News

የቅድመ አዋጭነት ጥናት ባለመደረጉ በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ዘርፈ ብዙ ክፍተቶች መፈጠራቸው ተገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር እየተገነቡ ባሉ ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ በ2014/2015 በጀት ዓመት ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት አስመልክቶ ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በአስተዳደር መ/ቤቱ እየተገነቡ ባሉት የአዘዞ-ጎንደር እና የጎንጂ -ቆላላ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በተካሄደው ኦዲት መሠረት የመንገድ ፕሮጀክቶቹን ቅድመ አዋጭነት ጥናት ያለማድረግን ጨምሮ በወሰን ማስከበር፣ በካሳ ክፍያ፣ በፕሮጀክት መጓተት፣ በቅንጅታዊ አሠራር፣ በግንዛቤ ማስጨበጥ፣ በአካባቢ ህብረተሰብ ጤንነትና ደህንነት ጥበቃ፣ በክትትልና ቁጥጥር፣ በተቋራጮችና አማካሪዎች አሠራር፣ በግልጽነትና ተጠያቂነት አሠራር፣ በባለድርሻ አካላትና ህብረተሰብ ተሳትፎና ሌሎች አፈጻጸሞች ላይ ጉልህ ክፍተቶች መታየታቸው በውይይት መድረኩ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር መሀመድ አብዱራህማን (ኢንጂነር) ጨምሮ በመድረኩ የተገኙ የተቋሙ አመራሮች በተነሱት የኦዲት ግኝቶች ላይ ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም የኦዲት ግኝቶቹን ትክክለኛነት ማረጋገጫ በመስጠትና ከኦዲቱ በኋላ ፕሮጀክቶችን በቦታው ላይ ሆነው በቅርበት የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ 25 የፕሮጀክት አስተዳደር ጽ/ቤቶችን በመላው ሀገሪቱ ማቋቋምን ጨምሮ በሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች አሠራር ላይ የተተገበሩ የግኝት ማስተካከያዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም  መ/ቤታቸው በመንገድ ፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ላይ በታዩት ችግሮች ዙሪያ መሠረታዊ የሚባል ከፍተት ያለበት መሆኑን በዝርዝር ጠቅሰው ችግሮቹ ቴክኒካል ከሆኑ የበጀት አያያዝ እና አጠቃቀም፣ ከተጋነነ የካሳ ክፍያ ጥያቄ እንዲሁም በአካባቢው ካሉ የአስተዳደር አካላት ቅንጅታዊ አሠራሮችም ጋር የሚያያዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የአስተዳደር መ/ቤቱን አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ ተከትሎ አስተያየታቸውን የሰጡት የቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው የአብዛኛዎቹ ግኝቶች ዋንኛ መንስዔ የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ሲታሰቡ ቅድመ አዋጭነት ጥናት ያለመደረጉ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቶች በአፈጻጸም ምዕራፎች ተከፋፍለው መከናወን እንደሚገባቸው የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከወሰን ማስከበር፣ ከካሳ ክፍያ፣ ከተቋራጮች አሠራርና ብቃት፣ ከባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር እና ሌሎች ችግሮች ጋር የተያያዙትና ለፕሮጀክቶቹ መጓተትና ሌሎች ክፍተቶች መነሻ የሆነው ተገቢ የሆነና መሠረታዊ የአፈጻጸም ዕቅዶችን ያካተተ የአዋጭነት ጥናት ያለመደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ተቋሙ የበርካታ የሀገሪቱ ህብረተሰብ መሰረታዊ ጉዳይ የሆነውን የመንገድ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥና ከሌሎች ሴክተሮች አንጻር ከፍተኛ የሀገሪቱ በጀት የሚመደብለት እንደመሆኑ በግልጽነትና ተጠያቂነት አሠራር የተጠናከረ፣ በተገቢ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እና በዕቅድ የተመራ ውጤታማ  ስራ እንደሚጠበቅበት የቋሚ ኮሚተው አባላት አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የመሠረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ ወንድሙ ሴታ(ኢንጂነር) በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከሀገሪቱ አመታዊ በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወሰድና ከህዝብ ፍላጎት አንጻር ትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የሚገነባ እንደመሆኑ ክፍተቶቹን በማስወገድ ሀገሪቱ በዘርፉ ያስቀመጠችውን ዓላማ መሰረት አድርጎ ውጤታማ ስራ መስራት ይገባዋል ብለዋል፡፡

በመንገድ ፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ላይ የታዩት ችግሮች መንገዶቹ በሚሰሩበት አቅራቢያ የሚደረግ ክትትልና ቁጥጥር ያለመኖርን ጨምሮ ከወሰን ማስከበር፣ ከካሳ ክፍያ፣ ከህግ ማዕቀፍ፣ ከተቋራጮች ጤናማ የአሠራር ሥርዓት እና ከቅንጅታዊ አሠራር ጋር የተያያዙ መሆናቸውን አክለው የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በተለይም የካሳ ጥያቄን በተመለከተ በፌዴራል ደረጃ በሚሰሩ ፕሮጀክቶች ላይ የሚጠየቀው የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ በክልሎች በሚሰሩ ፕሮጀክቶች ከሚጠየቀው አንጻር በጣም የተጋነነ በመሆኑ መፍትሔ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ በሰጡት አስተያየት ከኦዲቱ በኋላ በተሰጠው የማስተካከያ አስተያየት መሠረት የተፈጸሙና ያልተፈጸሙ ተግባራት ተለይተው መቅረብ የሚገባቸው መሆኑን ጠቅሰው የአንድ ፕሮጀክት ስራ ከመጀመሩ በፊት የፋይናንስ፣ የአካባቢ ተጽእኖ፣ የማህበራዊ እና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮችን ያካተተ የአዋጭነት ጥናት ማድረግ በመመሪያ የተቀመጠ በመሆኑ ወደስራ ከመገባቱ በፊት ጥናቱ መተግበር ይገባዋል ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ላይ 13.6% የሚደርስ ተጨማሪ ወጪን ከማስከተል፣ ከፕሮጀክት ማጠናቀቂያ ጊዜ መጓተት፣ ከጥራት ክትትልና ቁጥጥር አፈጻጸም እና በአካባቢ ህበረተሰብ ደህንነትና ጤንነት ላይ ተጽእኖ ከማሳደር አንጻር ጉልህና መሰረታዊ ችግሮች መታየታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ክቡር ም/ዋና ኦዲተሩ አክለውም በቀጣይ ስራዎች ላይ በህግ ማዕቀፍ የታገዘ የቅንጅት ስራን በማጠናከር፣ የካሳ ክፍያን በወቅቱ በመክፈልና ለህብረተሰቡ በግልጽ በማሳወቅና ግንዛቤን በማስጨበጥ፣ የፕሮጀክቶችን ድህረ ብቃት ግምገማን በማድረግ፣ ተገቢ የክትትልና ቁጥጥር ስራን በማጠናከር፣ ለአካባቢ ደህንነት ትኩረት በመስጠት እና ሌሎች የኦዲት ግኝት ማስተካከያ አስተያየቶችን በስራ ላይ በማዋል በተመሳሳይ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ሊታዩ የሚችሉ ቸግሮችን መቅረፍ ይገባል ብለዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በመውይይት መድረኩ ማጠናቀቂያ ላይ በሰጡት አስተያየት የመንገድ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የሀገሪቱ በጀት የሚመደብላቸውና በአፈጻጸሞች ላይ በርካታ ቅሬታዎች የሚነሱባቸው እንደመሆናቸው በአስተዳደር መ/ቤቱ የተጀመሩ የሪፎርም ጥረቶችንና ከኦዲት በኋላ የተከናወኑ የማስተካከያ እርምጃዎችን በማጠናከር አሠራርን ማስተካከል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ዋነኛ የፕሮጀክቶቹ ችግሮች ምንጭ ወቅታዊ የአዋጭነት ጥናት ያለመደረጉ መሆኑን በድጋሜ በማንሳት ይህ ጥናት ሳይደረግ ማንኛውም ፕሮጀክት መጀመር የሌለበት መሆኑን የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ አስተዳደሩ ከመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ጋር ሊኖር የሚገባው ቅንጅታዊ አሠራር መጠናከር ያለበት መሆኑንና  በዕቅድ፣ በቅንጅታዊ አሠራር፣ በካሳ አከፋፈልና ግልጸኝነት እንዲሁም በደንብና መመሪያ አተገባበር እንዲሁም በሌሎች አፈጻጸሞች ረገድ ቀጣይ ስራዎች እንዲስተካከሉ አሳስበው የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም ደረጃ በሚመከለት በየሶስት ወሩ ሪፖርት እንዲቀርብና ፕሮጀክቶቹ የደረሱበት አፈጻጸም በቀጣይ ቋሚ ኮሚቴው በሚያደርገው የመስክ ምልከታ የሚረጋገጥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *