News

የመ/ቤቱ ሰራተኞች ለሴቶች መብት መከበር የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡

የሀገራችን ሴቶች መብት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ሁለንተናዊ ተሳታፊነታቸው እንዲጎለብት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሰራተኞች የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ አስገነዘቡ፡፡ የመ/ቤቱ ሰራተኞች በአለም አቀፍ ደረጃ ለ108ኛ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ43ኛ ጊዜ “የላቀ ትኩረትና ቁርጠኝነት – ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት!” በሚል ሀገራዊ መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን የካቲት 29/2011 ዓ.ም በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ አዳራሽ አክብረዋል፡፡

በአሉን አስመልክቶ ክቡር ዋና ኦዲተሩ ባደረጉት ንግግር ሴቶች በወንዶች የበላይነት በደረሰባቸው ተጽዕኖ የተነሳ የትምህርት፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲሁም የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ሙሉ በሙሉ እንዳልተጠበቁላቸው ገልጸዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተሩ ከሀገራችን ህዝብ ግማሹን ድርሻ የሚይዙትን ሴቶች ሳያካትቱ ልማትን፣ ዲሞክራሲንና ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደማይቻል ገልጸው ለዚህም መብታቸውና ሁለንተናዊ ተሳትፏቸው እንዲረጋገጥ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ የሴቶችን መብትና ተሳትፎ ማረጋገጥ ከቤተሰብ ይጀምራል ያሉ ሲሆን ቤተስብ የሴቶችን መብት በማስከበርና በማስጠበቅ እንዲሁም መብታቸውን እንዲጠቀሙ በማድረግና በማዘጋጀት በኩል ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

የሴቶች መብት በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲረጋገጥ ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ያሉት ክቡር አቶ ገመቹ በዚህ ረገድ የመ/ቤቱ ሰራተኞችም የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በበአሉ አከባበር ላይ የሴቶችን ሚና የሚያጎሉ ግጥሞች፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች በሀገራችን ቀዳሚ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን የሚያስተዋውቅ መረጃ እንዲሁም ባለፉት አስርት አመታት የዓለም አቀፍ ሴቶች ቀን የተከበሩባቸው ሀገራዊ መሪ ቃሎች የቀረቡ ሲሆን የሻማ ማብራትና የዳቦ ቆረሳ ስነስርአቶች ተከናውነዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *