News

ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በኮሚሽኑ አሠራር ላይ የታዩ የኦዲት ግኝቶች እስከአሁን ድረስ ያለመስተካከላቸው ተጠቆመ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2013/2014 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ላይ ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት መሰረት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የታዩ የኦዲት ግኝቶች አስከአሁን ድረስ ያልተስተካከሉ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ እንደተገለጸው ኮሚሽኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ በስሩ የሚገኙ በርካታ የፌዴራልና የክልል የህብረት ስራ ማህበራትንና ዩኒየኖች ስራ ለመምራትና ለማስተዳደር በሚያስችለው የአሠራር ሥርዓት ላይ በርካታ ጉድለቶች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

ኮሚሽኑን ለማቋቋም በ2009 ዓ.ም የወጣውን አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ እስከአሁን ያልጸደቀ መሆኑ በመድረኩ ላይ የተነሳ ሲሆን የህብረት ሥራ ማህበራት አስፈላጊውን መስፈርት ሳያሟሉ ህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም ከፖሊሲ እና መመሪያ ዝግጅትና ትግበራ ጀምሮ በኢንስፔክሽን ስራዎች፣ በጥናት ትግበራ፣ በአቅም ግንባታ፣ በድጋፍና ክትትል በግብይት ትስስር፣ በመረጃ ልውውጥና አደረጃጀት እንዲሁም በቅንጅታዊ አሠራር ረገድ በርከታ ጉድለቶች መኖራቸው በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡

የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌታቸው መለሰ (ዶ.ር) እና የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች በተነሱት ግኝቶች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የኦዲት ግኝቶቹን በግብአትነት በመውሰድ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፖሊሲውን በተመለከተ ኮሚሽኑን የሚመለከቱ ጉዳዮች ተቋሙ ተጠሪ በሆነለት የግብርና ሚኒስቴር በኩል በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጀው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ውስጥ ተካተው የሚዘጋጁ በመሆኑ አስፈላጊውን የፖሊሲ ግብአት ለግብርና ሚኒስቴር መስጠታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከሰባት ዓመታት በፊት የወጣው የተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቶ በኮሚሽኑ በኩል የቀረበ ቢሆንም በሚመለከተው አካል እስካሁን ድረስ ያለመጽደቁን የጠቀሱት ኃላፊዎቹ በክትትልና ድጋፍ፣ በስልጠና፣ በኢንስፔክሽን ስራዎች እና በሌሎችም አሠራሮች ላይ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው ብለዋል፡፡

የኦዲት ግኝቶቹ የተቋሙን ተልዕኮ በቀጥታ የሚመለከቱ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሰጡት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ.ር) በበኩላቸው ትክክለኛውን መስፈርት ላላሟሉ ማህበራት ህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ መስጠት ተገቢ ባለመሆኑ ሚኒስቴር መ/ቤታቸው አስፈላጊውን የክትትልና ቁጥጥር ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡

በክልል ለሚገኙ ማህበራት አስፈላጊው በቂ ድጋፍ እየተሰጠ እንዳልሆነ ጨምረው የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚህም በኩል አስፈላጊው ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በተደረጉ ሶስት የክዋኔ ኦዲቶች በታዩ ግኝቶች ላይ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ አስተያየቶች እየተሰጡ ቢሆንም ተገቢና በቂ በሆነ ደረጃ የማሻሻያ እርምጃዎች እየተወሰዱ አይደለም ብለዋል፡፡

ከተቋቋሙ ከ1 ዓመት አስከ ሶስት ዓመታት የሆናቸው ማህበራት ወደ ስራ ያለመግባታቸውን ኦዲቱ የሚያሳይ መሆኑን ጨምረው የጠቀሱት ም/ዋና ኦዲተሩ ባልጸደቀ ደንብና ህግ የሚሰሩ ማህበራት መኖራቸውን ጠቁመው ማሻሻያ ይደረግባቸዋል የተባሉ በርካታ ግኝቶች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ማብራሪያ አለመሰጠቱን አንስተዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በበኩላቸው ለአርሶ አደሩ የግብርና ግብአት እንዲሁም ለከተማው ነዋሪ አስፈላጊ ፍጆታዎችን ከማቅረብና ገበያን ከማረጋጋት አንጻር የህብረት ስራ ማህበራት ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ማድረግ እንደሚገባው በመጥቀስ ኮሚሽኑ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ለተሰጡት የኦዲት ግኝት ማስተካከያ አስተያየቶች ትኩረት ያለመስጠቱንና ግብርና ሚኒስቴርም ፖሊሲና ደንብ አጸድቆ ከማስተግበር አንጻር ክፍተት ያለበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ተገቢ መስፈርት ሳያሟሉ ህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ መሰጠቱ ህጋዊ ያለመሆኑን የገለጹት ክብርት ወ/ሮ መሠረት በምርት ጥራት፣ በመረጃ  አደረጃጀት እና ልውውጥ፣ በድጋፍና ክትትል፣ በዳሰሳ ጥናት እና በሌሎችም ያሉ ክፍተቶችን ማስተካከልና አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ስራ በመስራትና ያሉባቸውን ችግሮች በጥናት በመፍታት የማህበራቱን አቅም ወደ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ደረጃ ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት የአመራር መለዋወጥ ቢኖርም ተቋማት ቀጣይና ቋሚ በሆነ የአሰራር ስርዓት መመራት እንዳለባቸው በመጥቀስ ኮሚሽኑ ካሉበት በርካታ ክፍተቶች አንጻር በተቀመጠለት ተልዕኮና ዓላማ ልክ እየሰራ አይደለም ብለዋል፡፡

ተከታታይ ኦዲት ተደርጎና አስተያየት ተሰጥቶ መሻሻል ያልታየበት ተቋማዊ አሠራር መታየቱ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጨምረው የጠቀሱት ም/ሰብሳቢዋ የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ የተሻሻለ አዲስ የድርጊት መርሀ ግብር በኮሚሽኑ በኩል ተዘጋጅቶ እስከ ሰኔ 15/2015 ዓ.ም ድረስ  እንዲቀርብና የተወሰዱ እርምጃዎች አፈጻጸምም በየሁለት ወራት ሪፖርት እንዲደረግ እንዲሁም ግብርና ሚኒስቴርም ደንብና መመሪያን አስመልክቶ በኮሚሽኑ የታዩ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ በማድረግ በ2 ወራት ውስጥ ሪፖርት እንዲያቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *