News

የስኳር ኮርፖሬሽኑና ፋብሪካዎቹ የመንግስትን እቅድና የህዝብን ፍላጎት በሚመልስ አግባብ በትኩረት ሊመሩና ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንና በስሩ በሚያስተዳድራቸው የተንዳሆ፣ የመተሀራ እና የወንጂ/ሸዋ የስኳር ፋብሪካዎች የስራ ኃላፊዎች ለስኳር ልማት ዘርፍ መንግስት በሰጠው ትኩረትና ህዝቡ ባለው የስኳር ፍላጎት ልክ እየተንቀሳቀሱ ባለመሆኑ መንግስት ከዘርፉ የሚጠብቀውን ውጤት በሚያስገኝና የህዝቡን ጥያቄ በሚመልስ አግባብ ስትራቴጂያዊ አመራር በመስጠት ዘርፉን መምራት እንዳለባቸው አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የተንዳሆ፣ የመተሀራ እና የወንጂ/ሸዋ የስኳር ፋብሪካዎች ከ2006 እስከ 2008 በጀት አመት አፈጻጸምና ውጤታማነት ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ባደረገው የክዋኔ ኦዲት ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት ታህሳስ 02/2010 ዓ.ም አድርጓል፡፡

በመድረኩ ላይ በሶስቱም የስኳር ፋብሪካዎች እንቅስቃሴ እንዲሁም በኮርፖሬሽኑ የክትትል የድጋፍና ቁጥጥር ስራ ላይ  ኦዲቱን መሰረት አድርጎ ዝርዝር ጥቄዎች የቀረቡ ሲሆን የፋብሪካዎቹ ዋና ስራ አስፈጻሚዎችና የኮርፖሬሽኑ የበላይ የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ አፈጻጸምን አስመልክቶ ዓመታዊ የግርድፍ መሬት፣ የውሃ ገብ መሬት ርክክብና የሸንኮራ አገዳ ተከላ እቅዶች አለመሳካታቸው፣ የፋብሪካው ግንባታና ተከላ በ6 ዓመት መዘግየቱ፣ የእርሻ ዘርፍ እቅድ አፈፃፀም (የሸንኮራ አገዳ የመስኖ ልማት፣ የመሬት ድልዳሎ) አነስተኛ መሆኑ፣ ለፋብሪካው በአማካሪነት ከተቀጠረው ድርጅት ጋር የተገባው ውል ለ7 አመታት መራዘሙና ይህም ወደ 9.5 ሚልየን ብር ጭማሪ (713.4%) እንዲከፈል ማድረጉ፣ ለ499 ቤቶች ግንባታ ከ300 በላይ ለሆኑ ተቋራጮች ካለውል ስራ መሰጠቱ  በኦዲት ግኝትነት ተነስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ዘመናዊ ማሽነሪዎች በብልሽትና በመለዋወጫ እጥረት አገልግሎት የማይሰጡ መሆናቸውና ይህም ለኪራይ ለሚወጣ ለተጨማሪ ወጪ ፋብሪካውን መዳረጉ፣ ከብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ለማሽነሪ ግዥ ብር 44 ሚሊዮን ውል ቢፈጸምም ከውሉ ጊዜ በላይ በአንድ ዓመት መዘግየቱ እንዲሁም ከአገልግሎት ውጪ የሆኑና ያልተወገዱ ቋሚ ንብረቶች መኖራቸው ተገልጿል፡፡

እንደዚሁም ለሸንኮራ አገዳ ልማት የቲሹ ካልቸርን ስራ ላይ ለማዋል ስለተመደበው በጀትና ስለወጣው ወጪ ማወቅ አለመቻሉ፣ ፋብሪካው ምርት ባለመጀመሩ በ2008 በጀት ዓመት የቆረጣ ጊዜ ያለፈበት 303.17 ሄክታር የሸንኮራ አገዳ እንዲገለበጥ መደረጉ እንዲሁም በአገዳ ዕድሜ እርጅና ምክንያት በ1,349.9 ሄክታር ላይ የተተከለ ሸንኮራ አገዳ ሙሉ በሙሉ መወገዱና ፋብሪካው አገዳ ተቀብሎ ባለመፍጨቱ 800 ሄክታር መሬት ዕድሜው ባለፈ የሸንኮራ አገዳ መሸፈኑ በኦዲት ግኝትነት ተጠቅሰዋል፡፡

በፋብሪካው የሰራተኞች መኖሪያ መንደር 18 አካባቢም የአካባቢውን ሙቀትና ንፋስ ለመቀነስ የሚያችል የዛፍ ሽፋን እንደሌለ ኦዲቱ አመልክቷል፡፡

በመተሀራ ስኳር ፋብሪካ ረገድ የኢታኖል ፕላንት ግንባታና ተከላ ጨረታ ሂደትን የሚያሳይ ሰነድ አለመገኘቱ፤ ለግንባታና ተከላ ከተመደበው መነሻ የኮንትራት ዋጋ በላይ በብልጫ ለተፈጸመው የብር 33,859,495.41 ክፍያ ምክንያቱን የሚገልጽ የውል ማስረጃ አለመቅረቡና ፕሮጀክቱም ከማጠናቀቂያ ጊዜው በ4 ወር መዘግየቱ፣ በመለዋወጫ እጦት ኢታኖል ለማምረት የሚያስፈልገውን የእንፋሎት ሀይል ማቅረብ ባለመቻሉ ከምርት ሊገኝ የሚቻል ከ68,6 ሚልየን ብር በላይ መታጣቱ እንዲሁም በግብዓትነት ሊውል የሚችል  ብር 39,193,770 የሚያወጣ ሞላሰስ መባከኑ ብሎም ብር 3,915,328.10 የሚያወጣ ከተሽከርካሪዎች ነዳጅ ጋር የሚቀላቀል 412,139.8 ሊትር ኢታኖልና ለተለያዩ የመጠጥ ኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት የሚሸጥ ብር 2,559,388.99 የሚያወጣ 176,631.4 ሊትር ረክቲፉይድ ስፕሪት አልኮል ባለመመረቱ በድምሩ ብር 6,474,717.09 ሀገሪቱን ማሳጣቱ ተገልጿል፡፡

በውል አፈጻጸምና ግዥ በኩል ከስኳር ኮርፖሬሽኑ ግዥ አፈፃፀም መመሪያ ውጪ ግዥ በመፈፀሙ ፋብሪካው ያልተገባ ተጨማሪ ወጪዎች እንዳወጣና በውል ያልታሰሩ ግዥዎችን እንደፈጸመም ተገልጾ በአብነት ለሥራ ላይ አደጋ መከላከያ አልባሳት ተጨማሪ ብር 168,834.89 ለሠራተኞች ዩኒፎርም ግዥ ደግሞ ብር 437,368.75 ተጨማሪ ወጪ ለሁለት አቅራቢዎች እንደከፈለ ተጠቅሷል፡፡

የእንፋሎት ሀይል ለማመንጨት የሚያስፈልገውን ውሃ እንዲያጣራ በብር 1,906,362 ለፋብሪካው ተገዝቶ ከህንድ የመጣና ሌሎች ልዩ ልዩ ክፍያዎች ተፈጽመውለት የተተከለ መሳሪያ ፋብሪካው ከሚጠቀምበት ነባር ቴክኖሎጂ ጋር ባለመግጠሙ ምክንያት ከሁለት ዓመታት በላይ አገልግሎት ሳይሰጥ መቀመጡን እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ2013/2014 በጀት ዓመት ብር 2,743,242.00 ለሚያወጡ ግዥዎች የክሌይም ጥያቄ በማቅረብ እ.ኤ.አ. እስከ 2015/2016 በተደረገ ጥረት ብር 480,533.67 ማስመለስ ቢቻልም ብር 2,262,708.33 ያልተመለሰ መሆኑን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

በንብረት አመዘጋገብና አያያዝ ረገድ በፋብሪካው እ.ኤ.አ. በ2012/2013 እና 2013/2014 በጀት ዓመት በዓመታዊ የንብረት ቆጠራ ወቅት በርካታ ንብረቶች ያልተገኙ በሚል በቋሚ ንብረት መዝገብ ላይ ቢመዘግብም ምንም የማስተካከያ እርምጃ አለመውሰዱ፣  በእርጅናና በተለያዩ ምክንያቶች ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ በርካታ የነባር የስኳር ፋብሪካዎች ቋሚ ንብረቶች አለመወገዳቸው፣  በተደረገው የነዳጅ ቆጠራ 3,224.86 ሊትር ፔትሮሊየም እና 8,304.95 ሊትር ዲዝል ከካርድ ባላንስ ጋር ሲነፃፀር በማነስ መገኘቱ እንደዚሁም በሁለት መርከብ ከውጭ ሀገር ተጭኖ ከመጣ ስኳር ውስጥ 3,777 ኩንታል የተበላሸ በመሆኑ ትክክለኛ ማስረጃ ባልተገኘለት መንገድ መቀበሩና ካሳ ያልተጠየቀበት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ረገድ ኮርፖሬሽኑ የወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ዲዛይንና ዝርዝር የኢንጂነሪንግ ፓኬጅ አቅርቦትን፣ ማንዋሎችንና የመለዋወጫ ስፔስፊኬሽኖችን በውሉ መሠረት ከተቋራጩ አለመረከቡ፣ የስኳር ፋብሪካ ማስፋፊያ የመነሻ ውል ስምምነት ላይ የፋብሪካው መጠናቀቂያ ጊዜ አለመገለጹ በተጨማሪም የፋብሪካ ግንባታና ተከላ ስራውን በአማካሪነት የተከታተለው ኩባንያ ውል ማጠናቀቂያ ጊዜ ለ8 ጊዜ እየተራዘመ ለ9 ዓመታት በመዘግየቱ ከመነሻ ኮንትራት ዋጋው በላይ ዩሮ 4,648,860 ተጨማሪ ክፍያ ለኩባንያው መከፈሉን ኦዲቱ አመልክቷል፡፡

ከዚህ ሌላም የሸንኮራ አገዳ እርሻ ልማት ለማከናወን የመስኖ ግድብና አውታር ግንባታ የወለንጪቲ ቦፋ መስኖ ፕሮጀክት በ3 ዓመት ለማጠናቀቅ ውል ቢገባም ለ2 ዓመት ከ2 ወር መዘግየቱን በተጨማሪም የግንባታው አማካሪ ሆኖ የሰራው የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የመነሻ ኮንትራት ውል ለ24 ወራት የሚያገለግልና እንደየአስፈላጊነቱ የሚታደስ ሆኖ የመነሻ ኮንትራት ውል ብር 17,427,728.99 የተፈረመ ቢሆንም ስራዎቹ በተቀመጠላቸው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸው ውሉ 4 ጊዜ የታደሰ በመሆኑ በድምሩ ብር 30,489,214 ከመነሻ ዋጋ ተጨማሪም ክፍያ መፈጸሙ ተገልጿል፡፡

ከእቅድ አፈጻጸም አኳያ ሲታይም በ2007 በጀት ዓመት የምርት ዘመን የሸንኮራ አገዳ ልማት መሬት ርክክብና ዝግጅት እቅድ አፈፃፀም አነስተኛ መሆኑ፣ በ2008 በጀት ዓመት የማሽነሪ አቅርቦት እጥረት መኖሩና ፋብሪካው በስሩ ከሚገኙት ድርጅት ከማሳ አገዳ የመቁረጥ አፈፃፀም አነስተኛ መሆኑ፤ ከባድ ጥገና እና ሰርቪስ ለማድረግ በታቀደው መሰረት በመለዋወጫ እጥረት ምክንያት አፈፃፀሙ አነስተኛ መሆኑ እንዲሁም አነስተኛ የፈረስ ጉልበት ያላቸው የጅንድር ትራክተሮች መለዋወጫ አለመቅረቡ እና የሸንኮራ አገዳ ፋብሪካ ማጓጓዣ ጋሪ እጥረት መኖሩ እንዲሁም ከ2006-2008 በጀት ዓመት በነበረው የፋብሪካው የስራ ሂደት ወቅት በእያንዳንዱ በጀት ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች ፋብሪካው በዕቅድ የተያዘለትን ምርት ማምረት ያልቻለ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህም ሌላ የመለዋወጫ ችግርን እንዲሁም ጂቡቲ ወደብ ተከማችተው የሚገኙ የፋብሪካ እቃዎችን በተመለከተ በፋብሪካው ለኮርፖሬሽኑ የቀረቡ የድጋፍ ጥያቄዎች አለመመለሳቸው፤ ከሞጆ ደረቅ ወደብ ለሚመጡ ዕቃዎች የገንዘብ ጥያቄን አስመልክቶ ብር 22,019,678.78 መከፈል ባለመቻሉ የመወረሻ ጊዜያቸው የተቃረበ 9 ዕቃዎችን በወቅቱ ባለማንሳት ለመጋዘን ኪራይ ብር 393,231.33 መከፈሉ ተመልክቷል፡፡

በንብረት አያያዝ በኩል እ.ኤ.አ በ2014/2015 በጀት ዓመት 124 ቀላል እና 41 ከባድ ተሽከርካሪዎች፤ እ.ኤ.አ በ2015/2016 በጀት ዓመት ደግሞ 172 ቀላልና 21 ከባድ ተሽከርካሪዎች በንብረት ቆጠራ ወቅት አለመገኘታቸው፣ የፋብሪካው የነዳጅ አጠቃቀም ከበጀት ሬት በላይ መሆኑን የውስጥ ኦዲት ሪፖርቱ ማሳየቱ እንዲሁም በእርጅናና በተለያዩ ምክንያቶች ከአገልግሎ ውጪ የሆኑ ቋሚ ንብረቶች አለመወገዳቸው በኦዲቱ ታውቋል፡፡

በአካባቢ ጥበቃ ረገድም በፋብሪካው የአገዳ አቅርቦት፣ በጥገና ጋራዥ እንዲሁም በአካባቢው በሚገኙት መንገዶች በሚነሳ አቧራ ብናኝ ሠራተኛው በጤና መታወክ ላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በኦዲቱ ለተመለከቱት ግኝቶች የየፋብሪካዎቹ የስራ ኃላፊዎች በዝርዝር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካን በተመለከተ የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ላይናዲስ በቀለ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ኦዲቱን መሰረት በማድረግ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የሰጣቸውን ማሻሻያ ሀሳቦች በጥልቀት በማየት እርምጃ በሚወሰድባቸው ጉዳዮች ላይ የድርጊት መርሀ ግብር በማዘጋጀት ለኮርፖሬሽኑ እንደተላኩና እየተሰራባቸው እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

ለሸንኮራ አገዳ ተከላ የግርድፍ መሬትና ውሃ ገብ መሬት ዝግጅት ስራን በተመለከተ ስራው ለውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጀት እንደተሰጠና ድርጅቱ በወቅቱ ስራውን አጠናቆ ባለማስረከቡ በስኳር ልማቱ ላይ ችግር እንደፈጠረና በቶሎ እንዲያስረክብ ግፊት ሲደረግ እንደቆየ አስረድተዋል፡፡ በፋብሪካው በኩልም በመለዋወጫዎች አለመኖር ሳቢያ ማሽነሪዎች በሙሉ አቅማቸው መስራት ባለመቻላቸው በሸንኮራ ልማት መሬት ዝግጅት ላይ ችግር መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡ በዚህም ለማልማት ከታቀደው 16ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 8 ሺህ ሄክታር ብቻ መዘጋጀቱን ጠቅሰው ይህንን ችግር ለመፍታት ተበላሽተው የቆሙ ማሽነሪዎችን በራስ አቅም በመጠገንና መለዋወጫዎቻቸውን በማፈላለግ በ2,700 ሄክታር መሬት ላይ አዲስ ተከላ መደረጉን እና ባጠቃላይ እነዚህን ማሽነሪዎች በመጠቀም በአሁኑ ወቅት በ10 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳ መትከል መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የፋብሪካው ግንባታ መዘግየቱንና የእርሻ ዘርፍ እቅድ አፈፃፀም መቀነሱን በተመለከተም በኮንትራክተሩና በንዑስ ኮንትራክተሩ አለመስማማት ስራው በ18 ወር እንደዘገየ በኋላም በተከላ ምዕራፍ ላይ የአዋሽ ወንዝ በመሙላቱ በጎርፍ ምክንያት ስራው የበለጠ እንደዘገየ አስታውሰው እ.ኤ.አ. በ2014 የመጀመሪያ ሙከራ ተደርጎ ስራ እንዲጀምር ተደርጎ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ተከላቸው ባላለቁ ፕላንቶችና ማሽነሪዎች ላይ የማሻሻያ ሥራ ሲሰራ መቆየቱንና በመሀል  ቆሻሻ ውሃ በጥቅም ላይ በመዋሉ በተርባይን ላይ ችግር መፍጠሩን በኋላም በድርቅ ምክንያት ስራው እንደቆመ   ኃፊው     አስታውሰዋል፡፡ ከድርቁ በተጨማሪም ማሳዎች በከብቶች ተጠቅተው ምርቱ መቀነሱን ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የቆሻሻ ማጣሪያ፣ የስኳር ማጠራቀሚያ መጋዘኖች ግንባታ፣ የእሳት አደጋ መከላከያ ወዘተ. ሥራዎች ላይ ያላለቁ ተግባራት ቢኖሩም የማሻሻያ ሥራዎችን በማከናወን ወደ ሥራ ለመግባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ቀሪ ሥራዎቹን ለማጠናቀቅም ኮንትራክተሩ ሥራውን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ እንዲያስረክብ ግፊት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለአማካሪ ድርጅት የተከፈለውን ተጨማሪ ክፍያ በተመለከተም አስቀድመው በጠቀሷቸው ምክንቶች ፋብሪካው በታቀደለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ስራውን ለሚከታተለው አማካሪ ድርጅት የተከፈለው ክፍያ መጨመሩን አስረድተዋል፡፡

የእርሻ ዘርፍ እቅድ አፈጻጸም አነስተኛነትን በተመለከተም ባለፈው ዓመት ወደ 4 ሺህ ሄክታር ለማልማት ታቅዶ 67% እንደለማና ዘንድሮም 6 ሺህ ሄክታር ለማልማት መታቀዱን ባጠቃላይም ወደ 10 ሺ ሄክታር ለማልማት እንደታቀደ ገልጸዋል፡፡

ከቤቶች ግንባታ ውል ጋር በተያያዘ ከቤቶች ልማት ጋር በውል እንደተሠራና ውሉም ለፌዴራል ዋና ኦዲተሮች የተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ማሽነሪዎችንና ተሽከርካሪዎችን በኪራይ መጠቀም ካስከተለው ተጨማሪ ወጪ ጋር ተያይዞም በርካታ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች በመለዋወጫ እጦት ቆመው እንደነበርና የአገዳ ተከላውን ለማሳለጥ ሲባል ወደ ኪራይ መገባቱን ተናግረዋል፡፡  ነገር ግን ቀደም ብሎ በጠቀሱት አግባብ የቆሙ ማሽነሪዎችንና ተሽከርካሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት መደረጉንና ሌሎች አማራጮች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ስራዎችን በራስ አቅም ለመሥራት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ሌላም ከብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የተገባው የግዥ ውል በአንድ ዓመት ዘግይቶ መፈፀሙን በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ ሥራውን በማዘግየቱ የተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መወገድ ሲገባቸው ያልተወገዱ ንብረቶችን አስመልክቶም በእርጅና ምክንያት የማይሠሩት በፋብሪካው ንብረት አስወጋጅ ኮሚቴ ቅደም ተከተል ተሰጥቷቸውና የማስወገጃ መርሃ ግብር ወጥቶላቸው እየተወገዱ እንደሆኑና እስካሁንም ወደ 5.2 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደተገኘባቸው ገልፀው በኦዲቱ ሳይወገዱ በግኝትነት የተገኙት እንደ ተሽከርካሪ ያሉ ንብረቶች በተቀመጠላቸው ቅደም ተከተል መሠረት በሂደት እንደሚወገዱ አስረድተዋል፡፡ ከዘመናዊ ማሽነሪዎች ብልሽት ጋር በተገናኘም ከኦዲቱ በኋላ ማሽነሪዎች ዕድሜያቸው ተራዝሞ የበለጠ ጥቅም እንዲሠጡ የንብረት አያያዝ አደረጃጀቱን በማስተካከል፣ የአሠራር ክለሳ በማድረግ፣ ቅድመ ጥገና በማከናወንና ቀደም ብለው የተገለፁትን በራስ አቅም የመጠገንና መለዋወጫ የማፈላለግ ዘዴዎችን በመጠቀም እየተሰራበት እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘም አካባቢው ድንጋያማና ዛፍ ለማብቀል የሚያስችል ለም አፈር ያልነበረው በመሆኑ 3,200 ኪዩቢክ ሜትር አፈር ከሸንኮራ ልማቶችና ከሌሎች አካባቢዎች በማምጣት ችግኝ የመትከል ስራ እንደተሰራ አስረድተዋል፡፡

የመተሐራ ስኳር ፋብሪካን አስመልክተው የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪኪያጅ አቶ አብዱልአዚዝ የሱፍ በሰጡት መልስ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተሰጠው የኦዲት አስተያየት መሠረት የማሻሻያ የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቷል፡፡

ዋና ስራ አስኪያጁ የኢታኖል ፕላንት ግንባታና ተከላ ጨረታ ሰነድ አለመገኘትን አስመልክቶ ግንባታው በወቅቱ በፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክት ስር እንደነበረና ፋብሪካው ሲቋቋም ፕሮጀክቱ ወደ ከሰም ስኳር ልማት ሲሄድ መረጃውም በሙሉ አብሮ እንደሄደ ሆኖም በመተሀራ ስኳር ፋብሪካ የተገኘው መረጃ ለፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ኦዲተሮች እንደቀረቡ፣ ጨረታውም በአግባቡ እንደተከናወነና በዚህ ምክንያት ፋብሪካው ያጣው ምንም ነገር እንደሌለ ለዚህም በቂ ማስረጃ እንዳለ ገልፀዋል፡፡

ከኢታኖል ፕላንት ግንባታና ተከላ ጋር በተገናኘ ተጨማሪ ክፍያ በአማካሪና በቀጣሪ ድርጅት መካከል የተፈፀመበት የውል ማስረጃ አለመቅረቡንና ግንባታው በ4 ወራት መዘግየቱን በተመለከተ ግንባታው እንዳልዘገየ እና ለዚህም የፕሮጀክት ማጠቃለያ እንዳለ ገልፀዋል፡፡ ለኢታኖል ፕላንት አስፈላጊ የሆነውን እንፋሎት ማምረት ባለመቻሉ ስለታጣው ጥቅም በተመለከተም የኦዲት ግኝቱ ላይ የተገለፀው ግነት እንዳለበትና የምርት ስሌቱ በ95% የማምረት ብቃት (Efficiency) ምጣኔ የተሰላ እና ይህም በተግባር ሊሆን የማይችል ብለው ተከራክረዋል፡፡ ከዚህ ውጪም ፋብሪካው ለእንፋሎት ማመንጫ የሚጠቀመውን አሮጌ ቦይለር ለማሻሻል ብሎም በአዲስ ለመተካት ጥረት እየተደረገ እንዳለና ፋብሪካው የቆየ በመሆኑ የእንፋሎት ብክነት እንዳለበት ገልፀው በሚቀጥለው ዓመት የኢታኖል ማምረቻው ውጤታማ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ከጨረታ ግዥ አፈፃፀም ጋር ተያይዞ  አላግባብ በተጨማሪነት ስለተከፈለው ክፍያም የግዥ ሥራውን የሚሠሩት ሠራተኛ በህግ ጥላ ስር ስለነበሩ ከመጀመሪያው አቅራቢ ለመግዛት ጊዜው በማለፉ እና ለማቅረብም ፈቃደኛ ባለመሆኑ እንዲሁም በሠራተኛው የሥራ ደህንነት ላይ ችግር እንዳይፈጠር በሚል ሁለተኛ ከወጣው አቅራቢ እንዲገዛ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ከውጭ ሀገር ተገዝቶ በፋብሪካው መገጠም ያልቻለውን ማሸነሪ በተመለከተ ማሽኑ በመተሐራ ካለው ማሽነሪ ጋር ቴክኒካል በሆነ ምክንያት ባለመጣጣሙ በተፈጠረ ችግር መሆኑንና ሌሎች የስኳር ፋብሪካዎች እንዲጠቀሙበት በሚል የከሰም ስኳር ፋብሪካ እንዲጠቀምበት ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከፋብሪካው ንብረት አመዘጋገብና አያያዝ ስርዐት ጋር በተያያዘ ያሉት ንብረቶች በአግባቡ ያልተቆጠሩበት ሁኔታ እንዳለና በቀጣይ እንደሚስተካከል ገልፀው በንብረት ማስወገድ በኩል 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ስክራፕና ሌሎች የሚወገዱ ንብረቶችን ጨምሮ በተደረገ ሽያጭ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱን እንዲሁም 24 ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን ለማስወገድ አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ እየተሟላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡   ከነዳጅ ቆጠራ ጋር ተያይዞ የደረሰው ጉድለትን አስመልክቶ ነዳጅ ይጠራቀምበት የነበረው አሮጌ ታንከር ከመሬት ሲወጣ በትነት መልክ በመቀነሱ እንዲሁም ታንከሩ የሚያፈስ በመሆኑ ልዩነቱ መጥቷል ብለው  እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡

ዋና ስራ አስኪጁ ትክክለኛ ማስረጃ ሳይቀርብለት ስለተወገደው የተበላሸ ስኳር ሲናገሩም አስወጋጅ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስኳሩ ተቀብሯል ብለዋል፡፡

በወንጂ ስኳር ፋብሪካ የኦዲት ግኝት ላይ የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቱሉ ለማ ምላሽ ሲሰጡ የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ የድርጊት መርሃ ግብር በማዘጋጀት ለስኳር ኮርፖሬሽን እንደተላከ አስረድተዋል፡፡

የፋብሪካ ግንባታ ዲዛይንና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች አለመረከብን በተመለከተ እ.ኤ.አ. በ2008 የዲዛይን ግምገማ ተካሂዶ እንደነበረና ፋብሪካው ባሉት 13 ፓኬጆች ላይ የዲዛይንና የማንዋል ርክክብ ቀደሞ ተጀምሮ እንደነበረ አስታውሰው ብዙ በመሆኑ ምክንያት አለመጠናቀቁንና ቀሪዎቹን ለመረከብ ኮንትራክተሮቹ ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በፕሮጀክት መጓተት ምክንያት ለአማካሪ ድርጅት ተጨማሪ ገንዘብ መክፈልን በተመለከተ ፋብሪካው 13 ፓኬጆች እንደነበሩትና አንድ ኮንትራክተር 3 ፓኬጆችን ከመያዙ በስተቀር ሌሎቹ ፓኬጆች በተለያዩ ኮንትራክተሮች የተያዙ እንደነበሩ በማስታወስ የአንዱ ፓኬጅ መዘግየት ሌሎቹን የሚያዘገይ በመሆኑ መጓተት መፈጠሩን ገልፀው ለፕሮጀክት መጓተት የሚከፈል የዋጋ ማሻሻያ ባይኖርም ስራው በመዘግየቱ ግን ለአማካሪ ድርጅቱ ተጨማሪ 4.6 ሚሊዮን ዩሮ እንደተከፈለ ከዚህ ውስጥም ሁሉም ስራ ባለመጠናቀቁ በትክክል የተከፈለው 2 ሚሊዮን ዩሮ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ከመስኖ ግድብና አውታር ግንባታ የወለንጪቲ ቦፋ መስኖ ፕሮጀክት መዘግየትና ተጨማሪ ወጪ መውጣት ጋር በተያያዘም ከመሬት ዝግጅት ጋር በተገናኘ  የውል ጊዜው በመራዘሙ ለውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ተጨማሪ ክፍያ መከፈሉን ገልፀዋል፡፡

ከዕቅድ አፈፃፀም አነስተኛነት ጋር በተያያዘ ማሽኖችን ጠግኖ ወደ ስራ አለመግባት እና የማሽነሪ መለዋወጫ ችግር እንዳለ ለዚህም የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር እንደተፈጠረ ገልጸው በራስ አቅም ሞዲፌኬሽን በመስራት ማሽነሪዎቹን ለማሰራት ጥረት እየተደረገ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

በመለዋወጫ እጥረት ምክንያት የእቅድ አፈፃፀም አነስተኛ መሆኑን በተመለከተ ቀደም ብለው በገለጹት ምክንያት የተፈጠረ እንደሆነና አፈፃፀሙን ለማሳደግ ቀደም ብለው የተጠቀሱትን ስልቶች በመጠቀም የሠራተኛውን ተነሳሽነት በማሳደግ ምርትን ለመጨመር እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በጅቡቲና በሞጆ ወደቦች ርክክብ ያልተፈጸመላቸውን እቃዎች አስመልክቶ ስለተፈጠረው ችግር ሲገልጹም ንብረቶቹን ከወደብ ለመረከብ ኮርፖሬሽኑ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ምላሽ ለመስጠት ባለመቻሉ እንደተፈጠረ ገልጸው ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር በመፃፃፍ ከወደቡ እንዲወጡ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ሌላም እቃውን ከወደቡ ተረክቦ ማምጣት ያለበት ኮንትራክተር ይህንን ማድረግ ባለመቻሉ ፋብሪካው በራሱ ወጪ እቃውን ማምጣቱንና ይህንንም ለማድረግ ያወጣውን ወጪም ለኮንትራክተሩ ተከፋይ ከሆነ ገንዘብ ላይ ቀንሶ ማስቀረቱንና ገቢ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

ከንብረት አስተዳደር ጋር ተያይዘው በተገኙት ግኝቶች ዙሪያም ችግሩ የተፈጠረው በስክራፕነት የተወገዱ፣ በሽያጭና ለጥገና የወጡ እንዲሁም በእርጅና ምክንያት የተከማቹ ንብረቶችን አንድ ላይ ባለመቁጠር መሆኑን ጠቅሰው የሁሉም ንብረቶች ማስረጃ እንደሚገኝና አንድም የጠፋ ንብረት እንደሌለ ገልፀዋል፡፡

ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ አቧራ እያስከተለ ያለው መንገድ በማሳ መሀከል የሚገኝ በመሆኑና ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ ጥርጊያ መንገድ በመሆኑ በአስፋልት ማንጠፍ እንደማይቻል ገልጸው የአቧራ ብናኙን ለመከላከል በየወቅቱ ገረጋንቲ የማልበስ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በአጠቃላይ በሶስቱም የስኳር ፋብሪካዎች ላይ ከሚያስተዳድረው ሀብትና ንብረት እንዲሁም ከተጣለበት ሀገራዊ ኃላፊነት አኳያ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን በመለየትና የመከላከያ ስልቶችን በማስቀመጥ የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ወጪ ቆጣቢ እና ውጤታማ እያደረጉ በመምራት በኩል ያለው ቁርጠኝነትና ዝግጁነት ምን እነደሚመስል ብሎም እስካሁን  ከመንግስት ህግና ደንብ እንዲሁም መመሪያዎች ውጭ በመስራት ለተፈጠሩት ችግሮች ማስተካከያ ከመውሰድና የህግ ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አኳያ ያከናወናቸው ስራዎች ምን እንደሆኑ ተጠይቋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በዛብህ ገብረየሱስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑን ቀጣይ እቅድ በተመለከተ ፋብሪካዎቹን የተመለከቱ አንዳንድ ችግሮች የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከመቋቋሙ አስቀድመው የተፈጠሩ ቢሆኑም ችግሮቹ ስር በሰደዱበት ልክ ለማስተካከል እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው አብዛኛዎቹን ጉዳዮች ወደ ህጋዊ ስርዓት መመለስ እንደሚያስፈልግና ለዚህም በዋነኝነት የአሰራር ስርዐት ማሻሻያ ፓኬጅ ቀረጾ መተግበር አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ከመንግሥት ግዥ ጋር በተጣጣመ መልኩ የኮርፖሬሽኑንና የፋብሪካዎቹን የግዥ ስርዐት መመሪያ የማዘጋጀት፣ ተገቢው የሥልጣን ውክልና እንዲኖር የማድረግ፤ የመልካም አስተዳደር እና የውስጥ ኦዲት ክፍሎችን የማቋቋም እንዲሁም የቁጥጥር /ሱፐርቪዥን/ ቡድኖች አሰራር የመዘርጋት ስራ እንደተሰራ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ሌላም የፋይናንስ ማሻሻያ ፓኬጅ በመተግበር ወደ ኋላ የ4 ዓመታት ሂሳብ ተጠናቆ ለኦዲት እንደቀረበና የፋይናንስ ማሻሻያ ፓኬጁን ለመደገፍ የተሰሩ ስራዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ተግባራት ውስጥ የፋብሪካዎችን ሂሳብ ወደ ተጠቃለለ አሰራር እንዲመጣ የማድረግ፣ የአደረጃጀትና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን የመሥራት ፣ የሀብት አጠቃቀምን ወጪ ቅነሳ ፓኬጅ በመተግበር ከካይዘን አሰራር ጋር ሥራዎችን የማያያዝ፣ የሀብትና ንብረት አስተዳደር ማሻሻያ ሥርዓትን በመተግበር ንብረቶችን በአግባቡ የመመዝገብና ማሽነሪዎችን ጭምር እያዟዟሩና አንድ ተቋም ላይ በትርፍነት ያሉ ንብረቶችን ወደ ሌላ ተቋም ሄደው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የባለድርሻ አካላት የትብብር ሥራን የሚያጠናክርና ችግሮች በጋራ የሚፈቱበት አሰራር እንደተፈጠረና ለፋብሪካዎቹ ስታንዳርድ ኦፐሬሽን ፕሮሲጀር (standared operation procedure ) እንደተዘጋጀም አክለው ተናግረዋል፡፡

ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው ከንብረት አያያዝ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ንብረቶች በባንክ ማስያዣነት ተይዘው ያሉ በመሆኑ ማስወገድ እንዳልተቻለና አንዳንድ ማሽነሪዎችም በጣም የቆዩ በመሆናቸው መለዋወጫ እንዳልተገኘላቸው አስረድተዋል፡፡

በፋብሪካዎቹና በኮርፖሬሽኑ የበላይ ኃላፊዎች በተሰጡት ምላሾችና በኦዲት ግኝቶቹ ዙርያ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱና በመድረኩ ላይ የነበሩ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተጨማሪ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ  ኮሚቴ  አባላት  ከፌዴራል  ዋና  ኦዲተር    መ/ቤት ጋር በችግሮች ዙሪያ ያለመተማመንና ነገሮችን ወደ ሌላ አካል የመግፋት ሁኔታ በፋብሪካዎቹ አመራር ላይ እንደሚታይ እንደዚሁም የኦዲት ግኝቶቹ ላነሱት የህዝብ ጥያቄ ለሆነው ለዚህ ትልቅ ጉዳይ በቂ ትኩረት ያልሰጠ የሚመስል የተዝናና ስሜት እንደሚታይባቸው በመተቸት የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በዚህ ዓመት በ10 ሺ ሄክታር መሬት ላይ እያለማ እንዳለ የገለጸው ንሸንኮራ አገዳ ወደ ስኳር ምርት መቀየር ስለመቻሉ እና እንደ በፊቱ ሁሉ የማይወገድ ስለመሆኑ እንዲሁም ወደ ሀገር ገብቶ ተቀበረ የተባለውን ስኳር ጥራት ቀድሞውኑ ማጣራት ስላልተቻለበት፣ ከተበላሸም ካሳ ስላልተጠየቀበት ስለአወጋገዱም ለፌዴራል ዋና ኦዲተር    መ/ቤት ማስረጃ ማቅረብ ስላልተቻለበት ምክንያት እንዲገለጽ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን 10 አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ለማካሄድ ቢታቀድም ለአዲሱቹ መሪ ይሆናሉ የተባሉት ነባር የስኳር ፋብሪካዎች የቆሙበት፣ አዲስ የተቋቋሙትም ማምረት ተስኗቸው የደረሰ ሸንኮራ አገዳ የሚያስወግዱበት ሁኔታ እንዳለ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ጠቅሰው ወደ ሌሎቹ አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ለመግባት ምን እንደታቀደ እንዲገለጽ ጠይቀዋል፡፡

የወንጂ ስኳር ፋብሪካ በስክራፕነት የተወገዱ፣ በሽያጭና በጥገና ላይ የነበሩ ንብረቶች በንብረት ቆጠራ ወቅት አልተቆጠሩም በሚል የሰጠው ምላሽ ተገቢ አለመሆኑና ማንኛውም ንብረት በየትኛውም መልኩ ሲወጣ እንዴት ካለማስረጃ ሊወጣ እንደሚችልና የንብረት ቆጣሪ ቡድን አባላትም የተቋሙ ሰራተኞች ሆነው ሳለ እንዴት ስለንብረቶቹ መገኛ መረጃ ላይኖራቸው እንደቻለ እንዲብራራ ጠይቀዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑና የስኳር ፋብሪካዎቹ አመራሮችም የስኳር ፋብሪካዎቹ ግንባታ ለምን ለዓመታት ተጓተተ የሚለውን ጥያቄ በትክክል እንዳልመለሱም ጠቅሰው ከአፈጻጸም ዝቅተኛነት ጋር ተያይዞ ባንድ በኩል የመለዋወጫ ችግር አለብኝ በሌላ በኩል ደግሞ ከወደብ መረከብ ያልቻልኩት ንብረት አለ የሚል የተዘበራረቀ ምላሽ የሚሰጥበት ምክንያት ምን እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡

ተቋማቱ ጤናማ ናቸው ወይስ የታመሙ፤ በህይወት አሉስ በሚል የጠየቁት የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ለአማካሪ ድርጅቱ የግንባታ ጊዜው በመራዘሙ ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፈለው ተደረገ የሚለው ምላሽ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸው ፋብሪካዎቹ ግንባታቸው በቆየ ቁጥር የፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ገንዘባቸው እያደገ በመምጣቱ ሁኔታው አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል በበኩላቸው የተቋማቱ ችግር ከውል ስምምነትና ከክትትልና ቁጥጥር ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ አንድ ዓመት አዘግይቶ እንዳስረከበው የተገለጸው ማሽነሪ መዘግየቱ ብቻ ሳይሆን መስራቱም መጣራት እንዳለበት፣ በመተሐራ ስኳር ፋብሪካም ለኢታኖል ፕላንት ፕሮጀክት በተጨማሪ የወጣው ብር 33.8 ሚሊዮን የተከፈለበት ምክንያት መገለጽ እንዳለበት፣ በጨረታ አሸናፊ ከሆነው አቅራቢ ድርጅት ውጪ በውድድር ሁለተኛ ከወጡት አቅራቢዎች ግዥ የተፈፀመበት ምክንያት ከመልካም አስተዳደር አኳያ ሊፈተሽ እንደሚገባው፣ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ቢባልም በስራ ላይ ያለው ነባሩ ፋብሪካ እንጂ አዲሱ እንዳልሆነ፣ በስክራፕነት ተሰጡ የተባሉት ንብረቶች ማስረጃ አለመቅረቡ አጠያያቂ መሆኑንና ንብረቶቹ እንደውም ጭራሽኑ ላይኖሩ እንደሚችሉ ገልጸው ፋብሪካዎቹ አዘጋጅተው ለኮርፖሬሽኑ የላኩትን የማሻሻያ የድርጊት መርሃ ግብር ኮርፖሬሽኑ ወደ ፌዴራል ዋና ኦዲተር ያልላከበት ምክንያት ምን እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡ የመንግሥት ልማት ድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የኦዲት ሪፖርቱን መሠረት አድርጎ የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን እንደሚያጠናክርም አክለው ገልፃዋል፡፡

በመድረኩ የመንግሥት ንብረት ግዥና ማስወገድ አገልግሎትን ወክለው የተገኙት የስራ ኃላፊ  በወንጂ፣ ተንዳሆ፣ ከሰም፣ ፊንጫና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች ላይ ተከማችቶ ስላለው ስክራፕ መ/ቤታቸው እንዳስጠናና ወንጂ/ሸዋ፣ተንዳሆና መተሀራ  ላይ የተወሰነ ንብረት እንደተወገደ ገልፀው በሌሎቹ ላይ ግን ለኮርፖሬሽኑ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዳልተሰጠ ገልፀዋል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴና ከባለድርሻ አካላት በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወዮ ሮባ በሰጡት ምላሽ የኦዲት ማሻሻያ መርሀ ግብሩ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር    መ/ቤት በኮርፖሬሽኑ በኩል መላኩንና ያልደረሰበት ምክንያት እንደሚጣራ ገልፀዋል፡፡

ተንዳሆ ላይ የተተከለውን ሽንኮራ አገዳ በተመለከተ ዘንድሮ አገዳው ተቆርጦ ወደ ምርት እንደሚገባና የሚወገድ አገዳ እንደማይኖር ገልፀዋል፡፡ ፋብሪካዎችን ከማጠናከር አንፃር የመተሀራ ስኳር ፋብሪካን አቅርቦትና አሰራርን ለማሻሻል፣ አቅሙን በማሳደግ ላይ እየተሰራ እንዳለና የፋብሪካውን እንቅስቃሴ የተሟላ ለማድረግና የአገዳ ተከላውን ካለበት ችግር ለማውጣት ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ እንዲሰራ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለው የውጭ ምንዛሪ ችግር ብቻ ሳይሆን የእቅድም ጭምር በመሆኑ ይህንን በአግባቡ የሚያከናውን ቡድን በዋና መ/ቤት ደረጃ መቋቋሙን የገለፁት ኃላፊው በመጋዘን ያሉትን መለዋወጫዎች ለይቶ ለማወቅ ካለፈው አመት ጀምሮ የማጣራት ስራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ አመራሩ ራሱን እንዲፈትሽ በማድረግ በኩል ስራ መሰራቱንና ይህን ቀጣይነት ያለው ማድረግ እንደሚገባ ገልፀው የተጠያቂነት ስርዓቱን ለማጠናከርም በተቻለ አቅም በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ተቋማቱ ጤነኛ ወይስ የታመሙ ናቸው ለሚለው ጥያቄ አሁን በዘርፉ ያሉት ችግሮች ሲታዩ ጤነኛ ናቸው ለማለት ባይቻልም ራስን ከችግር አውጥቶ ለመሻሻል የሚደረገውን ጥረት በማየት የታመሙ ናቸው ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ ተቋማቱም በህይወት ያሉ እንደሆኑና ለዚህም ቀድሞ በየዓመቱ ወደ 3 ሚሊየን ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ ስኳር የሚገባበትን ሁኔታ በመቀነስ ወደ 700 ሺህ ኩንታል እንዲደርስ ማድረጋቸውን እንደማሳያ ጠቅሰው በየወቅቱ በተፈጠሩ ተፈጥሯዊና ሌሎች ችግሮች ምክንያት ግን አሁንም ስኳር ወደ ሀገር ለማስገባት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ልማት ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ አብርሀም ደምሴ በበኩላቸው ለቀረቡት ጥያቄዎች በሰጡት መልስ በአሁኑ ወቅት ስላሉት የስኳር ፕሮጀክቶችና መገኛ ሁኔታና በቀጣይ እቅዶች ላይ ገለፃ አድርገዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በወንጂ ስኳር ፋብሪካ በቆጠራ ወቅት ያልተገኙ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ በመረጃ አያያዝ ችግር ምከንያት በኦዲት ወቅት አለመቅረቡን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ስላሉበት ሁኔታ ዘርዝረዋል፡፡

ለአማካሪ ድርጅት በተጨማሪ የተከፈለን ክፍያ በተመለተም በግንባታ አለመጠናቀቅ ምክንያት መከሰቱንና የግንባታዎችን መጓተትን ምክንያት ለማጣራት ግላዊ ግምገማ መደረጉንና ጉዳዩ በኮንትራት አስተዳደር ፓኬጅ በዝርዝር መታየቱን አስረድተዋል፡፡ የኢታኖል በአግባቡ አለመመረትን በተመለከተም ምርቱ በቦይለር የእንፋሎት ማምረት አቅም ላይ የተወሰነ በመሆኑ ለስኳር ምርት ቅድሚያ በመስጠት የኢታኖል ምርት እንዲዘገይ እንደተደረገና በታንከር የተከማቸውን ሞላሰስ በመጠቀም ክረምት ላይ ቦይለሩን ለኢታኖል ማምረቻነት የመጠቀም አሰራር እየተተገበረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፋይናንስ ማሻሻያ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሳ ዘይኑ ወደ ሀገር ገብቶ የተወገደውን ስኳር በተመለከተ ስኳሩ በመርከብ ላይ እንደተበላሸና በኢንሹራንስ በኩል ካሳ እንደተጠየቀበት አስረድተው ስኳሩ ለምግብነት ሊውል እንደማይችል በላብራቶሪ ምርመራ በመረጋገጡ ከሚመለከተው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን መ/ቤት በተሰጠ መመሪያ መሰረት ድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል በማይችልበት መልኩ ባለሙያዎችና የየክፍሉ ተወካዮች ባሉበት በመቅበር እንደተወገደ አስረድተዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት የተቋማቱ አመራር ከሚታይበት ተረጋግቶ የመኖር ስሜት ወጥቶ የህዝቡን ጩኸት ያዳመጠ ምላሽ የመስጠት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት፣ በአሰራር ላይ ያሉ ችግሮችን የመፍታትና አስፈላጊ መረጃዎችን የመያዝ ኃላፊነት ከአመራሩ እንደሚጠበቅ፣ ኦዲት የችግር መፍቻ አጋዥ መሳሪያ ነው የሚለውን አመለካከት በመያዝ ችግሮችን በደንብ ለይቶ መፍትሄ በማበጀት ላይ መሥራት እንዳለበት፣ በቆጠራ ወቅት ንብረት ጠፋ የሚባልበት የንብረት አስተዳደር ስርዓት መስተካከል እንዳለበትና መተሐራ ስኳር ፋብሪካ ላይ የማያገለግሉ ንብረቶችን ለማስወገድ የተጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን በበኩላቸው በተለይ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ ለጨረታ ህጋዊ አሰራር ትኩረት መስጠት እንደነበረበትና ለሰራተኛው ምቹ አረንጓዴ አካባቢ ለመፍጠር በሁለቱ ፋብሪካዎች የተሰራው ስራ በበጎ እንደሚታይ ገልፀዋል፡፡          ስለተቀበረው ስኳር በተሰጠው ምላሽ ላይም ስኳሩ ተቀበረ ከተባለ ስለመቀበሩ ማስረጃ ለዋና አዲተር መ/ቤት ያልቀረበበት ምክንያት አሁንም በቂ ማብራሪያ እንዳልተሰጠበት ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት አስተያየት በማስፋፊያ ፕሮጀክቶቹም ሆነ በፋብሪካዎቹ ግንባታ ላይ ወደ ጨረታ ሲገባም ሆነ ውል ሲሰጥ የተሟላ ጥናት አለመኖሩ የችግሮቹ መንስኤ ነው ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት የስኳር ፋብሪካው ግንባታ ለዘጠኝ ዓመት እንዲጓተት ያደረጉት አካላት ባደረሱት ጉዳት መንግስት ተጨማሪ ወጪ ማውጣቱን፣ ህብረተሰቡ ማግኘት የነበረበትን አገልግሎት አለማግኘቱን እንዲሁም በመንግስት ላይም የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንዲነሳ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው እነዚህ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ተቋራጮችን በወቅቱ ስራቸውን ጨርሰው ካላስረከቡ የሚገደዱበት አሰራር መፍጠር እንደሚገባና ለዚህም በውል ዝግጅት ወቅት ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ጋር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ከአገዳ ተከላ ጋር በተያያዘ ከተከላው ይልቅ ማስወገዱ የበለጠ ወጪ እያስወጣ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፤ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ የስራ ላይ አደጋ መከላከያና የሰራተኛ ዩኒፎርም የግዥ ሂደትን የሚያሳይ ማስረጃ ካለው አስቀድሞ ማቅረብ ይግባው እንደነበረ ከኢታኖል ምርት ጋር በተያያዘ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ስሌት የተጋነነ ነው ለተባለውም ስሌቱ ፋብሪካው በሰጠው መረጃ መሠረት እንደተከናወነ፣ በማስረጃ ላይ ተመስርተው የተሰጡ አስተያየቶችን አምኖ መቀበል እንደሚገባ፣ የንብረት አያያዝ ስርዓቱን ዘመናዊ የማድረግ ጉዳይ በጥብቅ ሊታይ እንደሚያሻ እንዲሁም የቆሸሸ ውሀ በመጠቀም በተንዳሆ የስኳር ፋብሪካ ተርባይን ላይ ለደረሰው ጉዳት የሚመለከተው አካል መጠየቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በማጠቃለያ አስተያየታቸው ተቋማቱ የተገኘባቸው የኦዲት ግኝት የጎላ ችግር ያለበት ወይም ተቀባይነት የሚያሣጣ አስተያየት የተሰጠበት በመሆኑ ለስራቸው ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውና የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ በማሻሻያ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች በኦዲት ግኝቱ ላይ ከተሠጡ ምላሽ ውስጥ በንብረት ማስወገድ በኩል ከተደረገው ጥረት በስተቀር ይህ ነው የሚባል የተወሰደ የማሻሻያ እርምጃ ቋሚ ኮሚቴው እንዳላየም ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአጠቃላይ የስኳር ፋብሪካዎችን በተመለከተ የጠራ እቅድ ማዘጋጀት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፤ የአማካሪና የተቋራጮች ውል ጉዳይን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግ እንዲሁም የግንባታና ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ጉዳይ ወሣኝ በመሆኑ በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ማድረግ እንደሚያሻ አሳስበዋል፡፡ እንደዚሁም ዘርፉ በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው እንደመሆኑ መጠን በአሠራር ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ፈትቶ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ዝግጅት የማድረግም ሆነ ለመንግስት የድጋፍ ጥያቄ የማቅረብ ኃላፊነት የዘርፉ አመራር እንደሆነ ገልፀው የስኳር ፋብሪካዎቹ ጉዳይ ቀለል ተደርጎ ሊታይ የማይችል በመሆኑ አመራሩ ጉዳዩን የህዝብ ጥያቄ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር  ጉዳይ አርጎ ሊያየው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለፋብሪካ ሥራ ተገዝተው የሚመጡ ማሽነሪዎች ከነባሮች ማሽነሪዎች ጋር መጣጣም ስለመቻላቸው አስቀድሞ ሊጠና እንደሚገባ የገለፁት ወ/ት ወይንሸት በንብረት አወጋገድ ላይ ከመንግስት ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ተቋማቱን በመከታተልና በመደገፍ ረገድም የኦዲት ግኝቱ የሚያሳየው የክትትል፣ የድጋፍና የቁጥጥር ችግሮች መኖራቸውን መሆኑን በመጥቀስ የበላይ አመራሩ እስከታች ድረስ ወርዶ ችግር ፈቺ ድጋፍና ክትትል  ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ሰብሳቢዋ አያይዘውም ለውስጥ ኦዲት አስተያየት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ፤ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ፤ የተደረጉ የማሻሻያ እርምጃዎች ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በየወቅቱ መላክ እንዳለባቸው፤ የሰራተኛ ፍልሰትን ለመቀነስ ሳቢ የስራ አካባቢ መፍጠር ላይ አትኩሮ መስራትና የሰራተኛውን ደህንነት በሚያስጠብቅ መልኩ የቁጥጥርና የክትትል ተግባር ማከናወን እንደሚገባ እንዲሁም ለመተግበር የተዘረጉት አሰራሮች ተግባራዊነታቸውን ማረጋገጥና አመራሩ ችግር ፈቺ ስትራቴጂክ አመራር መስጠት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *