News

በከተማ ፕላን ዝግጅትና አተገባበር ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ተገቢ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተገለጸ

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቀሚ ኮሚቴ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በከተማ ፕላን ዝግጅትና አተገባበር ላይ ለሚታዩ ክፍተቶች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳሰበ፡፡ ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የከተማ ፕላን ዝግጅትና አተገባበርን አስመልክቶ በቀድሞው በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በአሁኑ በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ላይ በ2012/2013 የኦዲት ዘመን ባካሄደው ኦዲት የታዩ ግኝቶች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችን አስመልክቶ ጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቀሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ የኦዲት ግኝቶቹን ተከትሎ በተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦች መሰረት ሚኒስቴር መ/ቤቱ እርምጃ ስለ መውሰዱ ዋና ዋና የኦዲት ግኝቶችን መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎች በቋሚ ኮሚቴው ቀርበዋል፡፡

የከተማ ልማት ስፓሻል ፕላንና የከተሞች ክላስተር ልማት ፕላን አለመተግበሩና ስፓሻል ፕላኑ በክልሎች እንዲዘጋጅ ድጋፍ የማድረግ እቅዱ ተግባራዊ አለመደረጉ፣ በከተማ ፕላን ዕቅድ ዝግጅት ወቅት የፊዚካል፣ የስፓሻል፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረጉ ሂደት የጥናትና ፕላን አተገባበር እንዲሁም የመረጃ ክፍተቶች መታየታቸው፣ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የተዘጋጁ የአካባቢ ልማት እና የነባር ከተሞች ፕላኖች መሬትን ለልዩ ልዩ የከተማ አገልግሎቶች ለማዋል በስታንዳርድ የተቀመጠውን የመሬት አጠቃቀም ምጣኔ ያልተከተሉ መሆናቸው በኦዲት ግኝትነት ተጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም የመሬት አጠቃቀም ፕላን ጥሰትን ለመከላከል የሚያስችል የክትትል፣ የማስተካከያ እርምጃና ግልጽ አሠራር አለመኖሩ፣ የመረጃ አያያዝ ስርዓት በአግባቡ ባለመዘርጋቱ በመሬት አጠቃቀም ላይ ህገ ወጥነት መታየቱ፣  በተጎራባች ክልሎችና ከተሞች መካከል የተቀናጀና የተናበበ የከተማ ፕላን ተዘጋጅቶ በአግባቡ አለመተግበሩ እንዲሁም  በከተሞች መካከል ሚዛናዊ ያልሆነና ሰፊ ልዩነት የሚታይበት የከተሞች  ደረጃ ልዩነት መኖሩ በኦዲቱ ወቅት መታየቱ ተገልጿል፡፡

ከዚህም ሌላ የከተማ ፕላኖች ከመዋቅራዊ ፕላኖችና መሬት ላይ ከሚገኙ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የማይናበቡና ተመጋጋቢ አለመሆናቸው፣ በከተማ ፕላን ዝግጅት ሂደት ማህበረሰቡንና የአስተዳደር አካላትን እንዲሁም የመሰረተ ልማት አቅራቢና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማትን በበቂ ሁኔታ ሊያሳትፉና ሊያቀናጁ  እንዲሁም ግንዛቤ ሊያስጨብጡ የሚያስችሉ ስራዎች በሚፈለገው መጠን አለመሰራታቸው፣ የከተማ ልማት ዝግጅትንና አተገባበርን በበቂ ሁኔታ ሊያግዝ የሚችል ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ፣ አደረጃጀት፣ ቅብብሎሽና ልውውጥ ሥርዓት በሚፈለገው ደረጃ አለመዘርጋቱ እና የከተማ ፕላን ዝግጅትና ትግበራ ደንቦች፣ መመሪያዎች ስታንዳርዶችና የአሰራር ማኑዋሎች ዝግጅትና አተገባበር ሂደት ላይ ክፍተት መኖሩ በኦዲቱ መታየታቸው የተገለጸ ሲሆን  በኦዲት ግኝቶቹ ላይ  የተወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲብራሩ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር  ዴኤታ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀንን ጨምሮ በመድረኩ ላይ የተገኙ የስራ ኃላፊዎች  ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም የክልሎችን ስፓሻል ፕላን ዝግጅት ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ትግበራ ከአለም ባንክ በተገኘ 7.2 ሚሊዮን ዶላር በ7 ክልሎች ፕሮጀክቱ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ በከተማ ፕላን  እቅድ ዝግጅት ላይ ካርታን በግብአትነት ከመጠቀም ባሻገር ታሳቢ መደረግ ለነበረባቸው የጽሁፍ ሰነዶችና  ለሌሎች ሶሺዮ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች  ትኩረት አለመሰጠቱ  የአሠራር ክፍተት መሆኑን  የጠቀሱት የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለማስተካከል ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንና  በሙያው የሰለጠኑ ባለሙያዎች ፍልሰትም በፕላኑ ዝግጅትና ትግበራ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም በክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የከተማ መሬትን በተቀመጠው የ30፣30፣40 እና 30፣25፣45 ስታንዳርድ መሰረት ለተለያዩ አግልግሎቶች ላይ ለማዋል የሚጠየቁ ከፍተኛ የካሳ ክፍያዎችን መሸፍን የሚያስችል አቅም አለመኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ ኃላፊዎቹ የመሬት አጠቃቀም ጥሰቶችን አስመልክተው ሲያስረዱም በህገ ወጥ አሠራሮችና መሬቶችን በከተማ መስተዳድሮችና ሌሎች አካላት እውቅና ጭምር ለጊዜያዊ መጠቀሚያ በሚል የመስጠት ተግባር በመኖሩ የመሬት አጠቃቀምን ከፕላን ውጪ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ተከስተዋል ብለዋል፡፡

የከተማ ፕላንን መሰረት አድርጎ በተጎራባች ክልሎችና ከተሞች መካከል የተቀናጀና የተናበበ አሠራር እንዲኖር የሚያስችል አሠራር አለመኖር ክፍተት እንደ ሀገር የሚታይ ችግር መሆኑን የጠቀሱት የስራ ኃላፊዎቹ በቅንጅታዊና የተናበበ አሠራር የገጠር ከተሞችን በማልማት ወደ ትላልቅ ከተሞች የሚፈልሰውን ማህበረስብ በአካባቢው ሆኖ ህይወቱን እንዲመራ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ መዋቅራዊ ፕላን በእያንዳንዱ ከተማ መዘጋጀትና መተግበር ያለበት መሆኑን ያመላከቱት ኃላፊዎቹ በአዘገጃጀቱና በትግበራው ሂደት የሚታየውን በመሬት ላይ ያሉ  ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያለማድረግ ክፍተት ለመቅረፍ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውንና ለክልሎችም አስፈላጊ የሆኑ የቴክኒክና የግብአት ድጋፎች እየተደረጉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በፕላን ዝግጅትና ትግበራ ላይ ሊኖር የሚገባው የአካባቢውን ማህበረሰብ የማሳተፍና ከመሰረተ ልማት አቅራቢ ባለድርሻ አካላት ጋር መደረግ ያለበት ቅንጅታዊ አሠራር የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል የተሟላ ውጤት  ለማግኘት የሚያስችል ቀጣይ ጥረት እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡ ሀገራዊ የከተማ ፕላን መረጃ አያያዝ፣ አደረጃጀትና ልውውጥ ስርዓቱ በተደራጀ ዘመናዊ የመረጃ ቋት አማካይነት መተግበር እንደሚገባው ያነሱት የስራ ኃላፊዎች ይህን ለማጠናከር የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርጾ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው የሚኒስቴር መ/ቤቱ የከተማ ፕላን የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በማጸደቅ ሂደት በተፈጠረ ክፍተት በወቅቱ ባለመጽደቁ የታዩ የደንብና መመሪያ አዘገጃጀትና ትግበራ ክፍተቶችም  አዋጁ እንደጸደቀ  የሚቀረፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በምላሾቹ ላይ አስተያየቶቻቸውን የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው አባላትና የስብሰባው ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት በኦዲት ግኝቶቹ መሰረት የተወሰዱ እርምጃዎች በቂ አለመሆናቸውንና ከከተማ ፕላን ዝግጅትና አስተዳደር ሁለንተናዊ ሀገራዊ ፋይዳ አንጻር ክፍተቶቹ መስተካከል እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ አክለውም በከተማ ፕላን አዘገጃጀትና ትግበራ ላይ በኦዲቱ የታዩትን የመረጃ አደረጃጀት ክፍተት፣ ማህበረስብና ባለድርሻ አካላትን በአግባቡ ያለማሳተፍ፣ የመሬት አጠቃቀም ጥሰት፣ ከክልሎች ጋር በሚገባው ደረጃ ተናቦና ተግባብቶ ያለመስራት፣ የገጠር ከተሞችን ምቹና የለሙ ያለማድረግ እና የደንቦች መመሪዎችና ስታንዳርዶች ዝግጅትና አተገባበር ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ጠንካራ ጥረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ የስፓሻል ፕላን አዘገጃጀትና ትግበራ፣  የህግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀትና  የመተግበር፣ ህጋዊ ያልሆኑ የመሬት አጠቃቀም ሁኔታዎችን የማስቀረትና በፕላን መሰረት የመመራት እንዲሁም በፕላን ዝግጅትና ትግበራ ላይ ማህበረሰቡንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በበቂ ሁኔታ የማሳተፍ አሠራሮች መተግበር እንደሚገባቸው ጠቁመው በህግ የተሰጡ ስልጣንንና ኃላፊነትን ተጠቅሞና ከክልሎች ጋር ተናቦ የታዩትን ግኝቶች መቅረፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አክለውም የተደራጀ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት ከሌለ በከተማ ፕላን አተገባበር ላይ የህግ ጥሰቶችን እንደሚያስከትል  አመላክተዋል፡፡

በመጨረሻም የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ የኦዲት ግኝቶቹን ለማስተካከል በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል የታየው ጥረት በሚፈለገው ደረጃ ያለመሆኑን ገልጸው መ/ቤቱ የተሰጠውን ስልጣንና ኃፊነት በአግባቡ ስለመወጣቱ ራሱን መፈተሽ አለበት ብለዋል፡፡ አክለውም ህብረተሰቡ መረጃ የማግኘት መብት ስላለው የከተሞች መዋቅራዊ ፕላን ለህዝብ ይፋ መደረግ እንደሚገባው ጠቁመው ይህም ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን ለመተግበር እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡

የኦዲት ግኝት ማሻሻያ ሀሳቦችንና በመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችን በማከል ችግሮቹን ለመቅረፍ አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ ያለበት መሆኑን ያሳሰቡት ሰብሳቢው  ለእርምጃ አወሳሰዱ ትግበራ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በአጭር ቀናት ውስጥ የእርምጃ አወሰሰድ የድርጊት መርሀ ግብሩን አዘጋጅቶ ለቋሚ ኮሚቴውና ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንዲያቀርብ  እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሚመለከታቸው ጉዳዮች ዙሪያ የማስተካከያ አሠራሮችን ቀይሰውና የአፈጻጸም ክትትላቸውን አጠናክረው በከተማ ፕላን አዘገጃጀትና ትግበራ ላይ የሚታዩትን ችግሮች በጋራና በቅንጅታዊ አሠራር ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *