ2008 በጀት አመት ወደ 3 ሚልዮን ብር መቀነስ መቻሉን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

ከሂሳብ መደብ ምዝገባ ስህተት ጋር ተያይዞም በሰው ሀይል እጥረትና ብቃት ማነስ ሂሳቦች በትክክለኛ መደባቸው ላይ አለመመዝገባቸውና መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ በየቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ እንዲስተካከል እየተሰራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን የመስተንግዶ ግዥ ካለ ጨረታ መከናወንን አስመልክቶም የአለም ሚቲዎሮሎጂ ቀንን በገልማ አባ ገዳ አዳራሽ ለማካሄድ ታቅዶ ስብሰባው ሲቃረብ አዳራሹን መጠቀም እንደማይቻል በመገለጹ ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ ግልጽ ጨረታ ማውጣት ባለመቻሉ በዋጋ ማቅረቢያ ብቻ የመንግስት ግዥ ኤጀንሲን ሳያስፈቅዱ አገልግሎቱ መገዛቱንና ወደፊት እንደዚሀ ያለ ሁኔታ ግዥ እንዳይፈጸም ጥንቃቄ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

በቅርንጫፍ ጽቤቶች የታየውን የሂሳብ ሰነድ አያያዝና አጠቃቀም ችግር ሲያስረዱም ድርጅቱ ባሉት 11 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ውስጥ በቂና ብቁ የሂሳብ ባለሙያዎች ባለመኖራቸው ሂሳቦቹ ወደ ዋናው መ/ቤት መጥተው ስለሚወራረዱ የቅርንጫፎቹ አቅም እስከሚገነባ ከሂሳብ አያያዝና ሰነድ አጠቃቀም ጋር የታዩት ችግሮች መከሰታቸውን ይህንንም ለመፍታት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ራሳቸውን ችለው የሂሳብ ስራዎችን እንዲሰሩ ለማድረግ መታቀዱን ተናገረዋል፡፡ በተጨማሪም ከሚመለከተቸው ኃላፊዎችና ሰራተኞች ጋር በተደረገ ውይይት ላይ በተሰጠው አቅጣጫ እንዲሁም በአካል ተሂዶ በተደረገው ክትትል መሰረት በተወሰዱ እርምጃዎች የሂሳብ ሰነዶች አጠቃቀም በአዳማና ጅግጅጋ ቅርንጫፎች እንደተስተካከለና ይሀም በውስጥ ኦዲት እንደተረጋገጠ ገልጸዋል፡፡ ከውስጥ ኦዲተሮች አለመኖር ጋር በተገናኘም በወቅቱ በዋናው መ/ቤት 1 የውስጥ ኦዲተር ብቻ የነበረ መሆኑና አሁን ተጨማሪ 4 የውስጥ ኦዲተሮች ተቀጥረው ስራው በአግባቡ እየተሰራና ክትትልም እተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከንብረት ማስወገድ ጋር በተያያዘም ኮምፒውተሮች እንዲወገዱ ለመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር መቅረቡና ሚኒስቴሩ በዝግጅት ላይ መሆኑ እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ንብረቶች እንዲወገዱ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበጀት አጠቃቀም ላይ የታየው ችግርም በጀት የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች ያልነበሩ በመሆኑ የተከሰተና አሁን ኤጀንሲው ለቦታው መደብ አስፈቅዶ ባለሙያዎች ተመድበው የበጀት ቁጥጥር ስራው እየተካሄደ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ ጥቅም ላይ ያልዋለ በጀት የተገኘውም ባለሁለት ፎቅ ህንጻ ለማስገንባት ለግንባታ ከተገመተው በጀት በላይ በጨረታ ወቅት የግንባታ ማከናወኛ ገንዘብ በመጠየቁ ምክንያት ግንባታው እንዲቀር በመደረጉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የሂሳብ ሪፖርትን በወቅቱ ካለመላካቸው ጋር ተያይዞ የበጀት አጠቃቀም ሁኔታን እያናበቡና እያተካከሉ ባለመስራት ችግሩ የመጣ መሆኑንና አሁን ግን በየወሩ ሪፖርት እንዲላክ በማድረግና በየሶስት ወሩ በሚኖር የጋራ የምክክር መድረክ ስራዎችን በማናበብ መሻሻል እየመጣ እንደሆነ ኃላፊዎቹ አብራርተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴውና የተፈጥሮ ሀብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተጨማሪ ማብራሪያ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ጠይቀው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡_DSC0042 with caption

ከዚህ በተጨማሪም የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ መስተካል በሚገቡ ጉዳዮች ላይ አስተያየቶችን ስጥተዋል፡፡ በዚህም ተቋሙ የፋይናንስና ንብረት አስተዳደሩንና የውስጥ ኦዲት አሰራሩን መፈተሸ እንዳለበት፣ ከሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ስለሚሰበሰበው ክፍያ ተመን በአግባቡ መመርመር እንደሚገባው፣ በተቋሙ የሚታዩ ችግሮ በድጋሚ እንዳይፈጸሙም ሆነ እንዳያገረሹ ድክመቶችን ማየት እንደሚያሻ፣ ከሆቴል አገልግሎት ግዥው ጋር ተያይዞም የመንግስት አአሰራርና መመሪያን መከተል እንደሚገባና ይህን አለማድረግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ኦዲቱ በናሙና ካያቸው የአሰራር ችግሮች በላይ አስፍቶ አሰራርን መፈተሸና ማስተካከል እንደሚያስፈልግ፣ ያልተሰበሰቡ ሂሳቦችን መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ  እንዲሁም በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ሂሳቦች ተወራርደው ተጠቃለው የሚመጡበትን አሰራር መቀየስ እንደሚያስፈልግ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስገንዝበዋል፡፡

ምክትል የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው ከሲቪል አቪየሽን የሚሰበሰበው ገቢ አሁንም ቢሆን በቀደመው አሰራር እየተሰራ መሆኑን በሂደት ላይ ያለው የ2008 በጀት አመት ኦዲት ሪፖርት ስለሚያሳይ ተጠንቶ ታሪፍ እንዲበጅለትና የመንግስት ገቢ እንዲሰበሰብ ማድረግ እንደሚገባ፣ የተሰብሳቢ ሂሳብ ጉዳይ በ2006 እና 2007 የኦዲት ሪፖርቶች አስተያየት ቢሰጥበትም ይብሱኑ በ2007 ከነበረበት 2.4 ሚልዮን ብር  በ2008 በጀት አመት ወደ 2.8 ሚልዮን ብር ከፍ እንዳለና ያልተሰበሰበ ሂሳብ በቆየ ቁጥር ወደ መሰረዝ ሊሄድ ስለሚችል ትኩረት ተሰጥቶት የመንግስት ገቢ እንዲሰበሰብ የውስጥ ኦዲቱ ትኩረት እንዲሰጥበት አሳስበዋል፡፡

_DSC0053 with captionምክትል ዋና ኦዲተሯ አክለውም በጣም ረጅም ጊዜ የሆናቸው ተከፋይ ሂሳቦች እንዲስተካከሉ  በ2006 እና 2007 የኦዲት ሪፖርቶች አስተያየት ቢሰጥባቸውም በ2008ም የሚታዩ በመሆኑ ይህንን ለማስተካከል ትኩረት መስጠት እንደሚገባና ከበጀት በላይ መጠቀምም እንደዚሁ እንዲታረም አስተያየት ቢሰጥበትም በ2008ም የታየ በመሆኑ በተደለደለው በጀት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በማጠቃለያ አስተያየታቸው ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ የመንግስት ግዥ ኤጀንሲና የመንግስት ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በኦዲት ግኝቱ ላይ ተመስርቶ በትብብርና በቅንጅት መስራታቸው ኦዲቱን መሰረት ያደረገ ክትትል እየተጠናከረ መሆኑን የሚያሳይ በጣም ጥሩ ስራ በመሆኑ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡  

በኤጀንሲው የኦዲት ግኝት በቸልታ ከሚታይበት አመለካከት ወጥቶ የኦዲት ግኝትን መሰረት የደረገ ስራ ለመስራት ጅምር ጥረት መኖሩ እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማጠናከር በይፋዊ ስብሰባው ላይ ተገኝቶ ለመማርና  ብዛት ያላቸው ኃላፊዎቹመጥተው መሳተፋቸው በመልካም ጎኑ እንደሚታይ ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ከሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ለአየር ንብረት ትንበያ የሚሰበስበው ገቢ መ/ቤቱ ነባር ከመሆኑና ገቢ አሰባሰቡም አለም አቀፋዊ አሰራር ያለው ከመሆኑ አንጻር ለምን እስካሁን ድረስ ለረጅም አመታት በተጠና የገቢ ማዕቀፍ አልተከናወነም የሚለው በትኩረት መጠናት እንዳለበት፣ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን አጥርቶ ለመሰብሰብ የተሄደበት ርቀት በአዎንታዊ ጎኑ ቢታይም የሰው ሀይል ማነስና የስራ ጫና የሚለውን እንደምክንያትነት ለመቀበል እንደማይቻል፣ ስለሆነም የቆዩም ሆኑ የቅርብ ተሰብሳቢ ሂሳቦች ተጣርተው በሙሉ ሊሰበሰቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሰብሳቢው አያይዘውም የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ቀንን በተመለከተ በአሉ እንደሚከበር ቀድሞ እየታወቀ በእቅድ ሳይመሩ በመጨረሻ ሰዓት አጣብቂኝ ውስጥ ገባሁ በሚል ሰበብ ከመንግስት መመሪያ ውጪ የሆቴል አገልግሎት ግዥ የተፈጸመበት ምክንያት ተቀባይነት የሌለውና የመ/ቤቱ የእቅድና የአመራር ችግር ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነ፣ ግዥውም በማኔጅመንት ውሳኔ በተገቢው ሁኔታ ሳይረጋገጥ፣ የግዥ አጥኚና አጽዳቂ አካላት ህጋዊ ሂደቱን ሳይከተሉ አየር ባየር በመዋዋል ወደ አስገዳጅ ግዥ የተኬደበት ሊሆን ስለሚችል በደንብ መረጋገጥ እንዳለበት ይህንን ጉዳይም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በግኝትነት ማለፍ ብቻ ሳይሆን መ/ቤቱ ይህን ለማጣራት የወሰደውን እርምጃ ማረጋገጥ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

  በስብሰባው መጨረሻ የኤጀንሲው ኃላፊዎች ከሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ገቢ የሚሰበሰብበት ታሪፍ ጉዳይ ከሃያ አመታት በፊትም ለመንግስት ቀርቦ ውሳኔ ያላገኘ በመሆኑ አሁን ኤጀንሲው የሚያደርገው ጥናት አጠናቆ ለመንግስት ሲያቀርብ ውሳኔ እንዲሰጠው ምክር ቤቱ እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *