News

በዘርፈ ብዙና ስርዓተ ጾታ አካታችነት ላይ ያተኮረ የስልጠናና የውይይት መርሀ ግብር ተካሄደ-በመርሀ ግብሩ ተሳታፊ የሆኑ የመ/ቤቱ የማኔጅመንት አባላት አዲስ በተዘጋጀው የዘርፈ ብዙና ስርዓተ ጾታ ማካተት ትግበራ ረቂቅ ማኑዋል ላይ የማዳበሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

 

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የማኔጅመንት አባላት የተሳተፉበት በዘርፈ ብዙና ስርዓተ ጾታ አካታችነት ላይ ያተኮረ የስልጠናና የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡

መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት የስልጠና ማዕከል የተጀመረው መርሀ ግብር አስከ ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት የተካሄደ መሆኑ ታውቋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ በመገኘት መርሀ ግብሩን ያስጀመሩ ሲሆን የስልጠናና የውይይት መድረኩን ዓላማና ፋይዳ አስመልክቶ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

መድረኩ በዘርፈ ብዙና በስርዓተ ጾታ አካታችነት ዙሪያ ጠቃሚ የአቅም ግንባታ ስልጠና የሚሰጥበትና በአዲስ መልክ ለተዘጋጀው የመ/ቤቱ የዘርፈ ብዙና የስርዓተ ጾታ አካታችነት የትግበራ ረቂቅ ማኑዋል ግብአት ለማሰባሰብ የሚረዳ የውይይት መድረክ መሆኑን ክብርት ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል፡፡

መ/ቤቱ በዘርፈ ብዙና በስርዓተ ጾታ አካታችነት ተግበራ ላይ አበረታች እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን በመክፈቻ ንግግራቸው ያስታወሱት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የመ/ቤቱ ሴት ሠራተኞች ለመደጎም የገቢ ማስገኛ አደረጃጀት ፈጥሮ ፋይዳ ያለው ስራ እየተሰራ መሆኑ እና ለሴት ሠራተኞች የትምህርት ዕድሎችን የማመቻትና ወደ ቀጣይ የስራ እርከን ለማሳደገም ልዩ ትኩረት መሰጠቱ በዘርፉ ላይ እየተደረጉ ካሉ የመ/ቤቱ ጠንካራ እንቅስቃሴዎች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የመ/ቤቱን የስርዓተ ጾታ ኦዲት ስራ ተገቢ በሆነ ስርዓት ለመምራት የስርዓተ ጾታ ኦዲት ትግበራ ማኑዋል ተዘጋጅቶ በስራ ላይ መዋሉም ሌላው ጠንካራ ስራ መሆኑን የጠቀሱት ክብርት ዋና ኦዲተሯ በጉዳዩ ላይ የሚታዩ የአፈጻጸም ክፍተቶችን በማረም የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ተቋሙ እንደዋና ኦዲተር መ/ቤት እነዚህን ሥራዎች በተቋሙ ውስጥ ከመተግበር ባለፈ ድርብ ኃላፊነት እንዳለበት ዋና ኦዲተሯ ጠቁመው  ኦዲት በሚያደርጋቸው ተቋማት ውስጥም እንደ ሀገር የወጡ የዘርፈ ብዙና የስርዓተ ጾታ ህጎች በአግባቡ ተፈጻሚ መሆናቸውን በኦዲት ሥራ የማረጋገጥ እና ያሉ ክፍተቶችም እንዲስተካከሉ የማመልከት ሚና ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በስልጠናውና በውይይት መድረኩ የሚገኙ ግብአቶች መ/ቤቱ እያከናወነ ያለውን የስርዓተ ጾታ ኦዲት መሰረት አድርጎ በዘርፉ ላይ ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ ለመሆን የሚያስችሉ እንዲሁም ረቂቅ ማኑዋሉን ለማዳበርና የመ/ቤቱን ተግባራዊ የዘርፈ ብዙና የስርዓተ ጾታ ማካተት እንቅስቃሴ የበለጠ ለማጠናከር ፋይዳ ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *