የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽ/ቤት የላብራቶሪና መመርመሪያ መሳሪያዎችን አስመልክቶ በሚሰጠው የአክሬዲቴሽን አገልግሎት አተገባበር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሊኖር የሚገባው ቅንጅታዊ አሠራር ዝቅተኛ በመሆኑ በአገልግሎቱ አተገባበር ላይ ክፍተት መፈጠሩ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን ጽ/ቤት ላይ በ2012 በጀት ዓመት ያደረገውን የክዋኔ ኦዲት ግኝት አስመልክቶ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰሰባ ላይ ነው፡፡
ጽ/ቤቱ ከሚሰጠው የአክሬዲቴሽን አገልግሎት አንጻር በጥራት ቁጥጥር፣ በፈቃድ አሰጣጥና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ረገድ ቀጥተኛ ትስስር ካላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር ከፍተኛ ክፍተት ያለበት በመሆኑ በጽ/ቤቱ አገልግሎት አተገባበር ላይ ችግር መፍጠሩ ተመልክቷል፡፡
ተቋማት የአክሬዲቴሽን ምልክቶችን በመጠቀም ሂደት የሚያሳዩትን ተገቢ ያልሆነ አሠራርና ሌሎች የአክሬዲቴሽን አተገባበሮችን ለመቆጣጠር የሚያስችል በቂ የክትትል ሥርዓት ያልተዘረጋ መሆኑንና በዚህም በርካታ ክፍተቶች እንደታዩ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል በሜዲካልና በፍተሻ ላብራቶሪ መስፈርቶች መሠረት የንጽጽር ፍተሻ (Proficiency Test) የማይካሄድ መሆኑና ተቋማት በሚያቀርቧቸው በሁሉም የላብራቶሪ አገልግሎት ዓይነቶች ላይ አክሬዲትድ ያለመሆናቸውና በውጭ ሀገር አክሬዲቴሽን አለን በሚል ሽፋን አክሬዲትድ ሳይሆኑ እንደሆኑ አድርገው በሚዲያ ማስታወቂያ ጭምር በማስነገር የላብራቶሪ አገለግሎት የሚሰጡ ተቋማት መኖራቸውም ተነስቷል፡፡
ስለ አክሬዲቴሽን አገልግሎት አተገባበርና መስፈርቶች ለተለያዩ አካላት መሰጠት የሚገባው ስልጠና፣ ግንዛቤና ወቅታዊ መረጃ በቂ ያለመሆኑም በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡ ከዚህም ሌላ አንዳንድ የተስማሚነት ምዘና ባለሙያዎችም ፍተሻ በሚያደርጉባቸው የላብራቶሪ አገልግሎቶች ላይ ከግል ልምድና ስሜት ገለልተኛ የሆነ እና ስታንዳርዱን ብቻ መሰረት ያደረገ ግምገማ የማያደርጉ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ አርአያ ፍስሃ የኦዲት ግኝቶቹን አስመልክቶ በተቋሙ ላይ ለተነሱት ሀሳቦች በሰጡት ምላሽ የአክሬዲቴሽን አገልግሎት አሰጣጥ የተስማሚነት ምዘና እና የቁጥጥር (ሬጉላቶሪ) ስራ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በቅንጅት የሚከናወን መሆኑን ጠቁመው ተቋማት የአክሬዲቴሽን ምልክቶችን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ከፈቃደኝነት የዘለለ አስገዳጅ ህግ ያለመኖሩንና ምልክቶቹን በአግባቡ የመጠቀም ሥርዓት እንዲኖር በጽ/ቤቱ በኩል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
አቶ አርአያ አክለውም ጽ/ቤቱ አክሬዲትድ በሆኑ ተቋማት ላይ አተገባበሩን በተመለከተ ክትትል የሚያደርግ መሆኑንና ተቋማቱ አክሬዲትድ ባልሆኑባቸው ወሰኖች ስለሚሰጧቸው አገልግሎቶች ቁጥጥር የማድረግ ስራው የሌላ አካል መሆኑን ገልጸው ስልጠናዎችና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች እየተተገበሩ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
የአክሬዲቴሽን የምስክር ወረቀታቸውን በተገቢው ጊዜ ማሳደስ ያልቻሉ ተቋማትን የምስክር ወረቀት የመንጠቅ እርምጃ መወሰዱን ያነሱት ዳይሬክተሩ የላብራቶሪ ንጽጽራዊ ፍተሻ (PT-Proficiency Test) የሚያደርግ ተቋም በሀገር ውስጥ ያለመኖሩም በአክሬዲቴሽን አተገባበር ላይ ክፍተት መፍጠሩን አንስተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ጽ/ቤቱ ስለሚሰጠው የአክሬዲቴሽን አገልግሎት በቂ የሆነ መረጃና ግንዛቤ መስጠት የሚገባው መሆኑን ጠቅሰው በተለይም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር ሰፊ ክፍተት ያለበት በመሆኑ መጠናከር ያለበት መሆኑን አሳስበዋል፡፡
አክለውም በህግ ማዕቀፍ ክፍተት ሳቢያ የሚታዩ ችግሮችም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር ተገቢ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኦዲቱ የጽ/ቤቱን ስልጣንና ተግባር መሰረት አድርጎ የተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው በተቋሙ የአክሬዲቴሽን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሰፊ የሆነ የቅንጅታዊ አሠራር ክፍተት መኖሩን ጠቁመው አገልግሎቱን በአግባቡ ለመተግበር፣ ተገቢ አገልግሎት ለመስጠትና የቁጥጥርና የክትትል ስራውን ለማጠናከር አስገዳጅ የሆነ የአክሬዲቴሽን የህግ ማዕቀፍ መኖር እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡
በውጭ ሀገር የአክሬዲቴሽን አገልግሎት የሚያገኙ ተቋማትም በጽ/ቤቱ በመመዝገብ ሀገራዊ የአክሬዲቴሽን አሠራር ዕውቅና ማግኘት እንደሚገባቸው የጠቆሙት ም/ዋና ዳይሬክተሯ የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ለሚፈልጉ ተቋማትም ሆነ ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ሰፊና ጥልቀት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ ባቀረቡት የማጠቃለያ አስተያየት በጽ/ቤቱ የአክሬዲቴሽን አገልግሎት አሰጣጥና አተገባበር ላይ በሚታየው ክፍተት ምክንያት ጥራታቸውንና ደረጃቸውን ባልጠበቁ ምርቶችና አገልግሎቶች ለጉዳት ሊዳረግ የሚችለው ህብረተሰብ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
በግል ዘርፉ ብቻ ሳይሆን ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችንና አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ የመንግስት ተቋማትም ጭምር በአክሬዲቴሽን ስርዓት ውስጥ ማለፍ እንደሚገባቸው አስተያየታቸውን የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጽ/ቤቱ ተጠሪ የሆነለት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርም የአክሬዲቴሽን ትግበራን ሊያጠናክር የሚችል ጠንካራ የቁጥጥርና ፈቃድ አሰጣጥ አሠራር ሊኖረው እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም ጽ/ቤቱ እስከ ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እንዲያቀርብ እና በቀጣይም የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ዕውቅና ያላቸውንና የሌላቸውን ተቋማት በመለየት ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ፣ ከሚለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር እንዲያጠናክር አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ቁጥጥርና ፈቃድ አሰጣጥን አስመልክቶ የጽ/ቤቱን አገልግሎት አሰጣጥ የሚደግፍ አሠራር እንዲዘረጋና ተገቢ ክትትልና ድጋፍ እንዲደርግ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የቋሚ ኮሚቴ አባላትም አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጨምረው አሳስበዋል፡፡





