Uncategorized

ዓለም አቀፍ የሙስና መከላከል ቀን ተከበረ

18ኛው ዓለም አቀፍ የሙስና መከላከል ቀን ህዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ተከበረ፡፡

በስነ-ምግባር የታነጸ አመራር ከሙስና ለጸዳች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ለ17ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ያለውን ዓለም አቀፍ የሙስና መከላከል ቀን ምክንያት በማድረግ የመ/ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል፡፡

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ሙስና ረቂቅ የሆነና ለመከላከልም የአስተሳሰብ ለውጥን የሚፈልግ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ክብርት ም/ዋና ኦዲተሯ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋና ዓላማ የህዝብና የመንግስት ሀብት ሙስናን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች እንዳይባክንና በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል የኦዲት ስራ ማከናወን መሆኑን ጠቅሰው የመ/ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች ሙስናን በመከላከል ሂደት ከፍተኛ ሀገራዊ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ አክለውም ከሙስና የጸዳች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከቤተሰብ ጀምሮ ሊኖር የሚገባው የአስተሳስብ ለውጥ ከሌለ ሙስና ሀገርን የሚያጠፋ መሆኑንም  አስገንዝበዋል፡፡

የመ/ቤቱ የስነ ምግባር መከታተያ የስራ ክፍል ኃላፊ አቶ ሀይሉ ፈረደ ስለሙስና ምንነት፣ የሙስና ደረጃና መገለጫዎች፣የሙስና ወንጀል ተግባር ባህርያት፣የሙስና ወንጀል ድንጋጌዎች፣ ሙስና በሀገርና በህዝብ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት፣ ሙስናን የመከላከል ዘዴ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ዝርዝር ማብራሪያ አቅርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በስነስርዓቱ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎችም ሙስናን ለመከላከልና ብሎም ለማጥፋት ለህዝብና ለሀገር ሀብት የሚቆረቆርና በመልካም አስተዳደር ታንጾ ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ ዜጋ የሚያስፈልግ መሆኑን በሰጧቸው ሀሰቦች አብራርተዋል፡፡

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙ የመ/ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች “NO MORE CORRUPTION” “ሙስና ይቁም” በማለት ሙስናን ለመከላከልና አጥብቆ ለመዋጋት በጋራ ቃል ገብተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *