News

ኮርፖሬሽኑ የኦዲት ግኝቶችን ለማረም እየወሰደ ያለው እርምጃ አበረታች መሆኑ ተገለጸ

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2010/2013 በጀት ዓመት የግዢ አፈጻጸም ሥርዓት ላይ ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት መሠረተ በማድረግ ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋዊ የህዝብ ውይይት አካሂዷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተካሄደውን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መሰረት በማድረግ ኮርፖሬሽኑ የግዢ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያዎችን በሥራ ላይ በአግባቡ ስለማዋሉ፣ የግዢ አፈጻጸም እና የግዢ ሰነዶች አያያዝና አጠባበቅ ላይ ስለታዩ የአሠራር ክፍተቶች እንዲሁም የመመሪያ ጥሰቶች የተቋሙ ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ አያሌው በሰጡት ማብራሪያ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እየሰጣቸው የሚገኙ ምክረ ሃሳቦችን በመሠረታዊነት ወስደው ለሥራቸው ውጤታማነት በግብዓትነት እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም ተቋማቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ለማከናወን ፍላጎት ያለው መሆኑንና ከወቅታዊ የዋጋ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞም በተቀመጡ የአሠራር ሥርዓቶች መሠረት ስራዎችን ለማከናወን እየተቸገሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

የተቋማቸውን አሠራር ይበልጥ ለማዘመንና የአሰራር ስርዓታቸውን ለማሻሻል የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመተግበር ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ እንዲሁም በኦዲት ግኝቱ መሠረት ተጠያቂነትንም ለማረጋገጥ እየሠሩ እንደሆነም አቶ ዮናስ አስረድተዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው ተቋሙ በራሱ ተነሳሽነት ኦዲት ለመደረግ ያሳየው ፍላጎት እና የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ እየወሰደ ያለው የዕርምት እርምጃ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ ሥራዎቹን ሲሰራ ለአሰራር ስርዓቶችና መመሪያዎች ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ እንዲሁም ተጠያቂነት ሊያረጋገጥ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ የኦዲት ሥራ ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘብ ኦዲት እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውሰው የተቋሙ አመራሮችም ከኦዲቱ በኋላ በተገኙ ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ የሄዱበት ርቀት የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አክለውም ኦዲቱ በናሙና የተከናወነ በመሆኑ የተቋሙ አመራሮች በዚህ ኦዲት የታዩትን ግኝቶች መነሻ በማድረግ ይበልጥ አሠራራቸውን ሊፈትሹና ሊያዘምኑ እንደሚገባ፤ የቁጥጥር ሥራዓቶችን ሊያጠናክሩ እና ተጠያቂ መሆን ያለባቸው አካላት ላይም ተጠያቂነትን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በመጨረሻ በሳተላለፉት መልዕክት ኮርፖሬሽኑ የኦዲት ግኝቱን የስራው አካል አድርጎ እያከናወነ ያለው ተግባር አበረታችና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ከጊዜ ጋር የሚሄድ የግዢ መመሪያ ማዘጋጀት የሚገባው መሆኑን የጠቀሱት የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ የሚታዩ የአሠራር ክፍቶችን በማረም ለብልሹ አሠራር የሚያጋልጡ ተግባራትን ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *