የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እና የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ሰራተኞችና አመራሮች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ህዳር 27 ቀን 2014 ዓ.ም የደም ልገሳ አደረጉ፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ የደም ልገሳ መርሀ ግብሩ በዋናነት ሀገራችን የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ እየተዋደቀ ላለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰራተኛውና አመራሩ አጋርነቱን ለመግለጽ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የማይመለስ ህይወቱን እየሰጠ እኛን እያኖረ ነው ያሉት ክብርት ምክትል ዋና ኦዲተሯ ከዚህ አንጻር የኛ የደም መለገስ ተጋኖ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሰረት በቀጣይም የደም ልገሳው ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉ ሲሆን ሰራዊታችን በግንባር በሚዋደቅበት ጊዜ በሚደርስ ጉዳት ምክንያት ደም የሚያስፈልገው በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ደም በመለገስ መሳተፍ አለበት፣ በደም ልገሳ ብቻ ሳይወሰንም ሌሎች ድጋፎችን ለሰራዊቱ መስጠት አለበት ብለዋል፡፡
ደም በመለገስ የተሳተፉ የመ/ቤቱ ሠራተኞች እንደገለጹትም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለውድና ለማይተካ ህይወቱ ሳይሰሳ ለሀገርና ለህዝብ ህልውና መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው የመከላከያ ሠራዊት ደማቸውን በመለገስ አጋርነታቸውን ለማሳየት በመርሀግብሩ መካፈላቸውን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አመራሮችና ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው በማዋጣት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የ1.8 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡