News

የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና መብት በበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በኩል ቀጣይና ጠንካራ ጥረቶችን በማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተነደፉት የዘላቂ ልማት ግቦች የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥና የሴቶችን የአመራርነትና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ የተቀመጠውን ግብ በሚፈለገው ደረጃ ማሳካት  እንደሚገባ ተገለጸ ፡፡ ይህ የተገለጸው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ጥር 16 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ  ነው፡፡

ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2013 በጀት ዓመት ከዘላቂ ልማት ግቦች ግብ 5ን መሰረት ባደረገ የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን የማረጋገጥና ሴቶችን ወደ አመራርነት የማምጣት አፈጻጸምን አስመልክቶ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ላይ ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በመድረኩ በኦዲት ግኝቶቹ ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችን በሚመለከት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ምላሽ እንዲሰጥ ቋሚ ኮሚቴው ዋና ዋና ግኝቶችን አቅርቧል፡፡

በዚህም በሴቶች ላይ የሚደረጉ ዘርፈ ብዙ መድሎዎችን ለመከላከል፣ ለማስወገድና አፈጻጸሙንም ለመከታተል የሚያስችል ስርዓት በሚፈለገው ደረጃ አለመዘርጋቱ፣ ጸታዊ ጥቃትን ለመከላከል፣ ተገቢ እርምጃን  ለመውሰድና የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በሚፈለገው ደረጃ አለመሰራቱ፣ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ተጎጂዎች ለመንከባከብና ከደረሰባቸው አካላዊና ስነ ልቡናዊ ጉዳት ሊያገግሙባቸው የሚችሉ የተለያዩ ድጋፎች በሚፈለገው ደረጃ አለመሟላታቸው፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስቀረት የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለማሳካትና ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን የተደረጉ ጥረቶች አናሳ መሆናቸው ተገልጿል፡፡እንደዚሁም ሴቶች በርካታ ጊዜያቸውን ክፍያ በሌላቸው የቤት ውስጥ ስራዎችና እንክብካቤዎች የሚያሳልፉ ስለመሆናቸው ህብረተሰቡ እውቅና እንዲሰጥ ለማድረግ የተሰራው ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ አጥጋቢ አለመሆኑና በተለይም በገጠር አካባቢ  የእርሻ መሬት የባለቤትነት ማረጋገጫን ጨምሮ ሴቶች በሚፈለገው ደረጃ  የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያለመሆናቸውና የሴቶችን ስራ የሚያቀሉ የአማራጭ ኢነርጂ፣ የጉልበት ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችና ሌሎች የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች እንዲሁም የተመቻቹ የስራ ቦታዎች የሌሏቸው መሆኑ በኦዲት ግኝቱ መታየቱ በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡

ከዚህ ሌላም የሴቶች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ይህን ችግር ለመቅረፍ የተደረጉ ጥረቶች የሚፈለገውን ለውጥ ያላመጡ መሆናቸው፣ ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጪ ቦታዎች ላይ ለማምጣትና ብቁ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎችና የተሰጡ ስልጠናዎች አጥጋቢና ተደራሽ አለመሆናቸው፣ የልማት ፈንዶችን በማቋቋምና የብድር አቅርቦቶችን በበቂ ሁኔታ በማመቻቸት እንዲሁም የቁጠባ ባህልን እንዲያዳብሩ በማድረግ የተለያዩ ስራዎችን ፈጥሮ ሴቶችን በስራ እድሎች ተጠቃሚ ለማድረግና በኢኮኖሚ ለማብቃት  የተደረጉ ጥረቶች በቂና ዘላቂ አለመሆናቸው፣ ሴቶችን በሚመለከት የወጡ ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ የልማት ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞችን መሰረት በማድረግ ክልሎችን ጨምሮ ሌሎች መስሪያ ቤቶች የሴቶችን ጉዳይ በማካተትና ተቋማዊ በማድረግ ረገድ የሰሯቸውን ስራዎች መመዘንና መለካት የሚያስችል በቂ ስራ አለመሰራቱ ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪም የሴቶችን የተለያዩ ጉዳዮች የያዙ መረጃዎችን በተደራጀ ዘመናዊ የመረጃ ቋት ለማስቀመጥ በቂ ትኩረት አለመሰጠቱና ከሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የተከናወነው ተግባር ደካማ መሆኑ፣ ስርዓተ ጾታን አስመልክቶ በተለያዩ ጊዜያት የሚቀረጹ ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ መመሪያዎችና ሌሎች የአሰራር ማዕቀፎች ወቅታዊ አለመሆናቸው እንዲሁም ለተግባራዊነታቸው የተሰጠው ትኩረት በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑ በኦዲት ግኝቱ መረጋገጡን  ቋሚ ኮሚቴው በማንሳት ግኝቶቹን ለማሻሻል በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተሰጡ አስተያየቶች መሰረት የተወሰዱ እርምጃዎች እንዲብራሩ ጠይቋል፡፡

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድን ጨምሮ በስብሳባው ላይ የተገኙ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የስራ ኃላፊዎቹ የሴቶች ጉዳይ በዘላቂ የልማት ግቦች ውስጥ የተካተተ ሀገራዊ ጉዳይ እንደመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ጠቅሰው ለውጤታማነቱ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኦዲት ግኝቶቹ ትክክለኛ መሆናቸውንና ለዚህም ሚኒስቴር መ/ቤቱ በተለያዩ ዘርፎች ግኝቶቹን ለማሻሻል የሚረዱ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የገለጹት የስራ ኃላፊዎቹ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ የሚረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች የመስራትና   ችግር ፈቺ ጥናቶችን የማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የልማት ፈንድ እንደገና የማቋቋም፣ የሴቶች ጉዳይን በማካተት ረገድ ተቋማትን በተሻለ የምዘና ስርዓት የመለካት፣ የሴቶችን ምርታማነት ለማሳደግና በኢኮኖሚና በማህበራዊ ሁኔታዎች  ለማብቃት  ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዎቹ ከእምነትና ከባህል ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ውጤታማ ስራ ለመስራት ጊዜ የሚጠይቁ ቢሆንም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስቀረት ከእምነት አባቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት ለመስራት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስቆም የተለያዩ አካላትን ያቀፈ  ሀገራዊ ግብረ ሀይል መቋቋሙን  ገልጸው በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል ስትራቴጂና የድርጊት መርሀ ግብር የማዘጋጀትና የአሠራር ፕሮቶኮሎችን የመከለስ ስራ ተሰርቶ ከግብረ ሀይሉ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በጾታዊ ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ የሚወሰዱ ቅጣቶች እንዲሻሻሉ ለፍትህ አካላት ግንዛቤ የመስጠት ስራ መሰራቱንና ለተጠቂዎችም ድጋፍ ማድረጊያ ማዕከላትን ከማስፋፋት ጀምሮ ለማዕከላቱ ባለሙያዎችም ስልጠና የመስጠት፣ ለተጠቂዎች የተሟላ የስነ ልቦናና ቁሳዊ ድጋፍ የማድረግ ጥረቶች ተደርገዋል ብለዋል፡፡ በሴቶች ላይ የሚካሄዱ ጭፍን ፍረጃዎችና መድሎዎችን ለማስቀረት ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መሰጠቱን የጠቀሱት የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ለሴቶች የስራ ዕድልን በማመቻቸት  ረገድ ከፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ጋር ቅንጅታዊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም በታችኞቹ የአስተዳደር እርከኖች ላይ ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት የእየተደረገ ያለው ጥረት የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም አበረታች ጥረቶች መኖራቸውን የጠቀሱት የስራ ኃላፊዎቹ በተቋማት በሚደረጉ የመዋቅር ክለሳዎች ላይ ለሴቶች አስፈላጊው ትኩረት እንዲሰጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክሮች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተሰጡትን ምላሾች መሰረት በማድረግ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱና የስብሰባው ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማረጋገጥ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ውስጥ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ሚና የጎላና ቀዳሚ መሆን እንደሚገባው  ጠቅሰው ሂደትን እንደ ውጤት ከመቁጠር ይልቅ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የኦዲት ግኝቶቹ በተጨባጭ የሚታዩ  በመሆናቸው ችግሮቹን ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ በባለቤትነት ስሜት ኃላፊነትን ወስዶ  በሴቶች ህይወት ላይ ለውጥ የሚያመጣ ተግባር ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ አክለውም የሚታዩት ችግሮች በፖሊሲ፣ በህጎችና በመመሪዎች ላይ የተቀመጡትን ወደ ተግባር  የመቀየር ክፍተቶች መሆናቸውን ጠቁመው ጾታዊ ጥቃቶችና ትንኮሳዎች ከመሻሻል ይልቅ እየተባበሱ የመጡበትን ሁኔታ ለማስቀረት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ተጨማሪ ጥናቶች፣ ውጤታቸው ሊገመገም የሚችል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችና ስልጠናዎች  እንዲሁም  ክልሎችን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው ገልጸው ሴቶችን ወደ አመራር ቦታዎች ለማምጣት ከታችኛው እርከን ጀምሮ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የመሰረተ ልማት ክዋኔ  ኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  ወ/ሮ ሚለን አማረ በበኩላቸው  ግኝቶቹን ለማሻሻል የሚረዱ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ የተላከ ባለመሆኑ ከኦዲቱ በኋላ  የተሻሻሉ ሁኔታዎችን ለማወቅ እንደሚያስቸግር ጠቁመው በሴቶች ላይ የሚደረጉ መድሎዎችና ጾታዊ ጥቃቶችን ለማስቀረት የተሰሩ ስራዎችን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች በኦዲቱ ወቅት አለመገኘታቸውና በግኝቶቹ ላይ እርምጃዎች ስለመወሰዳቸው ወደፊት በሚደረግ የክትትል ኦዲት እንደሚረጋገጥ አመላክተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየትም በሴቶች ላይ የሚደረጉ መድሎዎችና ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ጥናቶች ቢደረጉም አፈጻጸማቸውን ለመከታተል የሚስችል ስርዓት ያልተዘረጋና ስልጠናዎቹና ግንዛቤ ማስጨበጫዎቹ በቂ ያለመሆናቸውን ጠቁመው  ከመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችን ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አክለውም ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በስነ ልቦናና በቁሳቁስ ለመደገፍ የተቋቋሙትን ማዕከላት በሚፈለገው ደረጃ በባለሙያና አስፈላጊ ግብአቶች ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስቀረት ከህጋዊ ቅጣት ባሻገር የተጠናከረና ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የሴቶችን የአመራርነት ሚና ለማጎልበት እና የስራ አድልን በማመቻቸት የሴቶችን ህይወት ሊቀይር የሚችል ለውጥ ለማምጣት በጥናትና በተግባር የተደገፈ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው ሴቶችን በተመለከተ  የሚታየው የተዛነፈ አስተሳሰብ የቆየ በመሆኑ ጨርሶ ለማጥፋት ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም ሚኒስቴር መ/ቤቱ በቀዳሚነት የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት ተጠቅሞ ችግሮቹን ለመቅረፍ የበለጠ ጥረት ማድረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡ የኦዲት ግኝቶቹን ለማስተካከል ለሚኒስቴር መ/ቤቱና ለባለድርሻ አካላት አቅጣጫ ያስቀመጡት ሰብሳቢው ሚኒስቴር መ/ቤቱ የድርጊት መርሀ ግብሩን በማዘጋጀት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴውና ለሚመለከታቸው አካላት እንዲልክ እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም የተሰጡትን አስተያየቶች ተግባራዊነትና አፈጻጸም እንዲከታተሉ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *