የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት የ2013 በጀት ዓመት የፋይናንስ አሠራርና ንብረት አስተዳደር አፈጻጸም ላይ ባካሄደው የሂሳብ ህጋዊነት ኦዲት መሰረት በርካታ የህግና የመመሪያ ጥሰቶች መታየታቸው ተገለጸ፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰኔ 07 ቀን 2015 ዓ.ም ከኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት አካሂዷል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ብር ከ3.9 ሚሊየን በላይ በወቅቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ አለማድረጉን፣ በስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት የተሟላ ዝርዝር ደጋፊ ሰነድ ሳይቀርብ ብር 254,858.53 በወጪ መመዝገቡን፣ ያለአግባብ 32 ሺህ ብር በላይ ለውሎ አበል ክፍያ መፈጸሙን እንዲሁም ስራ ለለቀቁ ሠራተኞች በድምሩ ብር 34,717.73 ያለአግባብ ክፍያ መፈጸሙ በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በፋይናንስ ደንብና መመሪያ መሠረት ብር 171,919,447.38 ያልተሰበሰበ እና ብር 55,744,257.74 ተከፋይ በወቅቱ ያልተወራረደ ሒሳብን ጨምሮ ያለበጀት አመት የተወራረዱ ሂሳቦች፣ ያለበቂ ማስረጃ የተከፈሉ ክፍያዎች፣ በትክክለኛ መደብ ያልተመዘገበ ሂሳብ፣ ከ10 % በላይ ሥራ ላይ ያልዋለ በጀት መኖሩ እና በ2013 በጀት ዓመት የግዢ እቅድ አለመዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
ከንብረት አያያዝ አኳያም ሊብሬ የሌላቸው 8 ተሸከርካሪዎች መገኘታቸውን፣ የሒሳብ ሰነዶች በአግባቡ ተደራጅተው የማይቀመጡ መሆኑ እና በ2010፣ በ2011 እና በ2012 በጀት ዓመት ማስተካከያ እንዲደረግባቸው አስተያየት በተሰጠባቸው ግኝቶች ላይ እርምጃ አለመውሰዱ ተገልጾ የተቋሙ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ሀብቶም ገ/እግዚአብሔር እና የፋይናንስ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በአብዛኞቹ የኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃዎች መወሰዱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በ2013 በጀት ዓመት በወቅቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ ሳይደረግ የቆየ ሂሳብ ፈሰስ መደረጉን፣ ከስልክና ኢንተርኔት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ እያንዳንዱ የሥራ ክፍል የሚጠቀምበት የአገልግሎት ክፍያ ዝርዝር ተመን ማዘጋጀቱን፣ ያለአግባብ ለውሎ አበል የተከፈለ ሂሳብ ሙሉ በሙሉ ተመላሽ መደረጉን እንዲሁም በተሰብሳቢ እና በተከፋይ ሂሳቦች ላይ ሰፊ ሥራ በመስራት የተሰብሳቢ ሂሳብ 171 ሚሊየን በላይ ከነበረበት ወደ 95 ሚሊየን ዝቅ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ሊብሬ ከነበራቸው 8 ተሸከርካሪዎች ውስጥ 4ቱ እንዲኖራቸው ማድረግ የተቻለ ሲሆን ቀሪዎቹም እንዲኖራቸው ከሚመለከተው መ/ቤት ጋር እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም ለተከታታይ አመታት ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት አስተያየት ሲሰጠው የቆየ መ/ቤት እንደነበር አስታውሰው ተቋሙ ከነበረበት ችግር እንዲወጣ በፌዋኦ በኩል ለሙያተኞቻቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መሰጠቱን እና በዚህ በተሠራው ሥራም በዘንድሮ አመት በተደረገ ኦዲት የነበረባቸውን በርካታ ችግሮች ማሻሻል የቻሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ኢንስቲትዩቱ በወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች በ2013 በጀት ዓመት በኦዲት ግኝትነት ከታዩት ውስጥ ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ ሳይደረግ የቆየ ሂሳብ ፈሰስ ማድረጉን፣ የስልክና ኢንተርኔት አጠቃቀሙን ማስተካከሉን፣ ከመመሪያ ውጪ በብልጫ የተከፈለ ክፍያ መስተካከሉን፣ የግዢ እቅድ መዘጋጀቱን፣ በተሰብሳቢ እና በተከፋይ የነበረባቸውን ያልተወራረደ ሂሳብ የኦዲት ኮሚቴ አዋቅረው ችግሮቹን ለመቅረፍ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኢንስቲትዩቱ አሁንም ያልተሻገራቸው ችግሮች እንዳሉ ዋና ኦዲተሯ ገልጸው በተለይም ክፍያዎች ሲፈጽሙ ህግና መመሪያ ሊከተሉና ያለአግባብ የተከፈሉ ክፍያዎች ተመላሽ ሊደረጉ፣ ቀሪ ያልተሰበሰቡ እና ያልተከፈሉ ሂሳቦች ሊወራረዱ፣ የበጀት አጠቃቀማቸውን በእቅድ ሊመራ እንዲሁም ሊብሬ ያልወጣላቸው ተሸከርካሪዎች ሊወጣላቸው እንደሚገባ ገልጸው የጀመሩትን የማሻሻያ እርምጃ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው ተቋሙ ከነበረበት ተከታታይ የኦዲት ችግር ለመውጣት ያደረገውን ጥረት ቋሚ ኮሚቴው እውቅና የሚሰጠው መሆኑን ገልጸው ነገር ግን በርካታ ህግና መመሪያን እንዲሁም የአሠራር ሥርዓቶችን ተከትሎ ያለመስራት ችግሮች እንዳይቀጥሉ አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ስራዎችን በእቅድ ላይ ተመርኩዞ እንዲሰራ ማሳሰቢያ የሰጡት ሰብሳቢው የግኝት ማስተካከያ የድርጊት መርሀ ግብር በ10 ቀናት ውስጥ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በሚመለከታቸው የተቋሙ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አቀጥጫ ሰጥተዋል፡፡