News

ተቋሙ ዘርፈ ብዙ የአሠራር ችግሮች ላይ በቁጭት በመስራቱ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገቡ ተገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በቀድሞው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) በአሁኑ በኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ አፈጻጸም ላይ በ2013/2014 በጀት ዓመት ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት መሰረት በማድረግ በኦዲቱ ግኝቶች ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኦዲት ግኝቶቹ ላይ ከተቋሙ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሚያዚያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው የውይይት መድረክ እንደተገለጸው ቀደም ሲል ከነበረው ሰፊና ዘርፈ ብዙ ብልሹ አሠራር ተንከባለው የመጡ በርካታ ተቋማዊ ችግሮች በኦዲቱ ወቅት የታዩ ቢሆንም በአዲስ አደረጃጀትና አመራር የተዋቀረው ተቋሙ ችግሮቹን ሊቀርፉ የሚችሉ ተስፋ ሰጪ ተጨባጭ ለውጦችን ለማስመዝገብ ጥረት እያደረገ መሆኑን ካቀረበው ሪፖርት መረዳት መቻሉ ተገልጿል፡፡

ከ2002 ዓ.ም አስከ 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ ከ952.5 ሚሊዮን USD እና ከ27.8 ሚሊዮን EURO በላይ በሆነ ገንዘብ ከግዥ መመሪያና ፍላጎት ውጭ ግዥ ለመፈጸም ውል መገባቱ በመድረኩ ተነስቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ህጋዊ የግዥ ሂደት ያልተከተለና ሰነዶች ያልቀረቡበት ግዥ መፈጸሙ፣ ተቋማዊ አቅምን ያላገናዘቡና አፈጻጸማቸው በእንጥልጥል የቀረ የስራ ውሎች መደረጋቸው፣ ተቋሙ ከምርት ጥራት፣ ከውል ጊዜ እና ጥገናንን ጨምሮ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻር የደንበኞችን ፍላጎት በሚፈለገው ደረጃ ያላሟላና ተደጋጋሚ ቅሬታዎች የቀረበበት መሆኑ፣ የማምረት አቅሙም ከስታንዳርድ በታች ከመሆኑም በላይ ትርፋማ ከመሆን ይልቅ ኦዲቱ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ለተለያዩ ተቋማት መከፈል ያለበት በድምሩ ከብር 12.6 ቢሊዮን በላይ እዳ ያለበት መሆኑ በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡

በክትትል አሠራሩ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያለውና ስታንዳርዱን የጠበቀ የጥገና ጥራት ማረጋገጫ ላብራቶሪ ያልነበረው፣ ተገቢና በጥናት ላይ የተመሰረተ ተቋማዊ አደረጃጀት ያልነበረው እና በዘመናዊ ዘዴ መረጃን የማሰባሰብና የማደረጃት አሠራር የማይከተል መሆኑም የተጠቀሰ ሲሆን ዘመናዊ የማምረቻ ቴክኖሎጂዎችን ከመተግበር፣ የተለያዩ የማምረቻ ጅምር ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ፣ ምርቶቹን ከማስተዋወቅና፣ ከአበልና ሌሎች ክፍያዎች አንጻር በርካታ ክፍተቶች የነበሩበት ከመሆኑም ባለፈ የንብረት አያያዝ፣ አጠቃቀምና አወጋገድ አሠራሩም ጉልህ ችግሮች የነበሩበት መሆኑን የተካሄደው ኦዲት ማሳየቱ ተገልጿል፡፡

የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ክቡር አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎን ጨምሮ በይፋዊ ህዝባዊ ውይይቱ ላይ የተገኙት የተቋሙ አመራሮች ተቋሙ በአዲስ የሪፎርም አደረጃጀትና አመራር እንደገና ከመዋቀሩ በፊት ሰፊና ጥልቀት ያላቸው በርካታ ብልሹ አሠራሮች የነበሩበት መሆኑንና የኦዲት ግኝቶቹም ይህንኑ የሚያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰው ከሪፎርሙ በኋላ ግን የኦዲት አስተያየቶችን መሰረት ያደረጉ የማሻሻያ እርምጃዎች መወሰዳቸውንና ሌሎች ጥቂት የማይባሉ ተስፋ ሰጪና ተጨባጭ ለውጦች ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

የተቋሙ ኃላፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ ተቋሙ ሰፊ ችግር የነበረበት እንደመሆኑ ጊዜን የሚጠይቁ የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና የምርትና አገልግሎት ሽፋንና ደረጃ የበለጠ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ከውጭ ለሚገቡ ግብአቶች የሚውል የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

ከመመሪያ አዘገጃጀትና ትግበራ፣ ከግዥ አፈጻጸም፣ ከምርቶች ጥራት ማረጋገጫ ሥርዓት፣ ከሰው ኃይልና ተቋማዊ አደረጃጀት፣ ከምርምርና ስልጠና፣ ከባንክ ብድር አሠራር፣ የደንበኛ ቅሬታን ከመቅረፍና እርካታን ከመጨመር፣ ተቋማዊ አካባቢንና ገጽታን ከመቀየር፣ ከዘመናዊ አሠራር፣ ከምርቶች ሽያጭ ሥርዓትና አሠራር እና ከንብረት አጠቃቀምና አወጋገድ እና በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነትን ከማስፈን አንጻር የነበሩ ጉድለቶችን በማረም የተሻለ፣ ሀገርን ለመካስ የሚያስችልና ከሀገር ውስጥ ባሻገር ለውጭ ሀገራት ጭምር ምሮቶችን ለማቅረብ በሚያስችል አቅጣጫና መርህ ውጤታማ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተቋሙን አሠራር የሚከታተለውና የሚቆጣጠረው የመንግስት ልማት ድርጅቶችና ይዞታዎች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በቀድሞ አሠራሩና አደረጃጀቱ የነበሩበትን ጥልቀት ያላቸው ጉድለቶች ለማስተካከል እና የሀገር ሀብትን ለህዝብ ጥቅም ለማዋል ከፍተኛና ጉልህ ተግባራት እያከናወነ መሆኑንና በዚህም ተጨባጭ ለውጦች ማስመዝገቡን ጠቅሰው የተቋሙ ጥረት ተስፋ ሰጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊ የሆኑ የቋሚ ኮሚቴና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው የኦዲት ግኝቶቹን ለማስተካከል የተከናወነው ስራ ተቋሙን የሚያስመሰግነው መሆኑን በመጥቀስ በግዥ ሥርዓቱ፣ በተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሰብ፣ በንብረት አያያዝ፣ አጠቃቀም እና አወጋገድ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አተገባበር እና በምርታማነት ላይ ተጨማሪ ስራዎችን በመስራትና የውስጥ ኦዲትን በማጠናከር ቀሪ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ በመጠቆም ለብልሹ አሠራሮች ምክንያት የሆኑ አካላት ላይ ተገቢው የተጠያቂነት እርምጃ እንዲወሰድና በፍርድ ሂደት ያሉ ጉዳዮችን የመከታተል ስራም መጠናከር እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

ማሻሻያዎቹ በክትትል ኦዲት የሚረጋገጡ መሆኑን ጠቅሰው ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተሰጡ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ አስተያየቶችን መሰረት በማድረግ ጉድለቶችን ለማረም የተሰሩ ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን የጠቆሙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው የማሻሻያ እርምጃዎችን ማጠናከርና እልባት ላለገኙ ቀሪ ግኝቶች ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አክለውም በገንዘብና መመሪያን ባልተከተሉና ጥናትና ዕቅድን መሰረት ባላደረጉ ግዥዎች፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በኮንትራክት አስተዳደር፣ በደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ፣ በተሰብሳቢና ዕዳን ጨምሮ በተካፋይ ሂሳብ እና በጠፉ ንብረቶች ረገድ ያሉ ክፍተቶችን በማስወገድ ተቋሙ ከተሰጠው ተልዕኮና ከስሙ አንጻር ምርቶችን ከመገጣጠም ባለፈ እራሱ የኢንዱስትሪ ግብአቶችንና የማምረቻ ማሽነሪዎችን የማምረት አቋም ላይ ሊደርስ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው ተቋሙ የኦዲት ግኝት ማሻሻያዎችን መሰረት አድርጎ ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው የአሁኑ አመራር ቀደም ሲል ከነበረው ብልሹ አሠራር ትምህርት ወስዶ የተሻለ ስራ ለመስራት እያደረገ ያለውን ጥረት ማጠናከር አለበት ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የተከናወኑና በሪፖርት የቀረቡ ተግባራትን አፈጻጸም በመስክ ምልከታ እንደሚያረጋግጥ የጠቆሙት ም/ሰብሳቢዋ በተቋም ግንባታ እና የአሠራር ስርዓት እንዲሁም ትርፋማ ከመሆን አኳያ እና የአስተሳሰብ ለውጥ ከማምጣት አንጻር የበለጠ ስራ እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ በውይይቱ የተነሱ ጠቃሚ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ የማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር እስከ ግንቦት 5 ቀን 2015 ተዘጋጅቶ እንዲቀርብና በየጊዜው ለሚሰሩ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ ተግባራትም በየሶስት ወሩ ሪፖርት እንዲቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *