News

አገልግሎቱ የኦዲት ግኝቶችን ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ጥረት ማጠናከር አለበት ተባለ

የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2014/2015 ኦዲት ዓመት ባደረገው #የክዋኔ_ኦዲት የታዩ ግኝቶችን ለማስተካከል እየወሰደ ያለውን እርምጃ ማጠናከር እንዳለበት ታህሳስ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በተካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት መድረክ ተገለጸ፡፡

አገልግሎቱ ለፌዴራልና ለአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኞች በስራ ቀናት የደርሶ መልስ የተሟላ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ውል ከገባው የሠራተኛ ቁጥር በታች የሆነ አገልግሎት በማቅረብ ከፍያውን ግን በውሉ መሰረት ሙሉ ክፍያ እንደሚሰበስብ በኦዲቱ ወቅት መታየቱ በመድረኩ ተነስቷል፡፡

በተጨማሪም በአውቶቡስ እጥረት ሳቢያ ተገልጋዮች ረጅም መንገድ ቆመው እንደሚሄዱና እንግልት እንደሚስተዋል፣ የተገልጋዮች እርካታ ደረጃም ዝቅተኛ መሆኑን፣ የሚዘለሉ ፌርማታዎች መኖራቸውን ጨምሮ በሌሎች አሠራሮች ላይ ክፍተቶች መኖራቸው በመድረኩ ተነስቶ ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው ተጠይቋል፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬህይወት ትልቁ እና ሌሎች በመድረኩ የተገኙ የአገልግሎቱ አመራሮች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የኦዲት ግኝቶቹ ትክክለኛ መሆናቸውን ገልጸው ከኦዲቱ በኋላ በተሰጡ የኦዲት ግኝት አስተያየቶች መሰረት በርካታ ማስተካከያዎች መደረጋቸውንና በመታወቂያ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ጨምሮ ቀሪ ግኝቶችንም ተገቢ የቴክኖሎጂ ስርዓት በመዘርጋት ለማስተካከል ጥረት እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) በበኩላቸው ጥረቱን ማጠናከርና በተለይም የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ሠራተኞች ቁጥር በውሉና በሚከፈለው ክፍያ መጠን ያልሆነበትን ምክንያት መለየት እንደሚያስፈለግ ገልጸው ሚኒስቴር መ/ቤታቸው ለተቋሙ ቦርድ ቸግሮቹን ለመፍቅረፍ የሚያስችል አቅጣጫ እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ በሰጡት አስተያየት ከኦዲቱ በኋላ ማስተካከያ እንደተወሰደባቸው የተገለጹ ግኝቶች በቀጠይ የክትትል ኦዲት የሚረጋገጡ መሆኑን ጠቅሰው የአውቶብሶችን ቁጥር ለመጨመርና ሌሎች ማስተካከያዎችን ለማድረግ በድርጊት መርሀ ግብር የተቀመጡ ተግባራት በምን ደረጃ ላይ እደሚገኙና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሮችን ለመፍታት እየተደረገ ስላለው ጥረት ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

#የፌዴራል_ዋና_ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ #መሰረት_ዳምጤ በበኩላቸው ኦዲቱ የተቋሙን የትራንስፖርት አገልግሎት ስታንዳርድና መመሪያ አፈጻጸም፣ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር የትኩረት አቅጣጫ መሠረት በማድረግ የተካሄደ መሆኑን ገልጸው ተቋሙ ግኝቶችን ለማስተካከል እየወሰደ ያለው የማስተካከያ እርምጃ አበረታች ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ ገንዘብ ሚኒስቴርና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለፌዴራልና ለከተማው አስተዳደር ሠራተኞች ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚከፍሉት ክፍያ ከተቋሙ የትራንስፖርት አገልግሎት የማቅረብ አቅም ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን፣ መንግስት ለሠራተኞች የዘረጋው የትራንስፖርት ስርዓት አጠቃላይ በሠራተኛው መደበኛ የስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ ተጽዕኖ ያለው በመሆኑም አገልግሎቱ የትራንስፖርት አቅርቦት ውስንነቱን ሊቀርፍ ይገባል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ከአገልግሎቱ የሚገኘው እርካታ የሠራተኛው ብቻ ሳይሆን የመንግስትም ጭምር መሆኑን የጠቀሱት ዋና ኦዲተሯ የገቢ ፈሰስ በየዓመቱ መደረግ ያለበት መሆኑንና ፌርማታ በሚዘሉ የአውቶቡስ ካፒቴኖች ላይም ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አሳስበዋል፡፡

በቴክኖሎጂ የተደገፈው የክትትልና የቁጥጥር ስርዓት የመረጃ ትንተና በወቅቱ ሳይቆራረጥ መሰራት እንዳለበት፣ ተገልጋዮች መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ፣ የአሠራር መመሪያዎችም በተቋሙ ቦርድ እንጂ በማኔጅመንት መጽደቅ እንደሌለባቸው እንዲሁም ለአገልግሎቱ ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ በሚል የሚካሄዱ ሌሎች የኮንትራትና ተመሳሳይ ተጨማሪ አገልግሎቶች በቅድሚያ ተቋሙ የተቋቋመበትን ለሠራተኛው የትራንስፖርት አገልግሎት የማቅረብ ዓላማን ያስቀደሙ መሆን ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማዘመን የሚደረገው ጥረት እና አደጋን 0% ለማድረስ ግብ አስቀምጦ መስራቱ በጥሩ ጎኑ የሚታይ መሆኑን ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሳብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በውይይቱ ማጠቃለያ በሰጡት አስተያየት የፐብሊክ ሰርቪስ የትራንስፖርት አገልግሎት የተጠቃሚዎችን እርካታ ታሳቢ አድርጎ መሥራት ስላለበት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ሹፌሮች ፌርማታዎችን ጠብቀው መጫንና ማውረድ አለባቸው ብለዋል፡፡

የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የተቋቋመው የመንግሥት ሠራተኞች በጊዜ ገብተው ሥራቸውን እንዲሠሩና ወደ ቤታቸው ሲሄዱም የትራንስፖርት ችግር እንዳያጋጥማቸው ታስቦ በመሆኑ አገልግሎቱ ገቢ ለማግኘት መሥራት ያለበት በመጀመሪያ ለመንግሥት ሠራተኛው የትራንስፖርት አገልግሎት በአግባቡ ከሰጠ በኋላ መሆን እንዳለበት እንዲሁም ግኝቶችን ለማስተካከልና አሠራሩን ለማዘመን ተቋሙ የበለጠ መስራት እንደሚኖርበት የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ አሳበዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *