የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የጤና መድህን ተደራሽነትና የገቢ አሰባሰብ ቀልጣፋነትና ውጤታማነት አፈጻጸምን ለማረጋገጥ በ2013/2014 በጀት ዓመት ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት አካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት በበቂ ሁኔታ በጤና መድህን ዙሪያ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የማይሰጥ፣ ለጤና መድህን ተጠቃሚ አዲስና ነባር አባላት ምዝገባና እድሳት በወቅቱ የማያደርግ እና ለአባላቱ የአባልነት መታወቂያ በወቅቱ እያዘጋጀ የማይሰጥ መሆኑ በኦዲቱ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል አገልግሎቱ የጤና መድህን ሥርዓትን ለማስፋት የሚያደርጋቸውን ጥናቶች በወቅቱ አጠናቆ ተግባራዊ ያለማድረጉ፣ ከማህበረሰብ አቀፍ ተቋማት የሚሰበሰበው ገንዘብ በወቅቱ ስለመሰብሰቡ እና ወደ ባንክ ገቢ ስለመደረጉ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር የማያደርግ መሆኑን እንዲሁም የጤና መድህን አገልግሎት በተሟላና ጥራቱን በጠበቀ አግባብ እየተሰጠ ስለመሆኑ በአግባቡ ክትትል የማያካሂድ መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈም አገልግሎቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር መድረኮችን በማዘጋጀት የልምድ ልውውጥ የማያደርግ፣ አቤቱታዎችንና ቅሬታዎችን ተቀብሎ መፍትሔ የማይሰጥ እንዲሁም ዘመናዊ የሆነ የመረጃ አሰባሰብና አያያዝ ሥርዓት ያልዘረጋ መሆኑ ተገልጾ አገልግሎቱ ከኦዲቱ በኋላ በግኝቶቹ ላይ ምን የማስተካከያ እርምጃ እንደወሰደ ማብራሪያ ተጠይቋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እና የአገልግሎቱ የሥራ ኃፊዎች በተነሱት ጥያቄዎች እና የኦዲት ሪፖርቱን ተከትሎ በወሰዷቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው ኦዲቱን ተከትሎ ህብረተሰቡ በጤና መድህን ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ሰፋፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሰራታቸውን፣ ከአባልነት ምዝገባና እድሳት ጋር ያሉ ችግሮች በየደረጃው እየተስተካከሉ እንደሚገኙ፣ በጤና መድህን ዙሪያ በርካታ ጥናቶች መሠራታቸውን እና ጥናቶቹን መሠረት ያደረጉ የአሠራር ሥርዓቶችም እንዲቀየሩ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል፡፡
ለጤና መድህን ከተጠቃሚዎች የሚሰበሰበውን ገንዘብ በተመለከተም አንዳንድ ቦታ የተሰበሰበው ገንዘብ ለተገቢው አካል በአግባቡ የማይተላለፍ እና ከዓላማው ውጭ የማዋል ሁኔታዎች እንዳሉ ክብርት ሚንስትሯ ጠቁመው በየጊዜው የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓታቱን በማጠናከርና ግንዛቤን በማሳደግ የሚሰበሰበው ገንዘብ በወቅቱ ገቢ እንዲደረግ ክትትሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
አያይዘውም የጤና መድህን አገልግሎት ሥርዓት ቀልጣፋና ውጤታማ ሆኖ ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችል ዘመናዊ የመረጃ ቋት እንዲፈጠር እንዲሁም ጠንካራ የፋይናንስ አቅም እንዲገነባ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ክብርት ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል፡፡
ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው አገልግሎቱ ለኦዲቱ ትኩረት በመስጠት ችግሮቹን ለማሻሻል የሄደበት እርቀት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው አዲስ መታወቂያ ከማውጣትና ነባሩን ከማደስ ጋር ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አገልግሎቱ ስልት ቀይሶ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
የፌደራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው አገልግሎቱ በኦዲቱ የታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የወሰዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች በሚኒስቴር መ/ቤቱ ጭምር የቅርብ ክትትልና ድጋፍ መኖሩን የሚያመለክት መሆኑን ገልጸው ይህ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
በጤና መድህን አገልግሎት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በቀጣይነት መጠናከር እንደሚኖርባቸውና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችም በየጊዜው መፍትሔ ሊበጅላቸው እንደሚገባ የጠቀሱት ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በተለይም ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር ያሉ ግንኙነቶች መጠናከር እንደሚኖርባቸው እና የመታወቂያ አጠቃቀም፣ የገቢ አሰባሰብ እና የመረጃ አያያዞች በቴክኖሎጂ ሊደገፉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሰሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በማጠቃለያ በሰጡት አስተያየት ቋሚ ኮሚቴው በአገልግሎቱ የተወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎችን በአዎንታዊ መልኩ የሚመለከተው መሆኑን ገልጸው ነገር ግን ከገቢ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ በተለይም በክልሎች በአግባቡ ተሰብስቦ ወደ ባንክ ገቢ እንዲደረግ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በቀጣይም የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ በ10 ቀናት ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴውና ለሚመለከታቸው አካላት እንዲቀርብና የማሻሻያ እርምጃ አፈጻጸሞችም በየሶስት ወራት እንዲቀርቡ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በሚመለከታቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተቋሙን ለተሻለ ስራ የሚያበቁ የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን እንዲሰሩ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡