News

የላይኛው ጉደር ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት በአግባቡ እየተመራ አለመሆኑ ተገለጸ

በቀድሞ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መስኖ ልማት ኮሚሽን በአሁኑ የመስኖና ቆላማ አከባቢ ሚኒስቴር የሚመራው የላይኛው ጉደር ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት በተገቢው ሁኔታ እየተመራ አለመሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳየች ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡

በሪፖርቱ የላይኛው መስኖ ልማት ፕሮጀክት የሚፈለገውን የመሬት ማስረጃ ለከተማው ወይም ለወረዳው እንዳላቀረበ፤ ተቋራጮች አስተማማኝ የብቃት ደረጃ ላይ ስለመገኘታቸው በአግባቡ በማረጋገጥ ድህረ-ብቃት ግምገማ ያላደረገ መሆኑ እንዲሁም በፕሮጀክቱ የሚሠሩ ድርጅቶችና የሥራ ተቋራጮች በገቡት ውል መሠረት ሥራቸውን ያልጀመሩ መሆኑ ተጠቁማል፡፡

በሌላ በኩል የፕሮጀክቱ አማካሪ ድርጅት የዲዛይን ግምገማ እና ሌሎች የሚጠበቁበትን ኃላፊነቶች በአግባቡ አለመወጣቱ፤ ለልማት ተነሺዎች የንብረት ካሳ በወቅቱ ሳይከፈላቸው ከይዞታቸው እንዲነሱ የተደረጉ መሆኑ እና ስለልማቱ ዓይነት፣ ጠቀሜታና አጠቃላይ ሂደት እንዲያውቁት አለመደረጉም ተመላክቷል፡፡

እንደዚሁም ለፕሮጀክቱ ለሚሠሩ ሥራዎች የላብራቶሪ ዕቃዎች ተሟልተውና እና ተፈትሸው አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸውን፤ ከመስኖ ግንባታ ግብዓት ጋር በተያያዘም የአሠራር ጥሰቶች መፈጸማቸውን እና ለአከባቢው ማህበረሰብ ከሥራ ዕድል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ አለመደረጉ ተመላክቷል፡፡

የመስኖ እና ቆላማ አከባቢ  ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ደካማ አፈጻጸም እንዳለው በተቋማቸው መገምገሙን ጠቁመው የኦዲት ሪፖርቱ ቀድሞ እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል፡፡

የኦዲት ግኝቶቹ መረጃ ላይ የተመሠረቱ  እንዲሁም ጠቃሚና አስተማሪ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ ፕሮጀክቱን በገመገሙበት ወቅት የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ጥረት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የካሳ ክፍያ ጉዳይ ከተቋማቸው አቅም በላይም በመሆኑ ከክልሉ አመራሮች ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን እና በቀጣይም የኦዲት ግኝቱን የዕቅዳቸው አካል አድርገው እንደሚሠሩ ኢንጂነር አይሻ ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው ፕሮጀክቱን በአግባቡ የሚመራ አካል በሚኒስቴር መ/ቤቱ አለመኖሩ፣ ለኦዲት ግኝቱ ተገቢው ምላሽ ተሰጥቷል ብለው እንደማያምኑ እና በተለይም ከካሳ ክፍያ አፈጻጸም ጋር በተያያዙ ችግሮች ላይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለሠራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው በፕሮጀክቱ መነሻ ላይ በመንግስትም ሆነ በአከባቢው ማህበረሰብ ፍላጎት የነበረ ቢሆንም ወደ ሥራ ከመገባቱ በፊት በቂ ዝግጅት እንዳልተደረገበት እና በህብረተሰቡ ዘንድ በቂ የባለቤትነት ግንዛቤ አለመፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

አክለውም በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የታዩበት ከመሆኑ አኳያ ተጨማሪ ልዩ ኦዲት ቢሠራበት የተሻለ መሆኑን  ጠቁመዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በኦዲት ግኝት ማስተካከያው መርሀ-ግብር መሠረት እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የማስተካከያ እርምጃ ወሰዶ ሪፖርት እንዲያደርግ፤ ከላይኛው ጉደር መስኖ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን በመለየት እና ክፍተቶችን በመሙላት ጥፋተኛ በሆኑ ባለሙያዎች እና የሥራ ኃላፊዎች ላይ ርምጃ ወስዶ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲያሳውቅ አሳስበዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ክርስቲያን አክለውም የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሚያከናውናቸው የልማት ፕሮጄክቶች የአዋጭነት ጥናት የሚያስፈልጋቸው፣ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ የሚደረግባቸው እና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት እና ባለቤትነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ግንዛቤ ወስዶ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም ሰብሳቢው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከላይኛው ጉደር መስኖ ፕሮጄክት ጋር ተያያዥ በሆኑ የኦዲት ግኝቶች ማስተካከያ አፈጻጸም በየሦስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርብ እና የፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትም ልዩ ኦዲት እንዲያደርግ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *