News

የመ/ቤቱ የእቅድ አፈጻጸም ለሌሎች ተቋማት በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑ ተገለጸ

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን የ2017 የመጀመሪያ ግማሽ አመት የእቅድ አፈጻጸም በመገምገም አፈጻጸሙ ለሌሎች ተቋማት አርአያ ሊሆን እንደሚችል ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው መጋቢት 14/2017 ዓ.ም የመ/ቤቱን የእቅድ አፈጻጸም በገመገመበት መድረክ መ/ቤቱ እቅዱን በተቀመጠለት አግባብ ስኬታማ በሆነ መልኩ መተግበሩ እና በቋሚ ኮሚቴው በየወቅቱ የሚሰጡትን የማሻሻያ አስተያየቶችም ተገቢ ትኩረት በመስጠት ምላሽ መስጠቱ በጥንካሬ የሚነሱ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው በተዘጋጀው መድረክ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የ2017 በጀት አመት የመጀመሪያውን አጋማሽ የእቅድ አፈጻጸም ዝርዝር ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ከሪፖርቱ በኋላ በቋሚ ኮሚቴ አባላቱ የግምገማ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡

ክብርት ዋና ኦዲተር በሪፖርታቸው አጠቃላይ የኦዲት ሥራው የደረሰበትን ደረጃ፣ የኦዲት ጥራትን ለማሻሻልና የአቅም ግንባታ ስራን ለማጠናከር የተሰራውን ስራ እንዲሁም ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ እና በጀትን በአግባቡ ከመጠቀም አንጻር የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የሰው ኃይል ከማሟላት፣ የህጻናት ማቆያን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ከማደራጀትና  ምቹ የሥራ አከባቢ ከመፍጠር ፣ ከንብረት አወጋገድ፣ ዘረፈ ብዙ ጉዳዮችን ትኩረት ሰጥቶ ከመስራት፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትግበራ፣ ከባለድርሻ አካላት ግንኙነት እና ከሚዲያና ከኮሙዩኒኬሽን አንጻር የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን በመግለጽ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን አጠቃላይ የበጀት አመቱን የመጀመሪያ አጋማሽ የእቅድ አፈጻጸም 98.8 በመቶ በማድረስ ማሳካት መቻሉን ክብርት ዋና ኦዲተሯ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡

የሠራተኞችን አቅም፣ የኦዲት ሽፋንና ጥራት ከማሳደግ በተለይም ከአለም አቀፍ የኦዲት ተቋማት እና የሀገር ውስጥ የኦዲት ባለድርሻ አካላት ጋር ያሉ ግንኙነቶችንና ቅንጅታዊ አሠራሮችን ከማጠናከር አንጻር በግማሽ አመቱ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን በሪፖርታቸው ጨምረው የጠቀሱት ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ የኦዲተሮች አበልና ጥቅማጥቅም አለመፈቀድና የመስክ አበል በቂ አለመሆን፣ አንዳንድ ኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች በወቅቱ ሰነድ አለማቅረብ እና ሂሳብ በወቅቱ አለመዝጋትን ጨምሮ በእቅድ አፈጻጸም ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በሪፖርታቸው ጠቅሰው ችግሮቹን ለመፍታትና እቅዶቹን ለማሳካት በመ/ቤቱ በኩል ከፍተኛ ጥረት የተደረገ መሆኑንና የመፍትሔ እርምጃዎችም መቀጠላቸውን ገልጸዋል፡፡

በክብርት ዋና ኦዲተሯ የቀረበውን የእቅድ አፈጻጸም ዝርዝር ሪፖርት ተከትሎ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን የመ/ቤቱ የእቅድ አፈጻጸም እርምጃ በየጊዜው እያደገ የመጣና ለሌሎች ተቋማትም በአርአያነት የሚወሰዱ በርካታ ውጤታማ ሥራዎች የታዩበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

መ/ቤቱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያካሂዳቸው ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥራዎች፣ የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ሰራተኞችን ለማትጋት የተካሄደው የእውቅና ሽልማት መርሃግብር፣ ንብረቶችን ያስወገደበት መንገድ፣ ከዘርፈ ብዙ ጉዳዮች አንጻር የተሰሩ ውጤታማ ሥራዎች እና ሌሎች በተለይም ተቋሙ የህንጻ እድሳት ሲያከናውን ወጪ ቆጣቢ መንገድ በመከተል ለህንጻ ኪራይ ሊወጣ ይችል የነበረውን የ76 ሚሊየን ብር ወጪ ማዳን መቻሉ በአርአያነት የሚጠቀሱ የመ/ቤቱ ጉልህ ሥራዎች መሆናቸውን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር) በመድረኩ ማጠናቀቂያ በሰጡት አስተያየት አጠቃላይ የመ/ቤቱ አፈጻጸም በስኬታማ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው የባለድርሻ አካላትን ግንኙነትና ቅንጅታዊ አሰራር ከማሳደግ፣ የልማት ድርጅቶችን ኦዲት ትኩረት ሰጥቶ ከመስራት እና ከክልሎች ጋር ያሉ ግንኙነቶችን በአሠራር ሥርዓት ከማጠናከር አንጻር የሚሠሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *