News

በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ የማይወስዱ አካላት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተገለጸ

ኦዲት ተደራጊ ተቋማት የመንግስት ህግን አክብረው የመሥራትና የኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ ተጠያቂ እንደሚሆኑ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ገለጹ፡፡ ክብርት ወ/ሮ መሰረት ይህን የገለጹት ከግንቦት 15-16፣ 2011 ዓ.ም ድረስ ከኦዲት ተደራጊ የፌዴራል ተቋማት ጋር በኦዲት ግኝቶች እርምጃ አወሳሰድ ላይ በመ/ቤቱ አዳራሽ ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው፡፡

በመድረኩ መክፈቻ ላይ ክብርት ወ/ሮ መሰረት በአንዳንድ ኦዲት ተደራጊ ተቋማት ዘንድ በኦዲት በግኝቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የተሻለ ጥረት መኖሩን ገልፀው የእርምት አወሳሰዱ ግን የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዳልደረሰ የ2010 በጀት አመት ኦዲት እንዳሳየ ተናግረዋል፡፡ በተቋማት የተደረጉት ጥረቶችም በአብዛኛው በበጀት አመቱ በተካሄደው ኦዲት የተገኙ ግኝቶችን በማረም ላይ ያመዘኑ እንደሆኑና በቀጣይ ስህተቶቹ እንዳይደገሙ ለማድረግ ሥርዓት መዘርጋት ላይ ትኩረት እንዳላደረጉ ተናግረዋል፡፡ ክብርት ምክትል ዋና ኦዲተሯ አክለውም የበጀት አመቱን ኦዲት ግኝት ብቻ መሠረት በማድረግና ከተገኘው የኦዲት ግኝት በላይ አስፍቶ ባለማየት ምክንያት ታረሙ የተባሉ ግኝቶች በቀጣይ ኦዲት ወቅት በድጋሚ እየተፈጸሙ ብሎም በፊት ያልነበሩ አዳዲስ ግኝቶች ጭምር በተቋማት ላይ እየተገኙ ነው ብለዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሠረት በኦዲቱ መሰብሰብ አለበት የተባለ ገንዘብን ለመሰብሰብ በኦዲት ተደራጊዎች በተደረገ ጥረት የተመለሰ ገንዘብ ቢኖርም አብዛኛው በራሳቸው ያስመለሱት ሳይሆን በገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሰረዝ ያስደረጉት ነው ብለዋል፡፡

በእርምጃ አወሳሰድ ረገድም ኦዲት ተደራጊ ተቋማት የመንግሥትን ህግ ባላከበሩ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ እርምጃ እየወሰዱ አይደለም ብለዋል፡፡ በኦዲት ወቅትም አስፈላጊ መረጃ በወቅቱ በማቅረብ በኩል ተቋማት ድክመት እንዳለባቸውና ይህም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ስራ ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ኦዲት ተደራጊዎች በየዓመቱ ተደጋጋሚ ግኝት እየተገኘባቸውና ተመሳሳይ የኦዲት አስተያየት እየተሰጠባቸው የቀጠሉበትን ባጠቃላይም ካሉበት ሁኔታ ውስጥ ራሳቸውን ለማውጣት ያልቻሉበትንና በኦዲት ግኝት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የተቸገሩበትን ምክንያት ለመረዳት የውይይት መድረኩ እንደተዘጋጀ ጠቅሰው በነዚህ ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውንና ጥያቄያቸውንም እንዲያቀርቡ ክብርት ወ/ሮ መሰረት ጠይቀዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙ ኦዲት ተደራጊ የአስፈፃሚ አካላትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፋይናንስ፣ የግዥና የንብረት አስተዳደርና የውስጥ ኦዲት ኃላፊዎችም የኦዲት ግኝቶችን ለማረም የሄዱበትን ርቀትና በሂደቱ የገጠሟቸውን ችግሮች እንዲሁም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በራሳቸው ላይም ሆነ በጥቅሉ በኦዲት ተደራጊዎች ላይ ከሚያቀርባቸው የኦዲት ግኝቶችና ከሚሰጣቸው የኦዲት አስተያየቶች ጋር ተያይዞ ሊጤኑ ወይም ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች በአስተያየትና በጥያቄ መልክ አቅርበዋል፡፡

የስራ ኃላፊዎቹ በሰጡት አስተያየት ከበፊት ጊዜ ጀምሮ እርምጃ ሳይወሰድባቸው የመጡና የአመቱ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ግኝት ተደርገው የሚቀርቡ ተንከባላይ ሂሳቦች ተቋማትን በተከታታይ በየአመቱ ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት አስተያየት እያሰጣቸው መሆኑንና ይህም በፋይናንስ ሰራተኞች ሞራል ላይ ጉዳት እያስከተለ መምጣቱን በመግለጽ በመጨረሻ ኦዲት የተደረገው በጀት አመት የፋይናንስ አፈፃፀማቸው ብቻ ተወስዶ የኦዲት አስተያየት ቢሰጥ እንደሚሻል ገልጸዋል፡፡

የኦዲት ግኝቱ የተቋማትን በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ነባራዊ የስራ ባህሪ መሠረት ባደረገ መልኩ መሆን እንዳለበትና ኦዲቱ ኦዲት ተደራጊዎች ካለባቸው ችግር እንዲወጡ ደጋፊ እንጂ ስህተት ፈላጊ መሆን እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ተመሳሳይ የኦዲት ግኝቶች በተቋማት ላይ ከአመት አመት የሚገኙበትን ምክንያትና ከዚህ ጋር በተያያዘ መሻሻል በሚገባቸው አሰራሮችና ህጎች ላይ ጥናት በማድረግ ችግሮቹ በዘላቂነት እንዲፈቱ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

እንደዚሁም ለተቋማት የበላይ ሀላፊዎች የሚገዙ ቁሳቁሶችን እንደምሳሌ በመጥቀስ ግልጽ መመሪያ በሌላቸው ነገር ግን በአሰራር ባሉ ጉዳዮች ላይ መመሪያ ማውጣት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ገንዘብ ሚኒስቴር የቆዩና መመለስ የማይችሉ ገንዘቦችን መሰረዝ እንዳለበት፣ በኦዲት ተደራጊ ተቋማትና በዋና ኦዲተር መ/ቤት ኦዲተሮች መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከር እንደሚገባው፣ ተቋማት ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በሚልኩት የኦዲት ግኝቶች የማስተካከያ መርሃ ግብርና የተወሰዱ እርምጃዎች ላይ ግብረ መልስ መስጠት እንደሚስፈልግና መ/ቤቱ የውስጥ ኦዲተሮችን አቅም መገንባት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ ተቋማቸው በተገኙባቸው አንዳንድ ግኝቶች ላይ ያሏቸውን ጥያቄዎችና በማንሳት የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ የተቸገሩበትን ምክንያት የገለጹ ሲሆን በዘወትር የፋይናንስ አስተዳደር ስራቸው የሚገጥሟቸውን ችግሮችም አስረድተዋል፡፡ ከኦዲቱ አሰራር ጋር የተያያዙ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን የተመለከቱ ሌሎች ጥያቄዎችንም አንስተዋል፡፡

ከነዚህም ውስጥ በኦዲት ወቅት የተገኙና መሰብሰብ ሲገባቸው ያልተሰበሰቡ ገንዘቦችን ከተለያዩ ከግለሰቦችና ከድርጅቶች ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከቆይታ ርዝመት፣ ግለሰቦች ከሀገር በመልቀቃቸው ወይም በተለያዩ ምክንያቶች በቅርብ ሊገኙ ባለመቻላቸው፣ ድርጅቶች በመፍረሳቸውና በሌሎች ምክንያቶች ችግር እንደገጠማቸው ገልጸዋል፡፡

በIFMIS አሰራር ላይ ያለ የእውቀት ማነስና በቴክኖሎጂው ላይም ያለው ክፍተት፣ ከረጅም ጊዜያት አንስቶ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉና በሰራተኛው የማይታወቁ መመሪያዎች መኖርና በመንግስት ግዥ ኤጀንሲ በኩል ንብረቶች በወቅቱ ተገዝተው አለመቅረባቸው በጀት አጠቃቀም ላይ ችግር መፍጠሩ ለኦዲት ግኝት መንስኤ እየሆኑ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ለሰራተኞች ማበረታቻ ሽልማት ከተከፈለ ገንዘብ፣ ለተቋም የበላይ ሃላፊዎች ቢሮዎች ከተፈጸመ የቁሳቁስ ግዥ፣ ለደህንነት ስራ ከተከፈለ ክፍያ፣ ለረጅም አመት ከተከማቹ መጣራት ካለባቸው ሂሳቦች፣ በዩኒቨርሲቲ ሴኔቶች (ቦርድ) ከተፈቀዱ ክፍያዎችና በማኔጅመንት ውሳኔ ከሚፈፀሙ ስራዎች ጋር በተያያዘ የገጠሙ ችግሮችን ጠቅሰዋል፡፡ የፋይናንስና የውስጥ ኦዲተር ክፍሎች በሰው ሀይል ካለመሟላታቸው፣ ከፍተኛ የሰራተኛ ፍልሰት ከመኖሩና ከአቅም ክፍተት ጋር የተያያዙ ችግሮችም ተነስተዋል፡፡

በመድረኩ ተካፋዮች በተሰጡ አስተያየቶችና በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዳይሬክተሮችና ማናጀሮች እንዲሁም በክብርት ወ/ሮ መሠረት ዝርዝር ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሠረት ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ውይይቱን ባጠቃለሉበት ወቅት ከመድረኩ የተነሱት ሀሳቦች በግብአትነት አንደሚወሰዱ ገልጸዋል፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከዚህ ቀደምም ከህግና ከአሰራር አኳያ መስተካከል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ኦዲቱን መሠረት በማድረግ ለሚመለከታቸው አካላት ሲያሳስብ መቆየቱንና በዚህም ከህግ ማዕቀፍ ጋር ተያይዞ የተገኙ ውጤቶች እንዳሉ በዝርዝር ገልፀዋል፡፡ በመድረኩ በተነሱ አንዳንድ ጉዳዮች ላይም በቀጣይ መ/ቤቱ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የመ/ቤቱ ፍላጎት ስህተት መፈለግ ሳይሆን በተቃራኒው ተቋማት ከኦዲት ግኝት እንዲወጡ ማገዝ ነው ያሉት ክብርት ወ/ሮ መሰረት ኦዲት ተደራጊ ተቋማትን በአቅም ግንባታ በኩል ለመደገፍም ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ማስረጃን መሠረት በማድረግ የሚሰራ በመሆኑ ተቋማት በኦዲቱ ወቅት አስፈላጊ የሆኑ ማስረጃዎችን እስካላቀረቡና ህግና መመሪያን ያገናዘበ ስራ እስካልሰሩ ድረስ የተገኙ ክፍተቶችን በኦዲት ግኝትነት ማቅረቡ እንደማይቀር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ተቋማት ተንከባላይ ሂሳቦችን እስከመጨረሻው ድረስ ጥረት በማድረግ እስካላስተካከሉ እና በሚመለከተው አካል ውሳኔ እንዲሰጥባቸው እስካላደረጉ ድረስ ወደፊትም ግኝት ሆነው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አላግባብ በተፈጸሙ ክፍያዎች ላይ ክፍያውን የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባና መሰብሰብ ያልተቻሉ ሂሳቦችንና ሌሎች ግኝቶችን እስከመጨረሻው ድረስ በመከታተልና ከሚመለከተው አካል ጋር በመስራት እልባት እንዲያገኙ ማድረግ ከኦዲት ተደራጊ ተቋማት ይጠበቃል ብለዋል፡፡ አክለውም ተቋማት ከአሰራርና ከህግ ማዕቀፍ አኳያ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በዝርዝር ለይተው በቀጥታ ተጠሪ ለሆኑበት አካልና ለሚመለከተው የመንግሰት አካል በማቅረብ እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም ተቋማቱ በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ አለመውሰዳቸው ተጠያቂነትን የሚያስከትል በመሆኑም ትኩረት በመስጠት ከ2002-2009 በጀት አመት ድረስ ባሉ የኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ መውሰድና ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *