የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጀንሲና የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በየዘርፋቸው የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ከዘርፋቸው አላማ ጋር በጥብቅ አስተሳስረውና አጠናክረው ማከናወን እንዳለባቸው የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ በ2008ዓ.ም የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጀንሲ እና የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በሚል ለሁለት ከመከፈሉ አስቀድሞ በነበረው አደረጃጀት ሲሰራ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተካሄደበት የ2007 በጀት አመት የፋይናንሻልና የክዋኔ ኦዲቶች ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ ጥር 24 ቀን 2009 ዓ.ም አድርጓል፡፡
በስብሰባው ወቅት በቀድሞው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ላይ የተገኙት የፋይናንሻልና ክዋኔ ኦዲቶች ግኝቶች በዝርዝር ቀርበው ምላሽ እንዲሰጥባቸው የተጠየቀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ያሉት የሁለቱ አዲስ ኤጀንሲዎች የስራ ሀላፊዎች በጋራ ምላሽ ሰጥተውባቸዋል፡፡
በፋይናንስ አያያዝና አስተዳደር ረገድ በካዝና እንዳለ በሰነድ ከተገለጸው ብር 115,114.13 ውስጥ በቆጠራ ወቅት የተገኘው ጥሬ ገንዘብ ብር 11,558.25 ብቻ መሆኑን፣ ከካዝና ውስጥ ከ107 ሺህ ብር በላይ መሰረቁን፣ ክፍያ የተፈጸመበት ገንዘብ በወጪ ሂሳብ አለመመዝገቡን፣ ለሰልጣኞች የተከፈለ የውሎ አበል ለተገቢው ኃላፊዎች መከፈሉን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለመኖሩን፣ የሚመለከተው ባለስልጣን ሳይፈቅድ ለአገልግሎት ግዥ ክፍያ መፈጸሙን፣ ከብር 50 ሺህ በላይ የሆነ ክፍያን በባንክ መክፈል ሲገባ በቼክ መከፈሉን እና የሂሳብ አርእስት አመዘጋገብ ስህተቶች መኖራቸውን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡
የመስሪያ ቤቶቹ ኃላፊዎች በሂሳብ አያያዝና አስተዳደር ላይ የአቅም፣ የአሰራር፣ የግንዛቤና የሰው ሀይል ችግር በመኖሩ እንዲሁም በወቅቱ በነበሩ አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ምክንያት ስህተቶቹ መፈጸማቸውን ገልጸው ያለፉ ስህተቶችን ለማረምም ሆነ በቀጣይ እንዳይፈጸሙ ለማድረግ የእርምት እርምጃ እንደተወሰደ እንዲሁም ከካዝና የተሰረቀው ገንዘብ ጉዳይ ለፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔ እንደተሰጠበትና ውሳኔውን ለማስቀየር በይግባኝ ለመከራከር እንደታቀደ ገልጸዋል፡፡
በክዋኔ በኩል ለአዳዲስ ኢንተርፕራይዞችና ለነባር አንቀሳቃሾች የሚሰጠው የብድር አቅርቦት በየአመቱ ቢሻሻልም በእቅድ ከተያዘው ላይ አለመድረሱ፣ የብድር ተጠቀሚዎቹም አነስተኛ መሆናቸውና የተሰጠ ብድር አመላለስ ምጣኔውም በብሄራዊ ባንክ በተቀመጠው ልክ አለመሆኑ፣ የብድር ዋስትና ፈንድ በሁሉም ክልሎች ወጥ በሆነ መልኩ አለመቋቋሙና የከተማ አስተዳደሮችም ገንዘቡን የሚያሰራጩበት መንገድ ለብክነት የሚዳርግ መሆኑ፣ የድህረ ብድር ክትትልና ድጋፍ ባለመደረጉ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ውጤታማ እንዳይሆኑ የብድር አመላለሱም አስቸጋሪ እንዲሆን ማድረጉ፣ የማምረቻና መሸጫ ሼዶች ግንባታ ዝቅተኛ መሆኑና ከተገነቡ በኋላ ለ2 አመታት ያልተላለፉ ሼዶች መኖራቸው እንዲሁም መሰረተ ልማት ስላልተሟላላቸው ያልተላለፉና መሰረተልማት ሳይሟላላቸው ለኢንተርፕራይዞች የተላለፉ ሼዶች መኖራቸው፣ ምን ያህል ኢንተርፕራይዞች ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንደስትሪ እንደተሸጋገሩ ለማወቅ የሚያስችል መረጃ አለመኖሩ እንዲሁም ለማምረቻነትና ለመሸጫነት ተገንብተው ለኢንተርፕራይዞች ከተሰጡ ሼዶች ውስጥ 627 ሼዶች በህገወጥ መንገድ ለሶስተኛ ወገን የተከራዩ መሆኑ በኦዲቱ አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም በኢንተርፕራይዞች መካከል የፊትና የኋላ የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ ለምርታቸውም የመሸጫና የማሳያ ቦታ የማይመቻች መሆኑን፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚከፍሉት የማምረቻና መሸጫ የገበያ ማዕከላት የመጠቀሚያ የአገልግሎት ክፍያ ተመን ወጥ አለመሆኑ እንዲሁም ኢንተርፕራይዞቹ በማዕከላቱ መቆየት ከሚገባቸው 5 አመት የጊዜ ገደብ በላይ የቆዩ ኢንተርፕራይዞች መኖራቸው በኦዲት ግኝቱ ተመልክቷል፡፡
በመሆኑም በነዚህ ጉዳዮችና የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት የመታገያ ስትራቴጂ በመንደፍ ዘርፉ በልማታዊ አስተሳሰብ እንዲመራ እየተደረገ ስላለው ጥረት ማብራሪያ እንዲሰጠው ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡
የመስሪያ ቤቶቹ ኃላፊዎችም ኦዲቱ ያሳያቸው ችግሮች ትክክል እንደሆኑና ከዚህም የባሱ ችግሮች እንዳሉ ገልጸው ለጥያቄዎቹ ዝርዝር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም የብድር ዋስትና ፈንዱ በበቂ ጥናት ላይ ባለመመስረቱ በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ ችግር በመፍጠሩ ምክንያት በአንዳንድ ክልሎች ተጀምሮ እንደቆመና በአዲስ አበባ ላይ ግን እየተሰጠ እንደሚገኝ እንዲሁም የዋስትና ፈንዱን ለመማቋቋምና ለማስተዳደር በብሄራዊ ባንክ መመሪያ ሊዘጋጅለት ስለሚገባ መመሪያው እየተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከሼዶች ግንባታና አስተዳደር ጋር በተያያዘም የሼዶች አቅርቦት ችግር እንዳለ፣ ለገበያና ለስራ ምቹ ያልሆኑ ሼዶች ጥቅም ላይ ሳይውሉ ክፍት ሆነው እንደቆዩ፣ መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው እንዲሁም ግንባታቸው ሳያልቅ ስራ የጀመሩ ሼዶች እንዳሉ፣ ሼዶችን በባለቤትነት በማስተዳደርና በመከታተል ላይ በክልሎች ችግር እንደነበረ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ ጥናት እንደተለየ፣ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሼዶችንና እየተጠቀሙባቸው ያሉ ኢንተርፕራይዞችን የተመለከተ ዝርዝር መዘጋጀቱ፣ ሼዶችን የማስተዳደር የባለቤትነት ችግር እንዲፈታም ሼዶችን የሚያስተዳድር ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ተቋቁሞ ስራዎችን በቢዝነስ አይን አንዲያይ ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
እንደዚሁም ወደ ቀጣዩ የዕድገት ደረጃ ሳይሸጋሩ ቀድሞ የተሰጣቸውን ሼድ ይዘው ያሉትን ኢንተርፕራይዞችን ጉዳይ ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን፣ የሼዶች ግንባታ ላይ ችግር ፈጥሮ የነበረውን የቦታ ችግር ለመፍታት ከመሬት ልማት ኤጀንሲ ጋር እቅድ በማውጣት የሼዶች ዝግጅት መጀመሩን፣ በሼዶቹ መጠቀም ያለባቸውን ኢንተርፕራይዞች በትክክል ለማወቅ ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን እያስተቹ የመለየት ስራ መጀመሩን፣ በሼዶች ግንባታ ላይ በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ያለው ችግር እንዲፈታ መደረጉን ሆኖም ክልሎች ላይ የክትትል ችግር፣ የሰው ሀይል በየወቅቱ መቀያየርና የቁርጠኝነት ችግር እንዳለ ይህንንም ለመፍታት ክትትል በማድረግ ለችግሮች መፍትሄ እየተሰጠ መሆኑንና ለሼዶች የኤሌክትሪክ ሀይል የማቅረብ ችግር እንዲፈታ ራሱን የቻለ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ከመብራት ሀይል ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በክልሎች የኤሌክትሪክ ሀይል የማቅረብ ጉዳይ አስቸጋሪ በመሆኑ ቋሚ ኮሚቴው የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
መረጃን በተመለከተም ኢንተርፕራይዞች ባሉት ስድስት የእድገት ደረጃዎች ውስጥ ወደየትኛው ደረጃ እንደተሸጋገሩ የሚያሳይ በቁጥር የተደገፈ መረጃ እንደሌለ፣ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ሼዶችንና ሼዶቹን እንዲጠቀሙ የተሰጣቸውን አንቀሳቃሾ ማንነት የተመለከተ የተሟላ መረጃ እጥረት እንዳለ፣ በአሁኑ ወቅት የመረጃ መያዣ ሶፍትዌር ተዘጋጅቶ በዘርፉ ያሉ አካላት በኔትዎርክ እንዲተሳሰሩ እየተሰራ እንደሆነና ሴንትራል ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዘርፉ የመረጃ ቋት ሆኖ ወጥነት ያለው የመረጃ ስርአት እንዲፈጠር ከኤጀንሲው ጋር የውል ስምምነት መደረጉን ገልጸው የኔትዎርክ ዝርጋታው ከፍተኛ ወጪ በመጠየቁ ሳይከናወን በመቅረቱ ቋሚ ኮሚቴው የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የገበያ ትስስር መፍጠር ቀድሞም ቢሆን የተጀመረ ስራ እንደሆነ ነገር ግን መንግስት ምርታቸውን እንዲያስተዋውቅላቸውና የገበያ ትስስር እንዲፈጥርላቸው የመጠበቅ ሁኔታ በኢንተርፕራይዞች በኩል እንደሚስተዋል፣ በሌላ በኩልም በአንዳንድ አካባቢዎች የማሳያና የመሸጫ ሼዶች አመቺ ስፍራ ላይ አለመገንባታቸው በገበያ ትስስር ላይ የራሱን ችግር እንደፈጠረ ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡
የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚከፍሉት የማምረቻና መሸጫ የገበያ ማዕከላት የመጠቀሚያ የአገልግሎት ክፍያ ተመን ጋር ተያይዞም እንደየክልሎቹና እንደየማዕከላቱ መገኛ አካባቢዎች ነባራዊ ሁኔታ ታይቶ የሚተመን በመሆኑ ተመኑ ወጥ ሊሆን እንደማይችል ገልጸዋል፡፡
ከ5 አመት በላይ ሼዶችን ሳይለቁ የቆዩ ኢንተርፕራይዞችን በተመለከተም ከጥቃቅንና አነስተኛ ጀምሮ መልካቸውን እየቀያየሩ ያሉ እንዲሁም አሁንም እድገት እንዳላመጡና ቀድሞ በነበሩበት ደረጃ እንደሚገኙ የሚገልጹ ኢንተርፕራይዞች እንዳሉና እነዚህን ለማስለቀቅ ያልተቻለበት አንደኛው ምክንያት ኢንተርፕራይዞቹ የሂሳብ መዝገብ ስለሌላቸውና ሂሳባቸው ስለማይመረመር የደረሱበት የሀብት ደረጃ አለመታወቁ መሆኑን አስረድተው ይህንን ችግር ለመፍታት በአዲስ አበባና በትግራይ የሂሳብ ኦዲት መደብ ወደ መዋቅሩ እንዲገባ፣ ሌሎቹ ክልሎችም ኢንተርፕራይዞች ላይ የሂሳብ ኦዲት እንዲያደርጉ ባለሙያ እንዲመድቡ በማድረግ ስልጠና እንዲሰጥ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩልም ወደቀጣይ የእድገት ደረጃ ለሚሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች በእድገት ደረጃቸው መጠን የቦታ፣የብድር፣ የገበያና የስልጠና ማትጊያ ለመስጠት እንደታሰበ ገልጸዋል፡፡
መልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነትን በመታገል ረገድ የኪራይ ሰብሳቢነት መታገያ እቅድ ተዘጋጅቶ የህዝብ ንቅናቄ እንዲፈጠር ለክልሎች በራሳቸው አግባብ እንዲተገብሩት የተላከ መሆኑን ነገር ግን ክትትሉ ላይ ብዙም እንዳልተሰራ፣ በፌዴራልና በክልል የተቋቋሙ የዘርፍ ምክር ቤቶች ዘርፉን በመምራትና ኪራይ ሰብሳቢነትን በመታገል ረገድ ያላቸውን አፈጻጸም የተለያየና በአንዳንድ አካባቢዎችም የተዳከመ በመሆኑ ከጥልቅ ተሀድሶው ጋር በተያያዘ የመፈተሽና የማጠናከር ስራ እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ያለውን የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ችግር ተከታትሎ ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት፣ ኤጀንሲዎቹ የክትትል ስራን ከዘርፉ ዓላማ ጋር በጥብቅ አስተሳስረው መስራት እንዳለባቸው፣ ለሁሉም ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ፍትሀዊ አሰራርን መከተል እንደሚገባ፣ ኢንተርፕራይዞች ወደ ቀጣዩ የእድገት ደረጃ ሳይሸጋገሩ ባሉበት ለመቀጠል የሚያሳዩትን አዝማሚያ ለማስቀረት ክትትሉ መጠንከር እንዳለበት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ሁለቱንም ኦዲቶች በተመለከተ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ዋና ኦዲተሩ የፋይናንስ ኦዲቱን አስመልክተው ለስልጠና ተከፈለው የውሎ አበል ለትክክለኛው ኃላፊ መከፈሉ ተጣርቶ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት፣ የስልጠናው ቆይታም ተጣርቶ የተከፈለው ክፍያ ትክክለኛ መሆኑ መረጋገጥ እንደሚገባው እንዲሁም ማስረጃ ያልቀረበበት የትራንስፖርት ክፍያ ተጣርቶ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ክቡር አቶ ገመቹ በክዋኔ ኦዲቱ ላይ ሲናገሩም በዘርፉ ጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾችን በሂደት ወደ መካለለኛ እንዱስትሪ ደረጃ ለማሸጋገር የተጣለው ግብ መሳካቱ ሊለካ የሚችለው በዘርፉ ስለተፈጠረው የስራ እድልና ስለተሸጋገሩት ኢንተርፕራይዞች ትክክለኛ መረጃ ሲኖር በመሆኑ ለመረጃ አያያዝ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ፣ የብድር አመላለስ ምጣኔው ያሳየው እድገት ጥሩ ቢሆንም ወደሚፈለገው ደረጃ እንዲደርስ ማድረግ እንደሚገባ፣ የብድር ስርጭቱን በማሳደግ የተጠቃሚዎቹን ቁጥር ማሳደግ እንደሚያሻ፣ ዘርፉ በርካታ ችግሮች የሚታዩበት በመሆኑ መንስኤያቸውን ለይቶ ስትራቴጂ አዘጋጅቶና ስርዐት ዘርግቶ መስራት እንደሚያስፈልግ፤ ተገንብተው ስራ ላይ ያልዋሉ፣ መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸውና ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ ሼዶችን ተከታሎ ማስተካከል እንደሚገባ፣ ወደ ቀጣይ የእድገት ደረጃ የሚሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞችን መከታተል እንዲሁም መነሻ (baseline) የሚሆን መረጃ መያዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ክቡር ዋና ኦዲተሩ በተጨማሪም በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት መሀከል እንዲሁም ከሌሎች የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ጋር ትስስር እንዲጠናከር ማድረግና በትስስር ረገድ ያሉ ችግሮችን ፈትሾ ማስተካከል
እንደሚያስፈልግ፣ ከሼድ ለሚለቁ አንቀሳቃሾች በቂ ድጋፍ የሚሰጥበትና ራሳቸውን እስኪችሉ ተጨማሪ የስራ እድልና ገቢ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያሻ፣ የብድር ዋስትና ከማመቻቸት ጎን ለጎን መንግስት ዋስ ሆኖልናል በሚል ብድር ያለመመለስ የመለካከት ችግር ያልተለወጠበትን ምክንያት ማጥናት እንደሚያስፈልግ፣ የኦዲት ግኝቱን እንደመነሻ በመያዝ ችግሮችን አስፍቶ ማየትና የስትራቴጂ ክለሳ የሚያስፈልግ ከሆነም ማጤን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት በማጠቃለያ አስተያየታቸው ኤጀንሲዎቹ የኦዲቱ ግኝቱን ተቀብሎ ችግሮችን ለማረም የሰጡት ትኩረትና ያደረጉት ጥረት በጥሩ ጎን የሚታይ መሆኑን ገልጸው በጥቅሉ የተቋሙ ችግሮች የአፈጻጸም፣ የቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም የመረጃ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ክቡር አምባሳደር መስፍን አያይዘውም የፋይናንስ አስተዳደር ስርአቱን እያጠናከሩና የሰው ሀይሉን አቅም በተከታታይ እየገነቡ መሄድ እንደሚያስፈልግ፣ ሰፊ የስራና የገበያ እድል መፍጠር በማክሮ ኢኮኖሚ
የተቀመጠ ትልቅ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ከሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ግቦች ጋር እየተገናዘበ ዘርፉ በትክክለኛው አቅጣጫ መሄዱ መመዘን እንደሚኖርበት፣ በክትትልና ድጋፍ ረገድ ያሉ ጉድለቶች በፍጥነት መፈታትና ስራዎቹም መጠናከር እንዳለባቸው እንዲሁም ኮርፖሬሽን ተቋቁሞ ስራዎችን በቢዝነስ እይታ አንዲያይ ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱ ጥሩ እንደሆነና በዚህ ሳያቆም ዘርፉ አሁን ያለው አደረጃጀትና አወቃቀር በቂ ድጋፍ መስጠት ስለማስቻሉ እየፈተሸ መሄድ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
ሰብሳቢው አክለውም የኤጀንሲውንና የክልሎችን ሚናና የቅንጅት ስራውን በጥብቅ መፈተሽ እንደሚገባ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ጉዳይ አሁን ካለው በላይ በጥልቀት ማየትና መታገል እንደሚያስፈልግ፣ ኢንተርፕራይዞች ወደቀጣዩ የእድገት ደረጃ የሚያደርጉት ሽግግር በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ መሆኑን መከታተልና ማረጋገጥ እንደሚገባ፣ ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ላሉ የገበያ ትስስሮች ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ፣ ከተያዘው የጥልቅ ተሀድሶ እንቅስቃሴ አንጻር በተቋማቱ የጀመረውን መነቃቃት ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ለኔትዎርክ ዝርጋታ ከሚያስፈልገው ገንዘብና ከኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለቀረቡት የድጋፍ ጥያቄዎችም ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እገዛ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡