በኢትዮጵያ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ስር በሚገኘው የአዳሚቱሉ የፀረ- ተባይ ማምረቻ ፋብሪካ አፈጻጸም ላይ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ አስከ 2013 ዓ.ም ሲንከባለሉ የመጡ በርካታ የአፈጻጸም ችግሮች መኖራቸውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2013/2014 በጀት ዓመት ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት መረጋገጡ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተገለጸ፡፡
ፋብሪካው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በመስፈርትነት ካስቀመጠው የልኬት መጠን በላይ የሆኑ አካባቢን የሚበክሉ የኬሚካል ብናኞችን ወደ አየር ይለቅ እንደነበር እና በምርት ጥራት እንዲሁም ፍትሀዊና ሰፊ የግብይት አሠራርን ከመፍጠር አንጻር ዝቅተኛ አፈጻጸም ማሳየቱ በኦዲቱ መረጋገጡ ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም በፋብሪካው ህጋዊ የግዥ አሠራርን ያልተከተሉ በርካታ ግዥዎች መፈጸማቸውን ጨምሮ ከብር 4.7 ሚሊዮን በላይ የሆነ ገንዘብ በወቅቱ ባለመሰብሰቡ የይርጋ ጊዜው ያለፈበት በሚል እንዲሰረዝ ጥያቄ መቅረቡ እና ከብር 5.2 ሚሊዮን በላይ ሊሰበሰብ የሚችል ተሰብሳቢ ሂሳብም እስከ ኦዲቱ ጊዜ ድረስ ያለመሰብሰቡ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የአፈጻጸም ክፍተቶች መታየታቸው ተገልጿል፡፡
ዶ/ር ሁንዴሳ ደሳለኝ የኢትዮጵያ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ በተነሱት የኦዲት ግኝቶች ላይ ሰፊ ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን የኦዲት ግኝቶቹ ትክክለኛ መሆናቸውንና ለፋብሪካው አሠራር መሻሻልም አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከኦዲቱ በኋላ በአካባቢ ጥበቃ፣ በግዥ፣ በተሰብሳቢ ሂሳብ እና በሌሎች አሠራሮች ላይ የታዩትን የኦዲት ግኝቶች ለማሻሻል በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውንና በዚህም በፋብሪካው አሠራር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ጨምረው የገለጹት ኃላፊዎቹ ለግብአት መግዥያ የሚውል የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና በ2002 ዓ.ም የወጣው አዋጅ አስከአሁን ያለመሻሻሉ ለስራቸው እንቅፋት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት ግኝቶቹን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት የፋብሪካውን የአሠራር ችግሮች ለመፍታት እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች በጎ መሆናቸውንና ከግኝቶቹ ስፋትና ከባድነት አንጻር ቀጣይ እርምጃዎችን በመውሰድ በምርት ጥራት፣ በግዥ፣ በግብይት ሂደት፣ በተሰብሳቢ ሂሳብ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጠንካራ የማሻሻያ እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አክለውም ግኝቶቹ አሠራርን በዕቅድ ካለመምራት የመነጩ በመሆናቸው የኦዲት ግኝቶቹን የዕቅድ አካል በማድረግ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በሰጡት አስተያየት የኦዲት ግኝቶቹ በእውነታ ላይ የተመሰረቱና ተጨባጭ መሆናቸውን ጠቅሰው ለመ/ቤቱ በተላከው የኦዲት ግኝት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር ላይ የተጠቀሱ እርምጃዎችን በትክክል በመተግበር እርምጃዎቹ ያመጡትን ለውጥ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በበኩላቸው ኦዲቱ ከዳሰሳ ጥናት ጀምሮ ደረጃ በደረጃ የተካሄደ መሆኑን በመጥቀስ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ኦዲቱ እስከተከናወነበት 2013 ዓ.ም ድረስ ለበርካታ ዓመታት እየተንከባለሉ የመጡና እርምጃ ያልተወሰደባቸው ግኝቶች በኦዲቱ ወቅት መታየታቸውን ገልጸዋል፡፡
የተፈጸሙ ግዥዎች በዕቅድ ያልተመሩና መመሪያቸው ያልጸደቀ፣ የግዥ ህግን የጣሱና ወጪ ቆጣቢ ያልነበሩ መሆናቸውን ጨምረው የገለጹት ክብርት ዋና ኦዲተሯ የአዋጭነትና የአካባቢ ሁኔታ ጥናት ክፍተትን ጨምሮ በምርት ግብአት ጥራት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በገበያ ጥናትና ተደራሽነት፣ በአፈጻጸም፣ በተሰብሳቢ ሂሳብና በሌሎችም የታዩ ክፍተቶችን በማረም የፋብሪካውን ርዕይና ተልዕኮ የሚመጥን አሠራር በመስራት የምርት ግብአቶች በውጭ ምንዛሬ የሚመጡ መሆናቸውን ታሳቢ ያደረገ አፈጻጸም ማሳየት ይገባል ብለዋል፡፡
የማጠቃለያ አስተያየት የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በበኩላቸው የኦዲት ግኝቶቹ በውጤታማነት፣ በምርት ሂደት ህጋዊነት እና በምርት ግብይትና ፍትሀዊ ስርጭት ረገድ የታዩ ክፍተቶችን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን በመጥቀስ ፋብሪካው የኦዲት ግኝቶቹን በማስተካከል ውጤታማ ስራ እንዲሰራና ለዚህም በመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ አዲስ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር በ10 ቀናት ውስጥ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡