የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሰራተኞችን አስተዳደር በተመለከተ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው ደንብ ቁጥር 8/2010 እንዲሁም ደንቡን ተከትሎ በተዘጋጀው የመ/ቤቱ የሰራተኞች ምልመላና መረጣ አፈጻጸም ረቂቅ መመሪያ ላይ የመ/ቤቱ የድጋፍ ዘርፍ ሰራተኞችና አመራሮች የካቲት 13፣ 2011 ዓ.ም ተወያዩ፡፡
በመድረኩ ላይ የመ/ቤቱ የህግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አወቀ አግዘው የመ/ቤቱ ሰራተኞች አስተዳደር ደንብ እንዲጸድቅ የተደረገው ከፍተኛ ጥረት ፍሬ ማፍራቱ የመ/ቤቱን አስተዳደራዊና የሙያ ነጻነቱን ለማስጠበቅ የሚያስችል ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የደንቡ መጽደቅ መ/ቤቱ በሰው ሀይል ቅጥርና አስተዳደር ረገድ አደረጃጀቱን፣ የሰራተኛ ቅጥሩንና አስተዳደሩን እንዲሁም በጀቱን፣ ደመወዝንና ጥቅማጥቅምን በራሱ አጥንቶና በጸደቀው ደንብ መሰረት በሚቋቋመው የኦዲት ኮሚሽን አማካኝነት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ለማጸደቅ እንደሚያስችለው አቶ አወቀ ገልጸዋል፡፡
አቶ አወቀ ደንቡ ከፌዴራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 ውስጥ ያሉትን መሰረታዊ መርሆዎች ሳይለቅ ከተቋሙ የተለየ የስራ ባህሪ አኳያ የተዘጋጀ ራሱን የቻለ ልዩ ህግ እንደሆነ በመግለጽ በዚህ አግባብ እንዲያካትታቸው በተደረጉና ሰራተኛው ግንዛቤ ሊይዝባቸው ይገባል በተባሉ የተለዩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ገለጻ አድርገዋል፡፡ መ/ቤቱ ይህንን ደንብ በአግባቡ ስራ ላይ የማዋል ኃላፊነት እንዳለበትና ሰራተኛውም ደንቡን በመከተል መ/ቤቱ በራዕዩ ያስቀመጠውን በአህጉር ደረጃ ምርጥ የኦዲት ተቋም የመሆን ግብ እንዲያሳካ የራሱን ሚና መጫወት እንደሚጠበቅበት ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
የመ/ቤቱ የሰው ሀብት ስራ አመራር ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ጌታቸው መ/ቤቱ ባዘጋጀው የሰራተኞች ምልመላና መረጣ አፈጻጸም ረቂቅ መመሪያ ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
መመሪያው በምክር ቤቱ የጸደቀውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የሰራተኞች ደንብ ተከትሎ ተግባራዊ ለማድረግ ሲባል የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት አቶ አሸናፊ የጸደቀውን የሰራተኞች አስተዳደር ደንብ፣ በስራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን እንዲሁም የተቋሙን ተልዕኮና የወደፊት ግብ በማገናዘብና በማጣጣም እንደተዘጋጀ አስረድተዋል፡፡
አቶ አሸናፊ መመሪያው ቅጥርና ምልመላን፣ የደረጃ እድገትን፣ ዝውውርን፣ በተጠባባቂነት ማሰራትን እንዲሁም ማትጊያና ማበረታቻን የተመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮችን መያዙን ገልጸው ትኩረት በሚሹ ድንጋጌዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ረቂቅ መመሪያው ከሰራተኞች የሚሰበሰበውን ግብአት በማካተት ዳብሮ እንደሚጸድቅ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በቀረቡት ገለጻዎች ላይ የመ/ቤቱ ሰራተኞች ላቀረቧቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሰራተኞችን አስተዳደር በተመለከተ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው ደንብ ቁጥር 8/2010 ከታህሳስ 16 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ ውሏል፡፡
በቀጣይ ከኦዲት ዘርፍ ሰራተኞችና አመራሮች ጋር በደንቡና በረቂቅ መመሪያው ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡