News

በኦዲት አተገባበርና ሌሎች አሠራሮች ዙሪያ ያተኮረ የልምድ ልውውጥ ተካሄደ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኦዲት ሂደትና አተገባበር እንዲሁም በሌሎች የመ/ቤቱ አሠራሮች ላይ ያተኮሩ ልምዶቹን አካፈለ፡፡

ከየካቲት 7  እስከ የካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተካሄደው የሁለት ቀናት የልምድ ልውውጥ በመ/ቤቱ  ስልጣንና ኃላፊነት፣ ተልዕኮ እንዲሁም አወቃቀር፣ በፋይናንስና ህጋዊነት ኦዲት፣ በክዋኔ ኦዲት፣ በውጭና የህዝብ ግንኙነት፣ በኢንፎርሜሽን ሲስተም ሰርቪስ እና በሰው ሀብት ስራ አመራር አሠራሮችና አደረጃጀቶች ላይ ያተኮሩ ገለጻዎች ጉዳዮቹ በሚመለከቷቸው የመ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በስፋት ቀርበዋል፡፡

በልምድ ልውውጡ ወቅት በሁለቱም የኦዲት ተቋማት እየተተገበሩ ያሉ አሠራሮች በተሞክሮነት  የተነሱ ሲሆን ማብራሪያ ለሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ገለጻውን ያቀረቡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የስራ ኃላፊዎች ዝርዝር ምላሾችን ሰጥተዋል፡፡

በልምድ ልውውጡ የተሳተፉት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ኦዲተር ዶ.ር አማረ ብርሀኑን ጨምሮ ከመ/ቤቱ የተለያዩ የስራ ክፍሎች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች ናቸው፡፡

በመጨረሻም ስለ ልምድ ልውውጡ ሂደት ተጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡት ዋና ኦዲተሩ ደ.ር አማረ ብርሀኑ ልምድ ልውውጡ በርካታ ፋይዳ ያላቸው ልምዶችና ተሞክሮዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰው ለወደፊቱ የመ/ቤቱ እቅድ ጠቃሚ የሆኑ ግብአቶች የተገኙበትና የአሠራር ክፍተቶችንም ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *