News

አዲስ ለተቀጠሩ ኦዲተሮች የትውውቅ /Induction/ ስልጠና ተሰጠ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አዲስ ለተቀጠሩ ጀማሪ ኦዲተሮች የትውውቅ /Induction/ ስልጠና ሰጠ፡፡
ስልጠናው ከመስከረም 18-24/2015 ዓ.ም ድረስ በመ/ቤቱ የስልጠና ክፍሎች የተካሄደ ሲሆን የተለያዩ የስራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ የኦዲት ባለሙያዎች በአሰልጣኝነት እንዲሁም በጥቅሉ 28 አዲስ የተቀጠሩ ጀማሪ ኦዲተሮች በሰልጣኝነት በስልጠናው ተሳትፈዋል፡፡
የስልጠናው ዓላማ ሰልጣኝ ኦዲተሮቹ ለመ/ቤቱ የአሠራር ስርዓት አዲስ እንደመሆናቸው የተቋሙን አሰራር በማሳወቅ የኦዲት ማንዋሉን አውቀውና ተገንዝበው ሥራቸውን በአግባቡና በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት እንዲሰሩ ማስቻል እና ሥራቸውን ሲያከናውኑም ሁለንተናዊ የኦዲተር ሥነ-ምግባርን የተላበሱ እንዲሆኑ ግንዛቤ ለማስጨበጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው የመ/ቤቱን ደንብና መመሪያ፣ በመቤቱ ውስጥ ተግባራዊ እየተደረጉ ስለሚገኙ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓቶች፣ አጠቃላይ የኦዲት አሰራር እንዲሁም ሥነ-ምግባርን የተመለከቱ ይዘቶችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል፡፡
በስልጠናው የማጠቃለያ መርሀ ግብር ላይ የተገኙት የፌዋኦ ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በህዝብና በመንግስት ትልቅ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም መሆኑን ጠቁመው ይህን ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት ሁለጊዜም ራስን ማብቃት እና ስነ-ምግባር ተላብሶ በቡድን መንፈስ መስራት ከኦዲተሩ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡
ም/ዋና ኦዲተሩ አክለውም የትውውቅ ስልጠና የሚሰጠው ጀማሪ ኦዲተሮች ስለተቋሙ ምንነትና የሥራ ባህል ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል መሆኑን ገለጸው ከስልጠናው የተገኘውን እውቀት ወደተግባር መለወጥ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ሰልጣኞች በስልጠናው ማጠቃለያ በሰጡት አስተያየት በርካታ የኦዲት አሠራር ዕውቀቶችንና ክህሎቶችን ከስልጠናው እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ስልጠናው ቀደም ሲል በንድፈ ሀሳብ የነበራቸውን ውስን ዕውቀት ማሳደግ የቻሉበት፣ ዕውቀታቸውን እንዴት በተግባር ማዋል እንደሚገባቸው መሰረታዊ ግንዛቤ ያገኙበት እና ስለተቋሙ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስቻለ እንደነበር አመላክተው ለወደፊቱም ከሚሰሩት ሥራ ጋር በቀጥታ የተገናኙ ጉዳዮች ላይ በቀጣይ መሰል ስልጠናዎች እንዲዘጋጁላቸውም ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት መ/ቤቱን ለሚቀላቀሉ አዳዲስ ኦዲተሮች የትውውቅ፣ እንዲሁም ለነባር ኦዲተሮች የሙያ ማሻሻያ ተከታታይ ስልጠናዎችን ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የውስጥና የውጭ አሰልጣኞች በማካሄድ የሠራተኞቹን አቅም በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *