News

ኢንስቲትዩቱ ለኦዲት ግኘት ትኩረት አልሰጠም ተባለ

የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ለኦዲት ግኝት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ አለመሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የ2013/14 በጀት ዓመት የእንስሳት ብዝሀ ህይወት ሀብት አጠባበቅ እና አጠቃቀም ላይ የተካሄደውን የክዋኔ ኦዲት አስመልክቶ ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ነው፡፡

ብዝሀ ህይወትን በሚመለከት የህይወታዊ ሀብት ጥበቃና ምርምር ብሔራዊ ፖሊሲ ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ አለመከለሱ፣ የእንስሳት ጥበቃና አጠቃቀም በተመለከተም የወጣ ፖሊሲ አለመኖሩ እና ለማዕከላትና ለባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና ቴክኒካዊ ድጋፎች ላይ ውስንነት መኖሩ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

የብዝሀ ህይወት ናሙና ከውጭ አገር ለማስመጣት እና ከመጡ በኋላም አወጋገዳቸው ላይ መመሪያ አለመኖሩ፣ የብዝሀ ህይወት ናሙና ከውጭ አገር እንዲገባም ፈቃድ የሚሰጡት የተለያዩ የመንግስት ተቋማት በመሆናቸው የሀላፊነት መደራረብ መኖሩ እና እየተመናመኑ ላሉ ዝርያዎችም ተገቢው ትኩረት እየተሰጠ እንዳልሆነ ተነስቷል፡፡

ህብረተሰቡ ለዘርፉ ያለው ግንዛቤም ዝቅተኛ መሆኑ፣ እንደ ሀገር የብዝሀ ህይወት ሀብት ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት አለመዘርጋቱ እንዲሁም በኢንስቲትዩቱ የላብራቶሪ ግንባታ በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ተጨማሪ ወጪ መጠየቁ እና በፍቼ ከተማ የዘረ-መል (Gene) ባንክ ግንባታው ሳይጠናቀቅ ርክክብ መከናወኑ በውይይቱ ላይ የተነሱ ተጨማሪ ግኝቶች ናቸው፡፡

የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፈለቀ ወልደየሱስ በሰጡት ምላሽ የእንስሳት ጥበቃና አጠቃቀምን በተመለከተ እንደሀገር እንጂ እንደ ኢንስቲትዩት ፖሊሲ እንደማይወጣ አብራርተው ከአቅም ግንበታ ጋር ተያይዞ ያለው ክፍተት የበጀት እና የማቴሪያል ውስንነት በመኖሩ የተፈለገውን ያህል መስራት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም የብዝሀ ህይወት ናሙና ከውጭ አገር ለማስመጣትም ሆነ ወደ ውጭ ለመላክ ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉ፣ አገር በቀል ዝርያዎችም በህገወጥ መንገድ ከአገር እየወጡ እንደሆነና ይህም በተቋሙ የሚፈታ ሳይሆን በክልል ደረጃ መፈታት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ከፍቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞም የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ላይ የሀላፊነት መደራረብ በመኖሩ ለስራቸው ፈተና እንደሆነባቸው ዶ/ር ፈለቀ ጠቁመዋል፡፡

ከክትትልና ቁጥጥር ጋር ተያያዞ ኢንስቲትዩቱ ከሪፖርት መላላክ ጀምሮ የመስክ ምልከታ እስከማድረግ እና ግብረ መልስ የመስጠት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ም/ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው የዘረ-መል (Gene) ባንክ ግንባታ ርክክብ የተደረገው አንዱ ህንጻ በመጠናቀቁ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በኢንስቲትዩቱ የተሰጡ ምላሾች የኦዲት ግኝቶቹን በተገቢ ሁኔታ ያልዳሰሱ እና ተቋሙ ከዚህ ቀደም በድርጊት መርሀ ግብር ካሳወቀው ምላሸች የተለየ ሥራ መከናወኑን የማያሳዩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች የኦዲት ባለድርሻ አካላት ዘርፉ ከፍተኛ ገቢ የሚገኝበት እና በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ያለው መሆኑን ጠቅሰው ኢንስቲትዩቱ ህግና ስርዓት ዘርግቶ ከመስራት አኳያ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

አያይዘውም ኢንስቲትዩቱ በዘፈቀደ ሳይሆን በእውቀት እና በክህሎት መመራት እንዳለበት ጠቁመው ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና መመሪያ በማዘጋጀት እና የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ውሱን የሆነውን የብዝሀ ህይወት ሀብት በአግባቡ መጠበቅ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው በኦዲቱ ወቅት ዝግጅቱ 95 በመቶ እንደደረሰ ሪፖርት የተደረገው ፖሊሲ እስከአሁን አለመጽደቁ እና ሌሎች አስፈላጊ መመሪያዎች አለመዘጋጀታቸው ኢንስቲትዩቱ የአዲት ግኝቶችን ለማሻሻል የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የዘርፉን ተጠቃሚነት ላሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አስራር ማጠናከር፣ የብዝሃ ህይወት መዘክርን በአግባቡ ማደራጀት፣ እንደሀገር የብዝሃ ህይወት ያለበትን ደረጃ መከታተተል የሚያስችል ጠንካራ የቁጥጥርና የክትትል ስርዓት መዘርጋት እና ህብረተሰቡ በዘርፉ ያለው ግንዛቤ እንዲያድግም ተከታታይና ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ማዘጋጀት እንዳለበት ዋና ኦዲተሯ አሳስበዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አረሬ ሞሲሳ በበኩላቸው የኦዲት ግኝቶቹን መነሻ በማድረግ ኢንስቲትዩቱ እስከአሁን መሠረታዊ ማስተካካያዎችን አለመደረጉን እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተናቦ ከመስራት አኳያም ክፍተቶች እንዳሉበት ጠቁመዋል፡፡

አክለውም ኢንስቲትዩቱ የኦዲት ግኝቶች ላይ የማሻሻያ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የተከለሰ የድርጊት መርሀ ግብር በማዘጋጀት ለቋሚ ኮሚቴውና ለባለድርሻ አካላት ሪፖርት እስከ ሚያዚያ 30 እንዲያቀርብ፣ ፖሊሲ እና መመሪያዎችን አፀድቆ እስከ ግንቦት 30 እንዲያቀርብ  ም/ሰብሳቢዋ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በተጨማሪም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በሚመለከት የሚሰሩ ስራዎች በየሶስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርብ፣ ተቋሙ ተጠሪ የሆነለት የግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም የጋራ መመሪያና እቅድ በማዘጋጀት ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡:

ሙሉ የመድረኩን ሂደት ለማየት የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ

https://www.facebook.com/search/top/?q=house%20of%20peoples%20representatives%20of%20fdre

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *