የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን የኦዲት ጥራት ለማሳደግ የሚረዳና ከጥቅምት 14-16/2011ዓ.ም. የሚቆይ የአቅም ግንባታ ስልጠና በእንግሊዝኛ ተናጋሪ የአፍሪካ ሀገራት ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ማህበር (አፍሮሳይ-ኢ) አሰልጣኖች አማካኝነት ለመ/ቤቱ ኦዲተሮችና የስራ ሀላፊዎች መሰጠት ተጀመረ፡፡
በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ስልጠናውን በንግግር በከፈቱበት ወቅት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የፋይናንሻል ኦዲት ሽፋንን 100 ፐርሰንት ማድረስ እንደቻለና የኦዲት ጥራትን በየጊዜው ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጋር በማያያዝም በ2010 ዓ.ም ከአፍሮሳይ-ኢ የተወጣጣ ቡድን በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በመገኘት መ/ቤቱ የሚያደርገውን ኦዲት ጥራት መገምገሙንና ሊሻሻሉ የሚገቡ ጉዳዮችን ማመልከቱን በማስታወስ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት ቡድኑ እገዛ ለማድረግ በገባው ቃል መሰረት ስልጠናውን ለመ/ቤቱ ኦዲተሮች ለመስጠት መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሰረት መ/ቤቱ የሚያከናውነው ኦዲት በህብረተሰቡና በመንግስት ዘንድ ይበልጥ ትኩረት እያገኘ እንደመጣ ጠቅሰው የኦዲት ስራውን ጥራትን ማእከል አድርጎ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም ሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ መከታተልና በስራቸው የሚገኙ ሌሎች ባለሙያዎችን በማብቃት የተሻለ ጥራት ያለው የኦዲት ሪፖርት እንዲወጣ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡