የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት በ2009 በጀት አመት በፋይናንስ ኦዲት የተገኙበትን ግኝቶች ለማረም አበረታች ጥረት ቢያደርግም በ2010 የኦዲት ግኝቶቹ ይበልጥ ጨምረው በመገኘታቸው ያለፈውን ስህተት ከማረም ባለፈ ዳግም እንዳይከሰቱ ጭምር መስራት እንዳለበት ተገለጸ፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢንስቲትዩቱ የ2009 በጀት አመት ላይ ያደረገውን የሂሳብ ኦዲት መሰረት በማድረግ ህዝባዊ ይፋዊ ስብሰባ ግንቦት 14፣ 2011 ዓ.ም አድርጓል፡፡
ኦዲቱ በኢንስቲትዩቱ ላይ ካገኛቸው ግኝቶች ውስጥ ተቋሙን ለለቀቁ ሰራተኞች ብር 5,586 ከፍሎ መገኘቱ፣ ለስራ ኃላፊዎችና ለተመራማሪዎች በደመወዝና አበል መልክ ከከፈለው ክፍያ ውስጥ የስራ ግብር ብር 1,753,234.22 ተቀንሶ ለሚመለከተው አካል ገቢ አለመደረጉ እና ከአንድ ወር በላይ ለትምህርት ወደውጭ ሀገር ለሄዱ ተመራማሪ መከፈል ከነበረበት ደመወዝና አበል በላይ ብር 66,353.50 መከፈሉ ይገኙበታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከሁለት እስከ ሰባት ዓመት የቆየና በተለያዩ የሂሳብ መደቦች ከልዩ ልዩ አካላት ሳይሰበሰብ የቀረ በድምሩ ብር 8,573,950.94 እና በዚሁ ጊዜ ውስጥ ለተለያዩ አካላት መከፈል ሲገባው ያልተከፈለ በድምሩ ብር 4,206,375.34 መኖሩን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡
ለላብራቶሪ እቃዎች ግዥ ከተከፈለ ገንዘብ ውስጥ በድምሩ 138,506.88 እንዲሁም ከኢንስቲትዩቱ የቢሮ ኪራይ ክፍያ ገቢ መደረግ የሚገባው ተርን ኦቨር ታክስ ብር 4,800 በድምሩ ብር 143,306.88 ለሚመለከተው አካል ገቢ አለመደረጉም በኦዲቱ ተመልክቷል፡፡
ከዚህም ሌላ ከመደበኛ ወጪ ብር 3,833,736.89 ከበጀት በላይ ወጪ መደረጉ፣ ከመደበኛ በጀት በተለያዩ የሂሳብ መደቦች ከ10% በላይ ብር 6,248,015.15 ስራ ላይ አለመዋሉ፣ ከካፒታል ወጪ ከ10% በላይ ብር 13,695,056.23 ስራ ላይ አለመዋሉ እንዲሁም ከተፈቀደው ተጨማሪ በጀት ብር 5,828,792.63 ውስጥ ብር 1,305,252.40 በሂሳብ መግለጫ ያልተያዘ መገኘቱን ኦዲቱ ተመላክቷል፡፡
በንብረት አያያዝ በኩልም ለቋሚ ዕቃዎች መለያ ቁጥር በተሟላ ሁኔታ አለመሰጠቱ፣ አራት ተሽከርካሪዎች ከሁለት እስከ አራት ዓመት በብልሽት አገልግሎት ሳይሰጡ መቆየታቸው፣ በእጃቸው የሚገኝ ንብረት በአግባቡ ሳይመልሱ የለቀቁ ሠራተኞች መኖራቸው፣ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ አራት ተሽከርካሪዎችና አገልግሎት የማይሰጡ ሌሎች ንብረቶች ሳይወገዱ መገኘታቸው ተጠቅሷል፡፡
በእነዚህ የኦዲት ግኝቶች ላይ ስለተወሰደው የማስተካከያ እርምጃማብራሪያ እንዲሰጥ ቋሚ ኮሚቴው በጠየቀው መሰረት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ማርዮና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የስራ ኃላፊዎቹ በሰጡት መልስ ተቋሙን ለለቀቁ ሰራተኞች ለደሞዝ አላግባብ ከተከፈለው ብር 5,586 ውስጥ 3,915.46 መመለሱን፣ ከደሞዝና አበል ክፍያ ውስጥ ተቀንሶ ለሚመለከተው አካል መግባት የነበረበት የስራ ግብር ብር 1,753,234.00 ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተደረገ ግንኙነት በገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሰረዝ መደረጉን እንዲሁም ወደውጭ ለትምህርት የሄዱት ግለሰብ አላግባብ በትርፍ የተከፈላቸውን ብር 66,353.50 በሙሉ እንዲመልሱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ የሂሳብ መደቦች ከልዩ ልዩ አካላት ሳይሰበሰብ ከቀረው በድምሩ ብር 8,573,950.94 ውስጥ ከ6.5 ሚልዮን ብር በላይ መወራረዱን በየሂሳብ መደቡ በዝርዝር ገልጸው ቀሪውን ለማስመለስ ሂደት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በአንጻሩም ለተለያዩ አካላት መከፈል ካለበት ውስጥ አብዛኛው መከፈሉንና ቀሪውም በሂደት ላይ እንዳለ አስረድተው ለአብነትም ከልዩ ተከፋይ ብር 3,334,671.05 ውስጥ ብር 2,327,809.05 መከፈሉንና በምዝገባ ስህተት በተከፋይ በተያዘው 689,576.78 ብር ጉዳይ ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ውይይት እየተደረገበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ከላብራቶሪ እቃ አቅራቢው ድርጅት ላይ መቀነስ ያለበት ገንዘብንም በተመለከተ ጉዳዩ በሂደት ላይ እንዳለ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
ከበጀት አጠቃቀም ጋር ተያይዞም ለሁለት የላብራቶሪ ህንጻዎች ግንባታ 75 ሚልዮን ብር ተፈቅዶ እንደነበረና በጨረታው ላይ ተጫራቾች ተደጋጋሚ ክስ በማንሳታቸው ገንዘቡ በወቅቱ ጥቅም ላይ ሳይውል እንደቀረ በማስታወስ በ2010 ግን በጀቱ ወደ 187 ሚልዮን አድጎ ህንጻዎቹ እየተሰሩ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ሳይመዘገብ የተገኘው የተፈቀደ ተጨማሪ በጀት ብር 1,305,252.40 የሂሳብ ምዝገባ ማስተካከያ ምዝገባ ባለመደረጉ የተፈጠረ እንደሆነና ማስተካከያ መደረጉንም አክለው አስረድተዋል፡፡
በንብረት አስተዳደር ረገድ ለቋሚ እቃዎች መለያ ቁጥር እንደተሰጣቸው፣ በአገልግሎት ከማይሰጡ እቃዎች ውስጥ በጨረታ እንዲወገዱ መደረጉን እንደኮምፒዩተር ያሉት ቁሳቁሶች ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተልከው እንደተወገዱ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ተበላሽተው የቆሙ አራት ተሸከርካሪዎች ተጠግነው ስራ እንደጀመሩና መወገድ ካለባቸው አራት ተሽከርካሪዎች ውስጥም ሁለቱ እንደተወገዱ አንደኛው ደግሞ እንዲወገድ ለመንግሰት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት እንደተጠየቀ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ሌላም በውሰት የተሰጡ ንብረቶችም እንዲመለሱ እንደተደረገና ዋስትና ያላስያዙ ሰራተኞችም እንዲያስይዙ እንደተደረገ አብራርተዋል፡፡
ከቋሚ ኮሚቴው፣ ከግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት በግኝቶቹና ተያያዝ ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በ2009 በጀት አመት ለሰራተኞች አላግባብ የተከፈለ ክፍያ ላይ እርምጃ በመውሰድም በ2010 ጨምሮ መገኘቱንና ይህም ተቋሙ ከኦዲት ግኝቱ እንዳልተማረ እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡ እንዲሰረዝ የተደረገውን የብር 1.75 ሚልዮን የስራ ግብር በተመለከተም ሲገልጹ የስራ ግብር ሊሰረዝ የሚችል የግብር አይነት ባለመሆኑ ለገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሰረዝ መቅረቡ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሰረት ተሰብሳቢ ሂሳብን አስመልክቶም በ2009 በጀት አመት ተሰብሳቢ በነበረው ብር 4.2 ሚልዮን ላይ ኢንስቲትዩቱ እርምጃ እንደወሰደ ቢገልጽም በኦዲት የተረጋገጠ ያልተሰበሰበ ቀሪ ብር 3.4 ሚልዮን ያለ በመሆኑ አጥጋቢ ባለመሆኑ ተቋሙ ገንዘቡን ለማስመለስ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ ተከፋይ ሂሳብ ላይ እርምጃ እንደተወሰደ ቢገለጽም የቅጣቱና የወለዱን መጠን ብር 99,125.50 ባለጉዳዩ መክፈል ሲገባው ከመንግስት ካዝና ወጥቶ መከፈሉ ትክክል እንዳልሆነ በአጽንኦት ገልጸው ተከፋይ ሂሳቦች በወቅቱ መከፈል እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ ከበጀት አጠቃቀም ጋር በተያያዘም በ2010 በጀት አመትም ከበጀት በላይ ተቋሙ በመጠቀሙ ከባለፈው ኦዲት እንዳልተማረ ክብርት ምክትል ዋና ኦዲተሯ ገልጸው ለበጀት አጠቃቀም ትኩረት መስጠት ያሻል ብለዋል፡፡
ባጠቃላይም የተቋሙ ሂሳብ መሻሻል እንዳላሳየ፣ በ2009 በጀት አመት ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት አስተያየት ተሰጥቶት እንደነበረና በ2010 በጀት አመት ደግሞ ለኦዲቱ በቂ የሂሳብ ሰነዶች ባለማቅረባቸው የኦዲት አስተያየት ሊሰጠው እንዳልቻለ ክብርት ወ/ሮ መሰረት ገልጸው ኦዲቱን በአግባቡ አይቶ ከችግሩ የሚወጣበትን መንገድ መፈለግ አለበት ብለዋል፡፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ በኦዲት ግኝቱ መሠረት ተቋሙ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ እርምጃ ለመውሰድ እያደረገ ያለው ጥረት ጥሩ ቢሆንም ኦዲቱ በናሙና የሚሰራ በመሆኑ አሰራሩን አስፍቶ ማየት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ላልሰሩበት ቀን ደሞዝ ተቀብለው የሚለቁ ሰራተኞችን ተከታሎ ገንዘቡን ማስመለስ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ጉዳይ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና ገንዘብ ሚኒስቴር አብረው መስራት እንዳለባቸውና የስነ-ምግባር ጸረ-ሙስና ኮሚሽንም የሰራተኞች መሰል ድርጊት እንዳይፈጽሙ ስነምግባራቸው እንዲያድግ ተከታታይ ስራ መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የግብር አዋጁ ከሚፈቅደው ውጪ ገንዘብ ሚኒስቴር የገቢ ግብር መሰረዙ ልክ እንዳልሆነና ለወደፊትም ችግር የሚፈጥር መሆኑን ክቡር አቶ ገመቹ አስረድተዋል፡፡
ባጠቃላይ የ2010 የኦዲት ግኝት በግኝቶቹ ስፋት አይነትና በመጠን ጨምሯል ያሉት ክቡር ዋና ኦዲተሩ በ2009 በጀት አመት ግኝቶች ላይ እርምጃ መውሰዱ ጥሩ ቢሆንም ተመሳሳይ ግኝቶች ለወደፊቱ እንዳይከሰቱ አስቦ ችግሮችን ከስር መሰረቱ ለመፍታት አስፍቶ በማየት መሰረታዊ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡
በቋሚ ኮሚቴው የክዋኔ ኦዲት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ መ/ቤቱ ችግሩን ለመፍታት የሄደበት አግባብ ጥሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የስራ ግብር የማይሰረዝ ግብር ሆኖ እያለ በምን አግባብ ገንዘብ ሚኒስቴር እየሰረዘው እንዳለ ሚኒስቴር መ/ቤቱ መፈተሽ እንዳለበትና የሥራ ግብር የገቢ ምንጭ በመሆኑ የገቢዎች ሚኒስቴር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ አሰራሩ እንዲስተካከል የራሱን ጥረት ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ተቋሙ በፋይንንስና በሰው ሀይል ራሱን ማደራጀትና ሰራተኛውን አቅም መገንባት እንዳለበት እንዲሁም ገንዘብ ሚኒስቴርም በዚህ ውስጥ የራሱን ድጋፍ መስጠት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ አመራሮች የተቋሙ ፋይናንስ አሰራር ግልጽነት ባለው መንገድ መመራት እንዳለበት ግልጽ ግንዛቤ ይዘው መስራት ይገባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡