News

የመ/ቤቱ የ2010/2011 የስራ አፈጻጸም የተሳካ እንደነበረ ተገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ2010/2011 የኦዲት ዘመን እቅድ አፈጻጸም የተሳካ እንደነበረ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ገለጹ፡፡ መ/ቤቱ የ2010/2011 የኦዲት ዘመን የእቅድ አፈጻጸም የግምገማና የ2011/2012 የኦዲት ዘመን እቅድ ዝግጅት መድረኩን ከየካቲት 25-29/2011 ዓ.ም መላውን ሰራተኛ ባሳተፈ መልኩ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ አዳራሽ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ መክፈቻ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በ2010/2011 የኦዲት ዘመን በዋናነት እንዲሳኩ በመ/ቤቱ ትኩረት የተደረገባቸው ተግባራት እንደነበሩ በማስታወስ በነዚህ የትኩረት መስኮች ውጤታማ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም መ/ቤቱ በእቅድ የያዛቸውን ኦዲቶች ለማከናወን፣ የመ/ቤቱን የህግ ማእቀፍ በመተግበር ተቋማዊ ነጻነቱን ለማረጋገጥ፣ የስራ እቅዶችና አፈጻጸሞችን በአራቱ የቢ.ኤስ.ሲ እይታዎች ለማከናወንና ለመገምገም፣ የመ/ቤቱንና የሰራተኛውን የመፈጸም አቅም ለመገንባት፣ የተቋሙን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሳደግ፣ የኦዲት ጥራትን ለማሻሻልና ምቹ የስራ አካባቢን ለመፍጠር የተሰሩ ስራዎች ውጤት የተመዘገበባቸው እንደነበሩ አውስተዋል፡፡

የኦዲቱን ዘርፍ በማስመልከት ሲናገሩም በሁለት ዩኒቨርስቲዎች ላይ የታቀዱ ኦዲቶች ከመ/ቤቱ አቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች አለመሳካታቸውን ገልጸው ይህም በአንደኛው ዩኒቨርስቲ የነበረው የጸጥታ ችግር እንዲሁም ሌላኛው ዩኒቨርስቲም ሂሳቡን በወቅቱ መዝጋት ባለመቻሉ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከነዚህ ኦዲቶች በስተቀር ሌሎቹ ኦዲቶች መካሄዳቸውን፣ የመስክ ስራዎች በሙሉ መጠናቀቃቸውን ነገር ግን አንዳንድ የኦዲት ሪፖርቶች ገና አለመውጣታቸውን አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም የተገኘው ስኬት በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ በማለፍ የተገኘ በመሆኑ በዚህ ሂደት ያለፉ ሰራተኞችን በሙሉ አመስግነዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በመስሪያ ቤቱ ያሉ ሁሉም የኦዲትና የድጋፍ ዘርፍ ዳይሬክተሮች የየዳይሬክቶሬታቸውን የስራ አፈጻጸም በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የኦዲት ዘርፍ ዳይሬክቶሬቶች ባቀረቡት ዝርዝር ሪፖርት በፋይናንሻል ኦዲት የታቀዱት ስራዎች  መጠናቀቃቸው፣ በክዋኔ ኦዲት በእቅድ የተያዙትን በማጠናቀቅ የቀጣይ ዓመት አዳዲስ  ኦዲቶች መጀመራቸው፣ በድጋፍና ድጎማ ኦዲት ከታቀደው ያነሰ አፈጻጸም ቢኖርም አብዛኛው ኦዲት መከናወኑን እንዲሁም በኦዲት ዳይሬክቶሬቶች የሚከናወኑ ኦዲቶችን ጥራት የማረጋገጥ ስራዎች መሰራታቸው ተጠቅሷል፡፡

በድጋፍ ዘርፉም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በለውጥ ስራዎች አፈጻጸም፣ በእቅድ አፈጻጸም ግምገማና ክትትል፣ በህግ ማእቀፎች ዝግጅት፣ በፋይናንስ ግዥና ንብረት አስተዳደር፣ በሰው ሀይል ልማትና አስተዳደር፣ በውስጥና ውጭ የኮሙዩኒኬሽን ስራዎች፣ በውስጥ ኦዲት፣ በስልጠና እንዲሁም በስርዓተ ጾታና ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ረገድ የተሰሩ በርካታ ስራዎች መኖራቸው ተገልጿል፡፡

በሁሉም ዳይሬክቶሬቶች በኩል የአፈጻጸም ጥንካሬዎችና ድክመቶች እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ እርምጃዎች ቀርበዋል፡፡

የ2011/2012 ኦዲት ዘመን የመ/ቤቱ የኦዲትና የድጋፍ ዘርፎች የትኩረት አቅጣጫዎች የመ/ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች፣ ዳይሬክተሮችና በከፍተኛ ባለሙያ ደረጃ ያሉ ሰራተኞች በተገኙበት የተለዩ ሲሆን ጉዳዩ በሚመለከታቸው ዳይሬክቶሬቶች እቅድ ውስጥ በማካተት እቅዱ እንዲዘጋጅ ተደርጎ መላው ሰራተኛ በተሳተፈበት የማጠቃለያ መድረክ እቅዱ እንዲጸድቅ ተደርጓል፡፡

በማጠቃለያ መድረኩ ላይ ሁሉም ዳይሬክቶሬቶች በባለፈው አፈጻጸማቸው ጥንካሬዎችና ድክመቶች ላይ በስራቸው ካሉ ባለሙያዎች ጋር በዝርዝር እንዲወያዩ፣ የስራ እቅዳቸውን በበለጠ ጥልቀት እንዲፈትሹና በቢ.ኤስ.ሲ አሰራር መሰረት ካስኬድ በማድረግ ዝርዝር እቅድ እንዲያዘጋጁ፣ የቀጣይ አመት አፈጻጸማቸውን ከባለፈው የላቀ ለማድረግ በሙሉ ቁርጠኝነትና ዝግጁነት እንዲሰሩ በበላይ አመራሩ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

One thought on “የመ/ቤቱ የ2010/2011 የስራ አፈጻጸም የተሳካ እንደነበረ ተገለጸ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *