News

የመ/ቤቱን የኦዲት አሠራርና ውጤቶች ለህዝብ ለማድረስ የኮርፖሬሽኑ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተለያዩ ተቋማት ላይ የሚያከናውነውን ኦዲት ውጤቶችና የኦዲት አሠራር ሂደቶችን የሚመለከቱ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ተደራሽነትና ሽፋን ያለው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሚና የጎላ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የመ/ቤቱ የማኔጅመንት አባላት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በመገኘት የስራ ጉብኝት ባደረጉበት እና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከፍተኛ አመራሮች ከኮርፖሬሽኑ አመራሮች ጋር የጋራ ስራ የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረሙበት ስነ-ስርዓት ላይ ነው፡፡

የመ/ቤቱ የማኔጅመንት አባላት ህዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም የኮርፖሬሽኑን የስራ እንቅስቃሴና አሁን የደረሰበትን ደረጃ በመዘዋወር የጎበኙ ሲሆን በኮርፖሬሽኑ ስር ያሉ በርካታ የሬዴዮና የቴሌቪዥን የስራ ክፍሎችን የሰው ኃይልና የአሠራር አደረጃጀት፣ የግብአት አጠቃቀም እና በርካታ የዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በኮርፖሬሽኑ አመራሮች በተደረገ ሰፊ ገለጻ ጎብኝተዋል፡፡

ከስራ ጉብኝቱ በኋላ በሁለቱ ተቋማት መካከል የጋራ ስራ መግባቢያ ስምምነት የተካሄደ ሲሆን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤና አቶ ጌትነት ታደሠ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡

በስምምነት ፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠን ጨምሮ ሌሎች የማኔጅመንት አባላት ረዥም የአገልግሎት ጊዜ ያስቆጠረውና የሀገሪቱ አንጋፋ የሚዲያ ተቋም የሆነው ኮርፖሬሽኑ በሁለገብ አደረጃጀቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑን ከጉብኝታቸው መረዳታቸውን በሰጧቸው አስተያየቶች ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ከመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ስነ-ስርዓቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት ኮርፖሬሽኑ ከሀገር አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊሆን በሚችልበት ሂደት ላይ መሆኑን ከአደረጃጀቱና ከዘመናዊ አሠራሩ መመልከት መቻላቸውን ጠቅሰው የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ኮርፖሬሽኑ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ባለድርሻ ተቋም እንደመሆኑ የኦዲት አሠራሮችንና ውጤቶችን ለህብረተሰቡ በሰፊው ከማድረስ አንጻር ያለውን ድርሻ የበለጠ የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሠ በበኩላቸው የኮርፖሬሽኑን ስራ ለማጠናከር በተካሄዱ ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎች አበረታች የአደረጃጀት እና የአሰራር መሻሻሎች መታየታቸውን ገልጸው ይህ የኮርፖሬሽኑ ዘመናዊና ጠንካራ አደረጃጀት የመ/ቤቱን የኦዲት አሠራርና ውጤቶች በስፋትና በዘመናዊ መንገድ በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር አጋዥና የተጠናከረ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሀን ታሪክ ለዘጠና ዓመታት አገልግሎት ያለውና ከሬዴዮ ስርጭት አገልግሎት በመጀመር በርካታ ሰፋፊና ዘመናዊ የሬዴዮና የቴሌቪዥን ቻናሎችን በማቀፍ ሰፊ ተደራሽነት ያለው አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ አንጋፋ የሚዲያ ተቋም መሆኑ በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የሚያመነጫቸውን የኦዲት ውጤቶችና ሪፖርቶች እንዲሁም የኦዲት አሠራሮች ለህብረተሰቡ በስፋት ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ከሚገኙ በርካታ የሚዲያ ተቋማት መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡

      

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *