News

አገልግሎቱ ዜጎች ያልተገባ ነገር ውስጥ እንዳይገቡ የእድል ሎተሪ የሚያጫውቱ አካላትን በጥንቃቄ ሊቆጣጠር እደሚገባው ተገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት በፍቃድ ለሚሰሩ ሌሎች አካላት የዕድል ሎተሪ እንዲያጫውቱ የሚያደረግበት የፍቃድ አሰጣጥ እና ገቢ አሰባሰብ ኢኮኖሚያዊ፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ መሆኑን በተመለከተ ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት የታዩ ግኝቶች መስተካከል እንዳለበት ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በምክር ቤቱ በተካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ወቅት አገልግሎቱ የህግ ማዕቀፎችን አጠናቆ ወደ ሥራ ከማስገባት፣ ከእድል ሎተሪ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት፣ ከክትትልና ቁጥጥር፣ ከመረጃ አያያዝ፣ ከገቢ አሰባሰብ፣ ዘርፉን በቴክኖሎጂ ከማዘመን እና ህገወጥነትን ከመከላከል አኳያ በታዩ እና በሌሎች በተለዩ የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ላይ ተቋሙ ተጨባጭ የእርምት ማስተካከያ አለማድረጉ ተገልጿል።

የኦዲት ግኝቶችን ለማሻሻል አገልግሎቱ የወሰዳቸውን እርምጃዎችን እንዲብራሩ በቋሚ ኮሚቴው የተጠየቀ ሲሆን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ም/ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ኃ/ማርያም እና የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ቤዛ ግርማን ጨምሮ ሌሎች በመድረኩ የተገኙ የአገልግሎቱ የሥራ ሀላፊዎች የኦዲት ግኝቶቹ እና መድረኩ ለቀጣይ ስራቸው ጠቃሚ ግብአቶች ያገኙባቸው መሆኑን ገልጸው እየተወሰዱ ስላሉት የማስተካከያ እርምጃዎች ዝርዝር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አመራሮቹ በምላሻቸው አብዛኞቹ የስፖርት ቤቲንግ ማጫወቻ ቤቶች ተዘግተው ወደ ኦንላይን ሥርዓት መዞራቸውን፣ ትክክለኛ ፈቃድ ያወጡ ቤቲንግ ቤቶች እንዲቀጥሉ መደረጉን፣ የእድል ሎተሪ ማጫወቻ መተግበሪያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶች ያሏቸው እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ገልጸው አገልግሎቱ በኦዲቱ የተመላከቱ አብዛኛዎቹን ግኝቶች ለማስተካከል በገቢዎች ሚኒስቴር በኩል መሻሻል ያለበት መመሪያ አለመጠናቀቅ መሠረታዊ ችግር እንደሆነባቸው አንስተዋል፡፡

ኦዲቱ ከመነሻው ጀምሮ የተካሄደበትን ሂደት እንዲሁም የኦዲቱን የትኩረት አቅጣጫ በማብራራት አስተያየታቸውን የሰጡት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የአገልግሎት መ/ቤቱን መቋቋሚያ አዋጅ ተከትሎ መውጣት የነበረበት ደንብ እለመውጣቱን እና መመሪያዎችም አለመሻሻላቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይ የገቢዎች ሚኒስቴር መመሪያውን ማሻሻል እንደነበረበት ያወሱት ክብርት ዋና ኦዲተሯ በት/ቤቶች አከባቢ ህገወጥ ሥራ ይሠሩ የነበሩ ማጫወቻ ቤቶች መዘጋጀታቸው ተገቢ ቢሆንም አገልግሎት መ/ቤቱ አስቀድሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅታዊ ሥራ መስራትና በህገወጦች ላይም ተጠያቂነት ማረጋገጥ ይጠበቅበት እንደነበር አንስተዋል፡፡

ክብርት ዋና ኦዲተሯ አክለውም ዘርፉ በሌሎች ሀገራት ብዙ ገቢ ከሚሰበሰብባቸው ዘርፎች አንዱ መሆኑን አውስተው የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎትም እይታውን ሰፋ በማድረግ ከዘርፉ የተሻለ ገቢ መሰብሰብ የሚቻልበትን ህጋዊ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

አገልግሎቱ በቀጣይ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ በየ3 ወሩ ለተገቢው አካላት የአፈፃፀም ሪፖርት እንዲያቀርብ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የማጠቃለያ አስተያት የሰጡት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ አገልግሎቱ ዜጎች ባልተገባ መንገድ ላልተገባ ነገር እንዳይጋለጡ የእድል ሎተሪ የሚያጫውቱ አካላትን በጥንቃቄ ሊቆጣጠር እደሚገባ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ሎተሪ አገልገሎት መመሪያ ማሻሻል ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በመሪነት የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎትን፣ የፍትህ ሚንስቴርን እና የገቢዎች ሚኒስቴርን በቅንጅት በማወያየትና መፍትሔ በማስቀመጥ በ2018 ዓ.ም ምክር ቤቱ ሲከፈት የደረሱበትን ውጤት ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲያቀርብ ምክትል ሰብሳቢዋ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *